ኻን ዩኒስ፡ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነባት የጋዛ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰው ማዕበል ወደ ጋዛዋ ኻን ዩኒስ ከተማ ጎርፏል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን ውጡ ማስጠንቀቂያ ተከትለው መያዝ የሚችሉትን ሸክፈው ከሰሜናዊ ወደ ደቡባዊ ጋዛ ተሰደዋል።
ነዳጅ ያገኙ በመኪና፤ ከተገኘ ደግሞ በፈረስ ጋሪ አማራጭ ያጡ ደግሞ በእግራቸው ኳትነዋል።
የተሰደዱባት ከተማ ግን መጀመሪያም ቋፍ ላይ ነበረ። በአንድ ሌሊት የህዝብ ቁጥሯ በእጥፍ አድጓል። ይህንን ለማስተናገድ ግን ዝግጁ አልነበረችም።
በወንዶች፣ በሴቶችና በህጻናት ያልተጨናነቀ የከተማዋ መንገድ እና ቤት የለም።
ሐማስ እንደሚለው ከሆነ በሰሜን ጋዛ ከሚኖሩ 1.1 ሚሊዮን ህዝብ በ48 ሰዓታት ውስጥ 400 ሺህ ያህሉ ወደ ከተማ አቅንተዋል። እስራኤል ናት ነዋሪዎች ሰሜን ጋዛን ለቀው ወደ ደቡብ እንዲያቀኑ ትዕዛዝ ያስተላለፈችው።
ሩሽዲ አቡ አሉፍ እባላለሁ። እኔም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነኝ። ባለቤቴ፣ ሦስት ልጆቼ አብረውን ናቸው። የሁለት ቀን ምግብ ብቻ ነው የያዝነው።
የእስራኤል የቦምብ ዛቻ እና ያቀደችው ወረራ ብዙዎች እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል። ሐማስ ነዋሪዎች እንዳይወጡ ያቀረበውን ጥሪ ብዙዎች ችላ ብለውታል።
ይህች አነስተኛ በሆነች አካባቢ በሁሉም አቅጣጫ ተከባለች። ከተቀረው ዓለም ተቆራርጣለች። ስለዚህ ያሉት አማራጮች አነስተኛ ናቸው። የደህንነት ጉዳይም ዋስትና የለውም።
ብዙ የጋዛ ነዋሪዎች ቤታቸው ላይ በደረሰው የአየር ጥቃት ያላቸውን አጥተዋል፣ በፍርሃት ተውጠዋል፣ ቀጥሎ ምን አንደሚፈጠርም አያውቁም። ለዚህም ነው ወደ ካን ዩኒስ ያቀኑት።
400 መቶ ሺህ ነዋሪዎች የነበራት ከተማ በአንድ ምሽት የነዋሪዎቿ ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ከተማዋ የሰሜኖቹን ነዋሪዎች ብቻ አታስተናግድም። እአአ በ2014 ከነበረው ጦርነት ሸሽተው የመጡም ይኖሩባታል።
ሁሉም መጠለያ እና ምግብ ያስፈልጋቸዋል። ለምን ያህል ጊዜ የሚለውን ግን ማንም አያውቀውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የከፋው ችግር
ቋፍ ላይ የነበረው አቅርቦት በአሁኑ ወቅት በጣም እየተመናመነ ነው። የህዝብ ማዕበሉ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩ መባባስ ቀጥሏል።
የከተማዋ ትልቁ ሆስፒታል ቀድሞውንም መሠረታዊ የህክምና ቁሳቁስ እያለቀበት ነበር።
አሁን ደግሞ ህክምና ከመስጠት በተጨማሪ የስደተኞች መጠለያም ሆኗል።
የሆስፒታሉ መተላለፊያዎች በስደተኞች ተጣበዋል።
ሐኪሞች በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ለማከም ላይ ታች ይላሉ።
አካባቢው በሰዎች ድምጽ ተሞልቷል።
ሰዎች እዚህ በመምጣታቸው ሊወቀሱ አይገባም።
ሆስፒታሎች በዓለም አቀፍ ህግ ከለላ ስላላቸው በጦርነት ወቅት ለመሸሸጊያነት አስተማማኝ ከሆኑ ቦታዎች መካከል ናቸው።
ይህንን ከግምት በማስገባት ቢያንስ ለአሁኑ እነዚህን ሰዎች ዕድለኞች ናቸው ልንል እንችለለን።
አዳዲስ ስደተኞችን ለመርዳት እጃቸው ማጠሩን ሐኪሞች ይገልጻሉ።
ለታካሚዎች በቀን 300 ሚሊ ውሃ ይታደላል። ስደተኞች ግን ምንም አይደርሳቸውም።
