በቲክቶክ ከወንድ ጋር ሲደንስ መታየቱ ሕይወቱን ሊያሳጣው የነበረው ኢትዮጵያዊ

የቀስተ ደመና ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ በአንድ ፓርቲ ላይ ሁለት ወጣት ወንዶች አብረው ሲደንሱ የሚያሳይ ቪዲዮ በቲክቶክ ላይ ወጣ።

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውግዘቶች፣ ጥላቻዎች መጉረፍ ብቻ ሳይሆን በቪዲዮው ላይ ከወንድ ጋር ሲደንስ የሚታየው ወጣትም አገሪቱን ጥሎ ለመውጣት ተገዷል።

ሁለቱ ወንዶች በሚደንሱበት ወቅት እንደሚቀረጹ አላወቁም ነበር። ቪዲዮው መጀመሪያ ላይ የወጣው ኢንስታግራም ላይ ነበር። ቪዲዮው በቲክቶክ ከፍተኛ እይታን እንዳገኘ ተደርጎ ነበር የተለጠፈው።

“የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቴን በይፋ ማሳወቅ አልፈልግም ነበር። ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያ ተጎትቼ ማንነቴን እንዳወጣ ተደረግኩኝ” ሲል ቢቢሲ ማንነቱን ለመጠበቅ ሲል ስሙን በመቀየር አርኖልድ ሲል የሚጠራው ወጣት ተናግሯል።

“በአሁኑ ወቅት ማን እንደሆንኩኝ እንዲሁም የፍቅር ማንነቴም ይታወቃል” ይላል የ20 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ተማሪ።

የተመሳሳይ ጾታ ግንኑነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ-ወጥ ሲሆን ከ10 ቀናት እስከ ሶስት ዓመታት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።

አርኖልድ እንደሚናገረው ከጾታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ወይም ማንነትን አስመልክቶ በግልጽ መናገር አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ነው። ለዚህም በርካቶች ከሕግ በላይ በመሆን የቀጪነት ሚና በመውሰዳቸው ነው።

ዳንሱ ሕይወቱን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብሎ ጨርሶ አስቦት አያውቅም። ግጥም፣ ሙዚቃ እና እደ ጥበቦችን በያዘ አንድ ዝግጅት ላይ፤ “እየጠጣን፣ እየተዝናናን። ነጻ ሆነን ራሳችንን ሆነን ነበር” ይላል።

ያችን ምሽት የሚያሳይ ቪዲዮም ከሁለት ቀናት በኋላ በኢንተርኔት ላይ ወጣ። በመጀመሪያ ቪዲዮውን የለጠፈው ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ ባለስገባ ግለሰብ ነበር።

“በርካቶችም በቲክ ቶክ ላይ አዩት፤ እና በጣም ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ገባሁ” ይላል።

ፍርሃቱ በባዶ አልነበረም ከጥቂት ቀናት በኋላም በምሳ ዕረፍት ላይ እያለ ጥቃት ደረሰበት።

“ከሬስቶራንት ሰወጣ ሰብሰብ ያሉ ወንዶች ወደ እኔ መጡ እና በቪዲዮው ላይ እንዳዩኝ ነገሩኝ። የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ነህ አሉኝ”

“12 ያህል ወንዶች ከበውኝ ነበር። ሁለቱ ይደበድቡኝ ጀመር። እንደምንም አምልጬ መሮጥ ብችልም ያዙኝ እና ፊቴን ረገጡት። የጉንጭ አጥንቴንም ሰበሩት” በማለት የደረሰበትንም ይናገራል።

ሁኔታው በጊዜ ሂደት ይረጋጋል የሚል ተስፋ ነበረው። ነገር ግን ሐምሌ ወር ላይ ሌላ የቲክ ቶክ ቪዲዮ ተለጠፈ። ይህም ቪዲዮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን አገኘ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቪዲዮው ላይ አርኖልድን ጨምሮ በፓርቲው ታዳሚ የነበሩ ግለሰቦች ይታያሉ። ቪዲዮ “እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት የሚኖሩ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ናቸው” የሚል መግለጫም ይዟል።

መቼም ቢሆን ሊበርድ የማይችል እሳት እንደተለኮሰ ተሰማው። “ሁሉ ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። ስሜንና አድራሻዬን ለማወቅም ጥረት እያደረጉ ነበር” ይላል።

“በማህበራዊ ሚዲያዎችም ዜናዬ ናኘ። ከቤት ወጥቼ ሸሸሁ። በሕይወቴ ውስጥ በጣም አስፈሪ ቀናት ነበሩ። ካገኙኝ እንደሚገድሉኝ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበርኩ” ሲልም የነበረበትን ሁኔታ ያስታውሳል።

ከአንድ ወር በኋላ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የተመሳሳይ ጾታ ድርጊቶች ይፈጸምባቸዋል ባላቸው ሆቴሎች እና መጠጥ ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በተጨማሪም “አጸያፊ ድርጊቶች” ሲል የጠራቸውን ድርጊት የሚፈጽሙት ማህበረሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አቀረበ።

