ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቶተንሀም ከማንቸስተር ዩናይትድ፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪሰ ሱተን ቶተንሀም ከማንቸስተር የሚያደርጉትን ጨዋታ መገመት ፈጣን ሎተሪ እንደመፋቅ ነው ይላል።
ሱተን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ ጨዋታ ሁለት ግምቶችን አስቀምጧል።
ሌላኛው የ25ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ ከኒውካስል የሚያደርጉት ነው።
ኒውካስል በኢቲሀድ ስታድየም ድል ቀንቷቸው አያውቅም። ከ20 ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ነው አቻ የወጡት። በዚህኛው ዙር ድል ይቀናቸው ይሆን።
"አንዳንድ ስታድየሞች ለአንዳንድ ክለቦች የማይነኩ ናቸው። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አይገባኝም። ውጤቱ መቀየሩ ግን የማይቀር ነው" ይላል ሱተን።
ሱተን አርብ፣ ቅዳሜ እና እሑድ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።
ብራይተን ከቼልሲ
ባለፈው ቅዳሜ ሁለቱ ቡድኖች በኤፍ ኤ ዋንጫ ተገናኝተው ብራይተን ድል ቀንቶታል። ቼልሲ በዚህ ጨዋታ ጥሩ አልነበረም።
የኤንዞ ማሬስካ ቡድን አሁን ያለው አቋም ብዙም የሚያስተማምን አይደለም። ምንም እንኳ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ አራተኛ ቢሆኑም አቋማቸው ወርዷል።
በሌላ በኩል የብራይተን ውጤት ገባ ወጣ ያለ ነው። አሸናፊውን መገመት ከባድ ነው። ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 - 1
ሌስተር ከአርሰናል
የአርሰናል ደጋፊዎች ካይ ሀቨርትዝ ሲጎዳ ጥቅሙ የገባቸው ይመስላል። ሜዳ ላይ ሳለ ሲያጥላሉት የነበረውን አጥቂ አሁን ማሞገስ ይዘዋል።
አጥቂዎቹ ገብርኤል እየሱስ እና ካይ ሀቨርትዝ በጉዳት ምክንያት በያዝነው የውድድር ዘመን ወደ ሜዳ የሚመለሱ አይመስሉም።
አርሰናል ዘንድሮ ምንም ዋንጫ የማያገኝ ከሆነ ደጋፊዎቹ ጥሩ ምክንያት አገኙ ማለት ነው። ቡድኑ ለምንድነው አጥቂ የማስፈርመው የሚለውም ጥያቄ ጎልቶ ይወጣል።
ጥፋቱ የአርቴታ ነው ወይስ የክለቡ ቦርድ? ሀቨርትዝ እና ገብርኤል ብቻ ሳይሆኑ ሳካ እና ማርቲኔሊም ጉዳት ላይ ናቸው።
ነገር ግን አርሰናል ሌስተር ሲቲን ይረታል ብዬ አስባለሁ። ትሮሳርድ የአጥቂውን መስመር እየመራ ይገባል። ራሒም ስተርሊንግም ሊጫወት ይችላል።
ግምት፡ 0 - 2
አስተን ቪላ ከኢፕስዊች
የኢፕስዊቹ አሠልጣኝ ኬራን ማኬና አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ከመሸነፍ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አላውቅም።
አስተን ቪላ በኤፍ ኤ ዋንጫ ቶተንሀምን አሸንፈው ቢያልፉም በሊጉ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች አላሸነፉም።
የኡናይ ኤምሪ ቡድን የተከላካይ መስመር በጉዳት ታምሷል። ኤዝሪ ኮንሳ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ወጥቷል። ነገር ግን በውሰት ያስፈረሙት አክስል ዲሳሲ ሊታደጋቸው ይችላል።
ኢፕስዊች ጎል ያስቆጥራል፤ ቪላ ይረታል።
ግምት፡ 2 - 1
ፉልሀም ከኖቲንግሀም
ፉልሀም በያዝነው የውድድር ዘመን የመጀመሪያዎቹ ወራት በሜዳቸው ድንቅ ነበሩ። ነገር ግን ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አንድም ማሸነፍ አልቻሉም።
ኖቲንግሀም ደግሞ በተቃራኒው ከሜዳቸው ውጪ ጥሩ ውጤት አላቸው። ከሊቨርፑል ቀጥሎ ከሜዳ ውጪ በርካታ ውጤት መሰብሰብ የቻሉት ኖቲንግሀሞች ናቸው።
ይህም ጨዋታ ለግምት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ፉልሀም ውጤት ሊቀይሩ እንደሚችሉ አውቃለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ማንቸስተር ሲቲ ከኒውካስል
ኒውካስል በኢቲሀድ ስታድየም ያለው ታሪክ በጣም አሳፋሪ የሚባል ነው።
ሲቲ ያለፉትን አስር ጨዋታዎች አሸንፏል። ኒውካስል ለመጨረሻ ጊዜ ሲቲን በሜዳው ያሸነፈው በአውሮፓውያኑ 2000 በአለን ሺረር ጎል ነበር።
