ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን በጊዜያዊነት በተባበሩት መንግሥታት ስር እንድትሆን ፑቲን ሃሳብ አቀረቡ
ዩክሬን ብቁ የሆነ መንግሥት እስክትመርጥ ድረስ በጊዜያዊነት በተባበሩት መንግሥታት አመራር ስር እንድትሆን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሃሳብ አቀረቡ።
በኪዬቭ ተቀማጭ ያደረገውን የዩክሬንን አስተዳደር በህገወጥነት የሚፈርጁት የሩሲያው ፕሬዚዳንት አመራሩ እንዲቀየር በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ዩክሬን የፑቲንን ይህንን ሃሳብ "እብደት" ስትል የጠራችው ሲሆን፤ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሪነት የሚደገፈውን የሰላም ስምምነት ለማዘግየት የሚደረግ ስትራቴጂ ነው ብላለች።
ዋይት ሃውስ በበኩሉ የዩክሬን አስተዳደር በህገ መንግሥቱ እና በህዝቡ እንደሚወሰን አጽንኦት ሰጥቷል።
የፑቲን አስተያየት የተሰማው አራተኛ አመት ያስቆጠረውን የዩክሬን ጦርነት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በዋነኝነት እያሸማገለች ባለችበት ወቅት ነው።
ሩሲያ እና ዩክሬን ጥቁር ባሕር ላይ የሚያደርጉትን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረማቸውን ዋይት ሃውስ አረጋግጧል።
ሀገራቱ ሳዑዲ አራቢያ ውስጥ በየግላቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባደረጉት ስምምነት ነው የተኩስ አቁም ለማድረግ የወሰኑት።
ነገር ግን ሩሲያ የጥቁር ባህር የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው ምዕራባውን የጣሉት ማዕቀብ ሲነሳ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ቅድመ ሁኔታዎቿን አስቀምጣለች።
ይህም ሩሲያ የተኩስ አቁሙን ለማደናቀፍ እየሞከረች ነው የሚል ስጋትን አጭሯል።
ፑቲን በሰሜን ሩሲያ በምትገኘው ሙርማንስክ ከተማ የባህር ሰርጓጅ መርከብ ሰራተኞችን ባነጋገሩበት ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ስር የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደርን "ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ አገራት እና ከአጋሮቻችን እና ከጓደኞችን ጋር የምንወያይበት ነው" ብለዋል።
"ይህም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ፤ በህዝብ አመኔታ ያለው ብቁ መንግሥት ወደ ስልጣን ለማምጣት እንዲሁም የሰላም ስምምነትን ለመነጋገር እና ህጋዊ ሰነዶችን ለመፈረም ነው" ሲሉም ነው የተናገሩት።
ሩሲያ፣ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የስልጣን ዘመኑን ስለጨረሰ ህገ ወጥ መንግሥት ነው በማለት የፈረጀችው ሲሆን በዚህም የሰላም ድርድር ለመሳተፍ ህጋዊ መሰረት የለውም ትላለች።
ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው አገራቸው በጦርነት ውስጥ ስለሆነች ምርጫው በህጋዊ መንገድ በወታደራዊ ህግ እንዲዘገይ ተደርጓል ይላሉ።
በጦርነቱ ምክንያት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የዩክሬን ዜጎች በውጭ አገራት ከመፈናቀላቸው ጋር ተያይዞ፤ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጦር ግንባሮች ተሰልፈው ባሉበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው።
ፑቲን ምርጫውን አጀንዳ በማድረግ ዜሌንሰኪ በሰላም ድርድሩ ለመሳተፍ ህጋዊ መሰረት የላቸውም የሚለውን እያንጸባረቁ ይገኛሉ።
ዋይት ሃውስም ከዚህ ቀደም ይህንኑ ሃሳብ ሲያስተጋባ ተሰምቷል።
ፑቲን ምርጫ እንዲካሄድ የማስገደዱ ሁኔታ ከተሳካላቸው ዩክሬንን በጦር ግንባር በማዘናጋት ድልን እንዲቀናጁ ያደርጋቻዋል ተብሏል።