አርኖልድ በጓደኛው ቤት ለጥቂት ጊዜ ከተደበቀ በኋላ በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ የሚሰሩ እና መኖሪያቸውን በአውሮፓ ያደረጉ አምስት ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኞች ቡድን ጋር ተገናኘ።

ሃውስ ኦፍ ጉራማይሌ በመባል የሚታወቀው እንቅስቃሴ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ደኅንነታቸው እና መብታቸው እንዲጠበቅ የሚሰራ ሲሆን አርኖልድ ከኢትዮጵያ ወጥቶ ወደ ሌላ አገር የሚጓዝበትን ገንዘብም ሆነ መንገድ አመቻችተውለታል።

የእነዚህ በጎ ፈቃደኞች ቡድንም የቲክ ቶክ ቪዲዮዎች በርካቶች ላይ ጥቃት እና እንግልት በማድረስ እንዲሁም የግል መረጃቸውን ይፋ በማውጣት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥሉም ከተመለከቱት መካከል የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

የሃውስ ኦፍ ጉራማይሌ አንደኛው መስራች የሆኑት ፋሪስ ኩቺ ገዛኸኝ እነርሱ (ዘይ) በሚል ተውላጠ ስም ነው የሚጠሩት። በርካታ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ማንነት በማህበራዊ ሚዲያዎች ይፋ መሆን የበርካታ አፍሪካውያን እውነታ ነው ይላሉ።

“ለእኛ ማንነታችን ይፋ መሆን ብዙ ጊዜ የምርጫ ጉዳይ አይደለም” ይላሉ በኦስትሪያዋ ቪየና የሚኖሩት ፋሪስ።

ፋሪስ ወደ ኦስትሪያ የመሰደዳቸው ምክንያት የሆነው ለተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መብቶች መሟገታቸው ነበር።

ተሟጋቹ አርኖርልድን ሕይወቱን ስጋት ውስጥ የጣለውን ጨምሮ 110 የሚሆኑ በአሁኑ ወቅት የተሰረዙ የቲክቶክ ቪዲዮዎችን ሰብስበዋል።

አንዳንዶቹ በአደባባይ ሲደበደቡ፣ ሲረገጡ እንዲሁም በቡጢ ሲመቱ ያሳያል። ሌሎቹ ደግሞ ስማቸውን እና አድራሻቸውን የሚጠይቁ አስተያየቶችን የያዙ ቪዲዮዎችም ተካትተውበታል።

በአንደኛው ደግሞ ታዋቂ የኢቫንጀሊካል ክርስቲያን ፓስተር የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች እርቃናቸውን ተደርገው በአደባባይ እንዲገረፉም ጥሪ አቅርቧል።

ስልክ እያየ ያለ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እነዚህ ቪዲዮዎች ከመሰረዛቸው በፊት ለሳምንታት በቲክቶክ ላይ ቆይተዋል። በእነዚህ ጊዜያትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች አይተዋቸዋል።

“አብዛኛዎቹ እነዚህ ቪዲዮዎች የሚዘጋጁበት ቋንቋ በአብዛኛው በአማርኛ አንዳንዴም በኦሮምኛ እና ትግርኛ ነው” በማለት ፋሪስ ቪዲዮዎቹ ይዘታቸውን ለማወቅ እንዲሁም ለመሰረዝ ጊዜ የፈጀበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ሃውስ ኦፍ ጉራማይሌ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ እና በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ጥቃት እንዲፈጸሙ የሚያበረታቱ ቪዲዮዎችን ለማስወገድ ከማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ጋር እየሰራ ነው።

ቲክ ቶክ ይህንን አስመልክቶ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ በቀጥታ ለመመለስ ፈቃደኛ ባይሆንም የማህበረሰብ መመሪያውን እንዲመለከት ቢቢሲን ጠይቋል።

“ፖሊሲዎቻችን እና ተግባሮቻችን ሁሉንም በእኩል በሚያይ መልኩ እና ፍትሐዊ መሆናቸውን እንከታተላለን። ለዚህም ነው አዳዲስ ፖሊሲዎች በሚወጡበት ጊዜ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምክር እንጠይቃለን። እንዲሁም ያሉትን ፖሊሲዎችን በማሻሻል እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን ማዕከል አድርገን ደኅንነታቸው የሚያስጠብቁ ሁኔታዎችን ተግባራዊ እናደርጋለን” ብሏል።

እነዚህ በቲክቶክ ቪዲዮዎች ላይ የሚታዩ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ላይ ጥቃቶች እንዲበረታቱ የሚጠይቁ ይዘቶች በኢትዮጵያ ብቻ የተገደቡ አይደሉም።

ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ እንዲቀየር ቢቢሲን የጠየቀችው ኡጋንዳዊቷ ሴይላ ተመሳሳይ ተሞክሮዎች እንዳጋጠሟት ትናገራለች።

