ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ ክልል የዘመዱን ልጅ አግቶ የገደለው ግለሰብ እጁን ለፖሊስ ሰጠ
አንድ ተጠርጣሪ በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ አርሲ ዞን፣ ዶዶላ ከተማ ላገተው የሁለት ዓመት ልጅ የጠየቀው ማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ ባለመፈጸሙ ያገተውን ልጅ መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪው ኢዘዲን ከማል ላገተው የዘመድ ልጅ 100ሺህ ብር ማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፈለው ጠይቆ ነበር።
ይሁን እንጂ የጠየቀው ክፍያ ባለመፈጸሙ ህጻኑን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለ በኋለ እጁን ለፖሊስ መስጠቱ ተገልጿል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ኢንስፔክተር ተሾመ ተኤራ፤ ተጠርጣሪው ዶዶላ ከተማ ከሚገኝ ከራሱ ዘመድ ቤት ህፃኑን ‘ወደ አባቱ ልወስደው ነው’ በማለት ይዞ መሰወሩን ተናግረዋል።
ተጠርጣሪ የጠየቀውን የማስለቀቂያ ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ ህፃኑን ገድሎ አዋልደጌሳ የተባለ አውሬ የቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ መቅበሩን አምኖ እገታውን ከፈጸመ ከ10 ቀናት በኋላ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል።
ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪው ኢዘዲን የካቲት 1/2015 ዓ.ም. ታዳጊውን ይዞ ከተሰወረ በኋላ 100 ሺህ ብር እንዲከፍለው የህፃኑን አባት ይጠይቃል።
የህፃኑ አባት ግን የተጠየቁትን የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመክፈል ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረት ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል።
ኢንስፔክተር ተሾመ ተጠርጣሪው እና የታገተው ህፃን አባት ዝምድና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፖሊስም ታዳጊውን ፈልጎ ለማግኘት እንዲረዳው የህፃኑን ምስል ከአፋልጉኝ ማስታወቂያ ጋር አያይዞ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርቶ ነበር።
“ኢዘዲን ገንዘቡ አልገባልኝም በማለት [ከእገታው] ከሁለት ቀን በኋላ ህፃኑን ገድሎ ቀበረው” ሲሉ ይህ የፖሊስ አባል ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ተጠርጣሪው ከአገር መከላከያ አባልነት ስለማምለጡ መረጃ አለን የሚሉት ኢንስፔክተሩ፤ ሰኞ የካቲት 13/2015 ዓ.ም. ኮፈሌ ከተማ ለፖሊስ እጁን መስጠቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ቀንም ህፃኑ ከተቀበረበት ቦታ ወጥቶ አስክሬኑ ለምርመራ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ጳውሎስ ሆስፒታል ተልኳል ብለዋል።