ኤሎን መስክ ለሠራተኞቹ ማደሪያ በሚል የትዊተርን ቢሮ ወደ ‘ሆቴልነት’ ቀየረ

በቅርቡ ትዊተርን የገዛው ኤሎን መስክ የትዊተርን ቢሮ ለሠራተኞቹ ማደሪያ በሚል ወደ ሆቴልነት መቀየሩ ተነገረ።

ቢቢሲ ወደ መኝታ ክፍሎች የተቀየሩትን የትዊተር ቢሮ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ያገኘ ሲሆን የሳን ፍራንሲስኮ ባለሥልጣናት የሕንጻ ኮድን ጥሷል በሚል እየመረመሩት ይገኛሉ።

አንደኛው ምሥል ተደራራቢ አልጋዎች፣ ቁም ሳጥንና ሸበጦችን ያሳያል።

አዲሱ የትዊተር አለቃ ኤሎን መስክ ድርጅቱን ከገዛ በኋላ ኑሮውን በዋና መሥሪያ ቤቱ እንዳደረገ የተቋሙ የቀድሞ ሠራተኛ ተናግሯል።

በርካታ አወዛጋቢ ሥር ነቀል ለውጦችን እያካሄደ እንደሆነ የሚነገርለት መስክ፤ ባለፈው ወር ለሁሉም የትዊተር ሠራተኞች “እንቅልፍ አልባ በሆነ ሁኔታ ለሥራ እንዲተጉ” የሚል ኢሜይል መላኩ ይታወሳል።

ቅሬታ ያቀረበበት የሳን ፍራንሲስኮ የሕንጻ ቁጥጥር ዲፓርትመንት ጥሰቶችን እየመረመረ መሆኑን አረጋግጧል።

ይህ ያልተዋጠለት መስክ “ለደከሙ ሠራተኞቻችን አልጋ በማቅረባችን” የከተማው አስተዳደር ኩባንያችንን ኢላማ አድርጓል ብሏል።

በአሁኑ ወቅት በሰረዘው የትዊተር መልዕክቱም “ኩባንያው ችግሩ እስኪቀረፍ” ድረስ በቢሮው ውስጥ እንደሚሠራና እንደሚተኛ አስፍሮ ነበር።

ቢቢሲ በትዊተር ቢሮ እንደ አልጋ እያገለገሉ ያሉ ሶፋዎች ያሉበት ምሥልንም አግኝቷል።

በተጨማሪም ስብሰባዎች በሚካሄዱበት ክፍል የማንቂያ ሰዓት እንዲሁም የተነጠፈ አልጋ ይታያል።

“የሆቴል ክፍሎች ይመስላሉ” በማለት አንድ የቀድሞ ሠራተኛ ተናግረዋል።

እኚሁ ሠራተኛ መስክ በሳን ፍራንሲስኮ በሚገኘው የትዊተር ዋና መሥሪያ ቤት በርካታ ምሽቶችን እንደሚያሳልፍ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ቢቢሲ ይህንን አስመልክቶ ለትዊተር ጥያቄዎች ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

የትዊተርን ግዢ ባለፈው ወር ያጠናቀቀው መስክ ሁሉም የኩባንያው ሠራተኞች የወደፊቱ ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰነው ደከመች ሰለቸኝ ሳይሉ ረዥም ሰዓት መስራት ሲችሉ ነው የሚል ቆራጥ መልዕክት አስተላልፏል።

የካሊፎርኒያ ሴናተር ስኮት ዊነር ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ መስክ “ሠራተኞቹን በትዊተር ቢሮ እንዲያድሩ እያደረጋቸው ነው” ብለዋል።

“ለሰዎች ምንም እንደማያስብ ግልጽ ነው። በሱ ተቀጥረው ለሚሠሩ ግለሰቦች ደንታ የለውም” ሲሉም አክለዋል።

የሕንጻ ኢንስፔክሽን ዲፓርትመንት ባለሥልጣን በበኩላቸው ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት “ሕንጻው እንደታሰበው ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል።