በአውስትራሊያ ጫካ ውስጥ ለአምስት ቀናት የጠፋችው ሴት በወይን መጠጥ ሕይወቷ ተረፈ

በአውስትራሊያ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ ለአምስት ቀናት የጠፋችው የ48 ዓመቷ ግለሰብ አንድ ጠርሙስ ወይን በመጠጣት ህይወቷን ማትረፍ እንደቻለች ተነገረ።

ግለሰቧ ይዛው ከነበረው ጠርሙስ ወይን በተጨማሪም ጣፋጮችንም ይዛ ነበር ተብሏል።

ሊሊያን አይፕ ባለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት በቪክቶሪያ ግዛት በሚገኘው ጥቅጥቅ ባለው የቁጥቋጦ ስፍራ የነዳችውም እናቷን ለመጠየቅ በሚል አጭር ጉዞ ለማድረግም ነበር።

ነገር ግን በአንድ መንገድ ላይ ተሳስታ ከዞረች በኋላ አቅጣጫው የጠፋባት ሲሆን ተሽከርካሪዋም በጭቃ ውስጥ ተጣብቆ መውጣት አቃተው።

የአልኮል መጠጥ የማትጠጣው ይህች ግለሰብ በመኪናዋ ውስጥም በስጦታ ልትሰጥ ያቀደችው የወይን ጠርሙስም ይዛ ነበር።

ከጠፋች ከአምስት ቀናት በኋላም የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች እየበረሩ ሲፈልጓትም ሊያገኟት ችለዋል።

“ልክ እንዳገኙኝ መጀመሪያ የፈለግከት ውሃ እና ሲጋራ ነበር። አምላክ ይመስገን አንደኛዋ ፖሊስ ሲጋራ ሰጠችኝ” በማለት ሊሊያን ተናግራለች።

“በጫካው ውስጥ የምሞት መስሎኝ ነበር። የአደጋ ሰራተኞቹ ባገኙኝ አርብ ዕለትም መላ ሰውነቴ መስራት እያቆመ እንደሆነ እየተሰማኝ ነበር። ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ ላይ ነበርኩኝ” ብላለች።

በሕይወት የመገኘት ተስፋዋ በመነመነበት ወቅት ለቤተሰቦቿ እንደምትወዳቸው የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈች።

ሊሊያን በአቅራቢያዋ ካለችው ከተማ በ60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የተገኘች ሲሆን በጤና እክል ምክንያትም ከመኪናዋ ወርዳ በእግሯ መጓዝ ባለመቻሏ በስፍራው እንደቆየች የቪክቶሪያ ፖሊስ ተናግሯል።

የምትበላው ጥቂት ጣፋጮች ይዛ የነበረ ሲሆን ውሃም አልነበራትም።

“የአልኮል መጠጥ የማትጠጣው ሊሊያን በመኪናዋ ውስጥ የነበረው ብቸኛው መጠጠ ለእናቷ በስጦታ የገዛችው ወይን ነበር ይህም ሕይወቷን አተረፈላት” ሲሉም የወዶንጋ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ማርቲን ትሮፔ ተናግረዋል።

“በጫካው ውስጥ ባለመዘዋወሯና መኪና ውስጥ በመቀመጧ ፖሊስ በቀላሉ እንዲያገኛት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል” ብለዋል ኃላፊው አክለውም።

ሊሊያን ካጋጠማት ውሃ ባለማግኘቷ ያስከተለውን ድርቀት ለመታከም ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም በአሁኑ ወቅት ጤናዋ ተመልሶ ሜልቦርን ወደሚገኘው ቤቷ ተመልሳለች።