በኡጋንዳ ለአስርት ዓመታት ያህል የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሕገ-ወጥ ወጥ ሆኖ ቢቆይም በቅርቡ ግን መንግሥት ጠበቅ ያሉ ተጨማሪ ሕጎችን አጽድቋል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ድርጊቶችን ፈጽሟል ተብሎ የተከሰሰ ግለሰብ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲሁም እስከ ሞት በሚደርስ ቅጣት ሊቀጣ ይችላል። ከፋ ያሉት ቅጣቶች ተፈጻሚ የሚሆኑት እድሜያቸው ለወሲብ ካልደረሰ ወይንም ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ጋር የተመሳሳይ ጾታ የወሲብ ድርጊት በሚፈጽሙ ላይ ነው።

በመዲናዋ ካምፓላ መኖሪያዋን ያደረገችው ሴይላ ጎረቤቷ ለጸጥታ አካላት ሪፖርት ማድረጋቸውን ተከትሎ እሷና የሴት ጓደኛዋ እንደታሰሩ ትናገራለች።

“ፖሊሶቹ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች መሆናችሁን ካወቅን ለ20 ዓመታት ትታሰራላችሁ አሉን” ትላለለች።

ሆኖም ጥንዶቹ በእስር ሁለት ቀናትን ካሳለፉ በኋላ ተፈቱ። ፖሊስ ጥንዶቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን አደንዛዥ ዕፅ በመያዝ ጠርጥሬያቸው ነው በሚል ነው ሰነዱ ላይ ያሰፈረው።

“የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ስለመሆኔ ምንም ማስረጃ ስላልነበራቸው ሲለቁኝ ፋይሌ ላይ ያስቀመጡት አደንዛዥ ዕጽ በሚል ነው” በማለት ታስረዳለች።

ኡጋንዳዊት ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP

መታሰራውንም ተከትሎ በቲክቶክ ታዋቂ የሆኑት እነዚህ ጥንዶች ማስፈራሪያ እና ዛቻዎችን ማስተናገድ ጀመሩ። ለሕይወታቸውም ሰግተው መጋቢት ወር ላይ ወደ ኬንያ ተሰደዱ።

በዋነኝነት የቪዲዮ ማጋሪያ የሆነው የቲክቶክ ማሕበራዊ ድረ-ገጽ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተወዳጅነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የሚለጠፉ ይዘቶችን መቆጣጠር ወይም በተወሰነ መልኩ እንዲታገድም ጥሪዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።

ከቅርብ ወራት በፊት ሴኔጋል እና ሶማሊያ ቲክቶክን የሚያግድ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

በሴኔጋል ቲክቶክ ለመታገዱ ዋነኛው ምክንያት ፖለቲካዊ ነበር። ይህም የአገሪቱ ተቃዋሚዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ለማደራጀት እየተጠቀሙባቸው ነው በሚል ነው።

በሶማሊያ ደግሞ ቲክቶክ በአሸባሪዎች እንዲሁም “ኢሞራላዊ እና ነውር የሆኑ ይዘቶችን” የሚያስተላልፉ ቡድኖች ዋነኛ መድረክ ሆኗል ሲሉም ነው ባለስልጣናቱ ያገዱት።

በኬንያ ደግሞ አንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ነጋዴ የቲክቶክ አንዳንድ ይዘቶች “ለአገሪቱ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ እሴቶች ከባድ አደጋ” መደቀኑን በመጥቀስ የፖርላማ አባላቱ ማህበራዊ ገጹ ላይ እግድ እንዲያስተላልፉም ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ማሕበራዊ ገጹን ከማገድ ይልቅ የቁጥጥር ማዕቀፎች እንዲተገበሩ የሚሉ ውይይቶች መነሻ ሆኗል።

በቅርቡም የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሾው ዚ ጋር በተወያዩበትም ወቅት የተለያዩ ገደቦችን ለማበጀት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

“ተገቢ ያልሆኑ እና አጸያፊ ይዘቶች ይወገዳሉ” ሲልም የፕሬዝዳንት ሩቶ ጽህፈ ቤት ከስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ምንም እንኳን በቲክቶክ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች በርካታ ጥቃቶችን ቢያስተናግዱም ተጎጂዎች ግን ሙሉ በሙሉ ይታገድ በሚለው ላይ አይስማሙም።

“በርካታ ችግሮች ያጋጥሙናል ነገር ግን ስለ ማንነታችን ለሌሎች ለማስተማር ጥሩ መድረክ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤ ማንንም መጉዳት አንፈልግም” ስትል ሴሊያ ታስረዳለች።

“ሰዎች ነን” ትላለች።

አንድ ቀን ወደ አገር ቤት እመለሳለሁ የሚለውን ተስፋ የሰነቀው ኢትዮጵያዊው ወጣትም ቲክቶክ ሙሉ በሙሉ ይታገድ በሚለው አይስማም።

“የስነ ልቦና እና ሰብዓዊ መብቶችን ማጥናት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ማህበረሰቤን እንድረዳ ያነሳሳኛል” ሲልም ያስረዳል።

“እኔ ባለፍኩበት መከራ እንዲያልፍ ለማንም አልመኘውም” ሲልም ሃሳቡን አጠቃልሏል።