በዩኬ ለፍልስጥኤም ድጋፋቸውን ለመግለጽ በሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለንደን እና ማንቸስተርን ጨምሮ በበርካታ የዩናይትድ ኪንግደም ከተሞች ፍልስጥኤምን የሚደግፉ ሰልፎች ተካሄዱ።
የፍልስጥኤምን ሰንደቅ ዓላማ የያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም “ነጻ ፍልስጥኤም” ሲሉም ተደምጠዋል።
በለንደን የተደረገው የአደባባይ ሰልፍ የተጀመረው በፖርትላንድ ፕላስ በሚገኘው የቢቢሲ ዋና መሥሪያ ቤት ነው።
የቢቢሲ ሕንጻ መግቢያም ቀይ ቀለም ተረጭቶበት ተገኝቷል።
“ቀይ ቀለም የተረጨው፤ እስራኤል በፍልስጥኤም ሕዝብ ላይ እያደረገችው ባለው የዘር ማጥፋት አድሏዊ ዘገባ በማቅረብ እየተባበረ በመሆኑ ነው” በማለትም ፓለስታይን አክሽን የተባለ የመብት ተሟጋች ቡድን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ በማስፈር ኃላፊነቱን ወስዷል።
ፖሊስ በሕንጻው ላይ የደረሰውን ወንጀል እየመረመርኩ ነው ብሏል።
ቢቢሲ በበኩሉ የፖሊስ ጉዳይ ነው ሲል አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
በለንደን ለፍልስጥኤም በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ከአንድ ሺህ በላይ ፖሊሶች ተሰማርተው ነበር።
ፖሊስ በዚህ ሰልፍ ላይ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።ከነዚህም አንዱ በወንጀል ሌሎች ደግሞ የሕዝቡን ጸጥታ በመረበሽ ተጠርጥረው እንደሆነም አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሃማስ በእስራኤል ላይ የተቀናጀ ጥቃት ከከፈተ አንድ ሳምንትን አስቆጥሯል።
የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን በጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ ባደረገው ጥቃት ቢያንስ 1 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁ 150 ሰዎች ታግተዋል።
እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ነው በሚል በጋዛ ሰርጥ የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን በዚህም ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል ጦር ጋዛ ሰርጥን በሙሉ ከበባ ውስጥ እንድትገባ በማድረግም ውሃ፣ ምግብ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መቋረጡንም ከቀናት በፊት አስታውቋል።
ለፍልስጥኤም የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች በሊቨርፑል፣ ብሪስቶል፣ ካምብሪጅ፣ ኮቨንተሪ፣ ኤዲንብራ እና ስዋንሲን ጨምሮ በበርካታ የዩኬ ከተሞች ተካሂደዋል።
በለንደን በነበረው የድጋፍ ሰልፍ የቀድሞው የሌበር ፓርቲ መሪ ጄረሚ ኮርቢን ንግግር አድርገዋል።
የብሪታንያ ፖለቲከኞች የእስራኤልን የቦምብ ጥቃት ዘመቻ በቸልታ ሊያልፉት አይገባም ብለዋል።
“በዓለም አቀፍ ሕግ የምታምኑ ከሆነ፣ በሰብዓዊ መብት የምታምኑ ከሆነ፣ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ እየፈጸመው ያለውን ነገር ልታወግዙ ይገባል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፎቶው ባለመብት, Reuters