እርግጥ ነው የሲቲ ወቅታዊ አቋም ደካማ ነው። ቢሆንም ኒውካስል ጎል ከማግባት ውጪ ነጥብ ይዞ ይመለሳል ብዬ አላስብም።
ማንቸስተር ሲቲ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ ተሸንፏል። ከዚህ ጨዋታ በኋላ ወደ ማድሪድ ተጉዞ ሁለተኛውን ጨዋታ ያደርጋል።
ግምት፡ 2 - 1
ሳውዝአምፕተን ከቦርንመዝ
ቦርንመዝን ይህን ጨዋታ ካላሸነፈ የሚያስደነግጥ ነው።
ሳውዝአምፕተን በኤፍ ኤ ጨዋታ እንኳ ድል ሊቀናቸው አልቻለም። በሊጉ አሁን ያላቸውን ነጥብ ይዘው በጊዜ አምነው ወርደው ለሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቢዘጋጁ ይሻላቸዋል።
በተቃራኒው ቦርንመዝ እጅግ የተቀናጀ ቡድን ነው። አጥቂው ጀስቲን ክላይቨርት ድንቅ አቋም ላይ ይገኛል። የተወሰኑ ተጫዋቾች ቢጎዱባቸውም ሲነጫነጩ አንሰማቸውም።
ግምት፡ 1 - 3
ዌስት ሀም ከብሬንትፈርድ
ብሬንትፈርድ ከሜዳው ውጪ ያለው አቋም እምብዛም ነው። ዌስት ሀም ደግሞ ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ያገኘው።
ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስላል። ነገር ግን 1 አቻ ይጠናቀቃል የሚል ግምት የለኝም። ዌስት ሀም ያሸንፋል ብዬ ግምቴን ላስቀምጥ።
አዲሱ የዌስት ሀም አሠልጣኝ የውጤት ቀውስ ውስጥ ያለ ቡድን ነው የተረከቡት። ጃሬድ ቦዌን ከጉዳት ቢመለስ ቡድኑን የሚያነቃቃው ይሆናል።
ግምት፡ 2 - 1
ክሪስታል ፓላስ ከኤቨርተን
ባለፈው ወር ወደ ኤቨርተን የተመለሱት አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ የሚገርም ሥራ ሠርተዋል።
ረቡዕ ምሽት በተደረገው የመርሲሳይድ ደርቢ ኤቨርተን ታላቅ ተጋድሎ አድርጎ 2 አቻ ተለያይቷል። በዚህ ጨዋታ ግን ውጤት የሚቀናቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም ከሊቨርፑል ጋር የነበረው ፍልሚያ አድክሟቸዋል።
ክሪስታል ፓላስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልካም አካሔድ ላይ ናቸው። ማቴታ ጎል ማስቆጠሩን ቀጥሏል። የውጤት ግስጋሴያቸውን ይቀጥሉበታል።
ግምት፡ 1 - 0
ሊቨርፑል ከዎልቭስ
ዎልቭስ ባለፈው የሊግ ጨዋታ ቪላን መርታት ችሏል። በኤፍ ኤ ዋንጫ ግጥሚያም ብላክበርንን በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።
ነገር ግን ወደ አንፊልድ ተጉዘው ውጤት ይዘው ይመለሳሉ ብዬ አልገምትም።
ሊቨርፑል ከኤቨርተን ጋር በነበረው የመርሲሳይድ ደርቢ በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ቀጣዮቹ ሳምንታት ለሊቨርፑል ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ። የሊጉ መሪዎች ከዚህ ጨዋታ በኋላ ከአስተን ቪላ እና ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ነው የሚጫወቱት።
በዚህ ጨዋታ ሞሐመድ ሳላህ ያስቆጥራል፤ ሊቨርፑል ያሸንፋል።
ግምት፡ 3 - 0
ቶተንሀም ከማንቸስተር ዩናይትድ
ይህን ጨዋታ መገመት እጅግ ከባድ ነው። የግምቴ ተቃራኒ እንደሚሆን ግን አልጠራጠርም።
ባለፈው መስከረም ቶተንሀም ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ አቅንቶ 3-0 አሸንፎ ተመልሷል። ነገር ግን ይህ ውጤት ለዚህኛው ጨዋታ ምንም ተፅዕኖ የለውም።
አንዳንድ የስፐርስ ተጫዋቾች ከጉዳት ተመልሰው ሥልጠና ጀምረዋል። ነገር ግን ለዚህ ጨዋታ ምን ያህል ብቁ ናቸው የሚለው ግልፅ አይደለም።
ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ስናቀና አንዳንድ ተጫዋቾች በሩበን አሞሪም ደስተኛ አለመሆናቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ወጥተዋል።
እኔ አሞሪም ጊዜ ይፈልጋል ባይ ነኝ። የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ነው የመጣው። የሚፈልጋቸውን ተጫዋቾች ማስፈረም አልቻለም።
ሁለቱም ቡድኖች ትዕግስት ይፈልጋሉ። ቢሆንም እንደምናውቀው የእግር ኳስ ደጋፊዎች ትዕግስት የላቸውም።
በዚህኛው ጨዋታ አሞሪም ተሽሎ ይገኛል የሚል ግምት አለኝ።
ግምት፡ 1 - 2