ነዋሪዎች አዲስ ስደተኞችን ያስተናግዳሉ። ብዙዎቹ የካን ዩኒስ ነዋሪዎች ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ነበር የሚኖሩት። አሁን ደግሞ እጅጉን ተባብሷል።
መያዝ ከሚችሉት በላይ ሰዎችን ያስተናግዱ የነበሩ አነስተኛ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አሁን 50 እና 60 ሰዎችን ለማስተናገድ ተገደዋል። በዚህ መልኩ ግን ለረዥም ጊዜ መኖር አይቻልም።
ቤተሰቤ ሁለት ትንንሽ መኝታ ክፍሎች ያለውን ቤት ከአራት ሰዎች ጋር ይጋራል። የተወሰነም ቢሆን የግላችን የምንለው ቦታ አለን። በዚህ በኩል ራሳችንን እንደ ዕድለኞች እንደሆንን ይሰማኛል።
በከተማው ዙሪያ ያሉ ትምህርት ቤቶች በብዙ ሰዎች ተሞልተዋል። ሰዉን ልቁጠር ቢሉም ላይጨርሱ ይችላሉ።
በተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ድርጅት በሚተዳደር አንድ ትምህርት ቤት ሁሉም ክፍሎች ተሞልተዋል። በረንዳውም በሙሉ ተይዟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እናቶች በግቢው ውስጥ በሚገኙ ሜዳዎች ላይ ምግብ ሲያበስሉ የተራቡ ልጆቻቸው ደግሞ በትዕግስት ይጠባበቃሉ።
ተጨማሪ ቦታ ግን የለም። ሰዉ ወደ ጎዳና መውጣቱ አይቀሬ ይመስላል።
ያለው ምግብ እና ነዳጅ ተመናምኗል። ሱቆች ውሃ የላቸውም። የውሃ ማደያዎች ብቸኛው ተስፋ ነው። አሁን አስከፊ ሁኔታ ነው።
ከተማዋ ከጥቃት ግን ነጻ አይደለችም። በየጊዜው በቦምብ ትደበደባለች ። አሁንም በጦርነት ዞን ውስጥ ናት። የፈራረሱ ሕንፃዎች ጎዳናዎቹን ሞልተዋል።
ሐማስ እስራኤልን ማጥቃቱን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ከሆስፒታሉ አቅራቢያ የሮኬት ተኩስ እሰማለሁ። ይህ የበቀል ግብዣ ነው።
የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ቀጣይ ዒላማቸውን ሲያፈላልጉ ተደጋግሞ ይሰማል።
ቦምቦች ይወድቃሉ። ሕንጻዎች ይፈርሳሉ። ሬሳ ማቆያዎቹ እና ሆስፒታሎች ሞልተዋል።
ዛሬ ጠዋት በቤተሰቤ አፓርታማ አካባቢ ቦምብ ወድቆ ነበር። የቴሌፎን አገልግሎት በሙሉ ወይም አብዛኛው ስለተስተጓጎሉ ልጄን ለማግኘት 20 ደቂቃ ፈጅቶብኛል።
ሰዎች እንደዚህ መኖር ይከብዳቸዋል። ወረራው ገና አልጀመረም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋዛ ውስጥ ስለተደረጉ አራት ጦርነቶችን ዘግቤያለሁ። ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቼ አላውቅም።
የቀደሙት ጦርነቶች የቱንም ያህል የከፉ ቢሆኑም ሰዎች ሲራቡ ወይም በውሃ ጥም ሲሞቱ አይቼ አላውቅም። አሁን ግን ይህ የመሆን ዕድል አለው።
ከጋዛ ውጭ ያለው ብቸኛ አማራጭ ወደ ግብፅ ለመሻገር የሚያስችለው የራፋህ መስመር አሁንም ተዘግቷል። ካይሮ መስመሩን ከከፈተች አዲስ ሰብአዊ አደጋ እንደሚያመጣ ታውቃለች።
ከራፋህ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መስመሩ እንዲከፈት የሚጠብቁ አንድ ሚሊዮን የጋዛ ስደተኞች አሉ። መስመሩ ከተከፈተ ትርምስ ይፈጠራል።
እአአ በ 2014 በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከጦርነት ለማምለጥ ሲሞክሩ ተመሳሳይ ነገር ተፈጥሮ ተመልክቻለሁ። የአሁኑ በጣም የከፋ ይሆናል። ግብፅ የምትፈራው ይሄው ነው።
የሰው ጎርፍ በቀላሉ ድንበሩን ጥሶ ያልፋል። በድጋሚ ጥፋት በድጋሚ ትርምስ ይሆናል።














