የ6 ዓመቱ ታዳጊ በጸረ ሙስሊም ጥቃት መገደሉን የአሜሪካ ፖሊስ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, CAIR/Handout via REUTERS
በአሜሪካ ሙስሊም በመሆናቸው የስድስት አመት ታዳጊ እና እናቱን በስለት የወጋው የቤት አከራይ በነፍስ ግድያ እና በጥላቻ ወንጀል ተከሰሰ።
ታዳጊው 26 ጊዜ በስለት መወጋቱንም ፖሊስ ገልጿል።
ጥቃት አድራሹ አድራሹ ጆሴፍ ዙባ የተባለ የ71 ዓመት ግለሰብ ነው።
ግለሰቡ በስለት ከወጋቸው በኋላ የስድስት አመቱ ታዳጊ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን የ32 ዓመቷ እናት ህይወቷ መትረፍ ችሏል።
ከሰሞኑ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን የሐማስ እና እስራኤል ግጭት ተከትሎ ኢላማ መደረጋቸውንም ፖሊስ አስታውቋል።
ፍልስጥኤማዊ- አሜሪካዊ በሆኑት እናት እና ልጅ የተፈጸመው ጥቃት “እንዳሳመማቸው” የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ገልጸዋል።
“እንዲህ አይነት አሰቃቂ የጥላቻ ተግባር በአሜሪካ ውስጥ ቦታ የለውም። ከመሰረታዊ እሴቶቻችን ጋር የሚቃረን ነው” ሲሉም ባይደን ተናግረዋል።
“እንደ አሜሪካውነታችን አንድ ላይ ተባብረን ጸረ ሙስሊምነትንም ሆነ ሁሉንም ዓይነት ጥላቻን እና ጭፍንተኝነትን መቃወም አለብን” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቺካጎ አቅራቢያ በምትገኘው ፕላይንፊልድ አካባቢ በቤት አከራይዋ ጥቃት እየደረሰብኝ ነው የሚል የድንገተኛ ጥሪ ቅዳሜ ዕለት እንደደረሰው ፖሊስ አስታውቋል።
ግለሰቧ “ወደ መታጠቢያ ቤት ሮጣ በማምለጥ ጥቃት አድራሹንም እየታገለችው” እንደነበር ተናግራለች።
እናት እና ልጅ መላ ሰውነታቸው በርካታ ስፍራዎች ላይ በስለት ተወጋግቶ ነው ፖሊስ በስፍራው የደረሰው።
እናት እና ልጅ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን የልጁን ህይወት መታደግ አልተቻለም።
ህጻኑ 26 ጊዜ በስለት መወጋቱም ተረጋግጧል።
“በዚህ ጥቃት ላይ 12 ኢንች ርዝመት እና ባለ ሰባት ኢንች ምላጭ ያለው ወታደራዊ ጥቅም ላይ የሚውል ስለት” እንደሆነም ፖሊስ ገልጿል።
እናት ከባድ ጉዳት ቢደርስባትም ልታገግም እንደምትችል ይጠበቃል።
ህጻኑ ዋዴያ በአሜሪካ የተወለደ ሲሆን እናቱ ከፍልስጥኤም ዌስት ባንክ ግዛት ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት መምጣቷን የአሜሪካ መብት ተሟጋች ቡድን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽን አስታውቋል።












