የፍልስጤም ታዳጊዎች መለቀቅ እና ስምምነቱ ሊራዘም ይችላል መባሉ የጫረው ተስፋ

በሦስተኛው የጋዛ የታጋቾች ልውውጥ ወቅት 39 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስር ቤቶች ተፈተዋል።

ፍልስጤማዊያኑ የተለቀቁት መስከረም 26 ከእስራኤል የተወሰዱ 40 ታጋቾች በመለቀቃቸው ነው።

አርብ ዕለት ከተካሄደው የመጀመሪያው ልውውጥ በኋላ በሶስት ዙር የተለቀቁት ፍልስጤማውያን ቁጥር 117 ደርሷል።

እስራኤል እና ሐማስ በተስማሙት ስምምነት መሠረት የመጨረሻው ልውውጥ ዛሬ እንደሚከናወን ይጠበቃል። ስምምነቱ ሊራዘም ይችላል የሚል ተስፋ ግን ተጭሯል።

በቅርቡ ከተፈቱት ፍልስጤማዊያን እስረኞች መካከል 16 ወራትን በእስር ያሳለፈው ታዳጊው መሐመድ አል-አዋር ይገኝበታል። በመፈታቱ ዙሪያ እናቱ የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማት ተናግራለች።

“በጋዛ በተገደሉት በርካታ ሰዎች ምክንያት ደስታችን የተሟላ አይደለም›› ስትል ከልጇ ጋር ከተገናኙ በኋላ ተናግራለች።

ሌላኛው ታዳጊ አብዱራህማን አል-ዛጋል ከእስር ቢፈታም በእስራኤል ሆስፒታል በህክምና ላይ ስለነበር ከሌሎቹ ጋር አልነበረም።

በነሐሴ ወር ዳቦ ሊገዛ በወጣበት ጭንቅላቱ ላይ በጥይት ተመትቷል፤ ስለታማ ነገርም ታችኛውን ሰውነቱን ክፍል እንዳገኘው አጎቱ ተናግሯል።

የእስራኤል ባለስልጣናት ጉዳዩ ወዲህ ነው ይላሉ። ታዳጊው አል-ዛጋል በአቅራቢያው በሚገኝ የሰፈራ ጣቢያ ላይ የቤንዚን ቦምብ ለመጣል ሞክሯል ሲሉ ይከሳሉ።

የአል-ዛጋል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እያደረገ በመሆኑ ጉዳዩ እሱ በሌለበት ነው የታየው።

እሑድ ከእግሩ ላይ የተገጠመውን የኤሌክትሮኒክ አምባር ሲያወልቅ ታይቷል።

እንዳለፉት ቀናት ሁሉ እስረኞቹን ለመቀበል በርካታ የዌስት ባንክ ነዋሪዎች ወደ ጎዳናዎች ወጥቷል።

ከተለቀቁት መካከል የተወሰኑት በሰዎች ትከሻ ላይ ሆነው ሲዘዋወሩ ነበር። ህዝቡ ደግሞ የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልብ ታይቷል።

እስራኤል ከሐማስ ጋር በተደረሰው ውል መሠረት ሊፈቱ የሚችሉ 300 የፍልስጤም እስረኞችን ይፋ አድርጋለች። አብዛኛዎቹ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊ ወንዶች ናቸው።

በኳታር አደራዳሪነት ከስምምነት በተደረሰው መሠረት ለአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታ ተደርጓል። በእነዚህ ቀናት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 50 የእስራኤል ታጋቾች በሐማስ ይለቀቃሉ። እስራኤል ደግሞ በልውውጡ 150 ህጻናት እና ሴቶች የፍልስጤም እስረኞች እንዲፈቱ ተወስኗል።

እስካሁን 40 እስራኤላዊያን ታጋቾች እና 18 የውጭ አገር ዜጎች ተፈተዋል።

ቢያንስ 10 እስራኤላውያን በየቀኑ የሚለቀቁ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊራዘም እንደሚችል ቴል አቪቭ ቀደም ብላ አስታውቃለች። አሁንም ቢሆን የኔታንያሁ መንግስት ሐማስን ጠራርጎ ለማጥፋት እየዛተ ያለ ሲሆን ማንኛውም የተኩስ አቁምም ጊዜያዊ ብቻ ነው ብሏል።

ሐማስ በበኩሉ በትናንትናው ዕለት እንዳስታወቀው የተኩስ አቁም ፋታውን ለማራዘም እና የሚለቀቁትን ታጋቾች ቁጥር ለመጨመር ይፈልጋል።

በኳታር የተካሄደውን ድርድር በቅርበት የሚያውቁ አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ቡድኑ ለአሸማጋዮቹ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከሁለት እስከ አራት ቀናት ለማራዘም ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል። ስምምነቱ ከተራዘመ ተጨማሪ ከ 20 እስከ 40 እስራኤላውያን እንደሚለቀቁ ገልጸዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የስምምነቱን ማዕቀፍ “የተባረከ” ሲሉ ገልጸውታል። ስምምነቱ ሊራዘም እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱራህማን ለፋይናንሺያል ታይምስ እንደተናገሩት ሐማስ ስምምነቱ ለማራዘም በጋዛ ውስጥ በሌሎች ቡድኖች የተያዙ በደርዘን የሚቆጠሩ ታጋቾችን ማግኘት ይኖርበታል።

በመስከረም 26ቱ ጥቃት ከታገቱት ወደ 240 የሚጠጉ ሰዎች አብዛኛዎቹ በሐማስ የተያዙ ናቸው።

የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖችም ጥቂት ታጋቾችን ይዘዋል ተብሎ ይታመናል።

እንደ እስራኤል ከሆነ በመስከረም 26ቱ ጥቃት አብዛኛዎቹ እስራኤላዊያን የሆኑ አንድ ሺህ 200 ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል በወሰደችው የበቀል እርምጃ ጋዛ ላይ ያለ ማባራት ቦምብ በመጣል መሰረተ ልማቷን አውድማለች።

በርካታ ህጻናትን ጨምሮ ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል ሲል ሐማስ አስታውቋል። በተለይም ምግብ፣ ውሃ እና የንጽህና መጠበቂያዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የእርዳታ አቅርቦት ያስፈልጋል።