ፖፕ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ቡራኬ ልትሰጥ እንደምትችል ጠቆሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶችን ልትባርክ እንደምትችል ጠቆሙ።
ፖፑ ይህንን የተናገሩት ከቤተክርስቲያኗ አባቶች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ምላሽ በተጠየቁበት ወቅት ነው።
ፖፕ ፍራንሲስ ማንኛውም የቡራኬ ጥያቄ “በበጎ አድራጎት” ተግባር መታየት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የቤተክርስቲያኗ ካህናት ለማንኛውም ማኅበረሰብ አገልግሎት ከመስጠት ጋር የተያያዘ ከመሆኑም ጋር ተገልጿል።
“እኛ የምንክድ፣ የምናገል እና የማንቀበል ዳኞች ብቻ መሆን የለብንም” ብለዋል።
ሆኖም ቤተክርስቲያኗ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነቶችን እንደ ሐጢአት እንደምታይ እና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን እንደማትቀበል ተናግረዋል።
የማብራሪያ ጥያቄው በመጪው ረቡዕ በቫቲካን የሚካሄደው እና ለሳምንታት በሚቆየው የቤተክርስቲያኗ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚመክረው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ለፖፑ ከተላኩት አንዱ ነው።
በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ቡራኬ ማለት ካህናት ወይም አገልጋዮች ለአምላክ የሚያቀርቡት ጸሎት ወይም ልመና ነው። የእምነቱ አባቶች ቡራኬ የሚሰጧቸውን ሰዎች አምላክ በበጎ እንዲያመለከታቸው ይጠይቃሉ።
ቤልጂየም እና ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ጳጳሳት ካህናቱ ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ቡራኬ እንዲሰጡ መፍቀድ ቢጀምሩም የቤተ ክርስቲያኗ ባለስልጣናት አቋም ግልጽ አይደለም።
ከሁለት ዓመት በፊት ተመሳሳይ የማብራሪያ ጥያቄ መጠየቁን ተከትሎ የቫቲካን የቀኖና ቢሮ ቡራኬ መስጠት እንዳይፈቀድ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከሰሞኑ ማብራሪያ ላስፈለገበት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም ቤተክርስቲያን ጋብቻን “በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚፈጸም፣ የተረጋጋ እና የማይፈርስ አንድነት” አድርጋ ነው የምታየው ብለዋል።
“ከዚህ ጋር የሚጋጭ ማንኛውንም ዓይነት ሥርዓት ማስወገድ አለባት” ሲሉም ተናግረዋል።
ሆኖም “ቡራኬ ሲጠየቅ ለአምላክ መማጸንን የሚጠይቅ እንዲሁም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ አምላክ እንዲያሟላላቸው ጸሎት ማድረግን” ነው ብለዋል።
የቡራኬ ሃሳብ ከጋብቻ ጋር በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም እንደማይገባ ጠቅሰው ቡራኬን መጠየቅ ልምድ ሊሆን እንደማይገባ ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያኗ ከሕዝቡ ጋር ያላትን ግንኙነት “በደግነት፣ በትዕግስት፣ በማስተዋል፣ በመተሳሰብ እና በማበረታታት" በተመሰረተ ልታየው ይገባል ብለዋል።
በየካቲት ወር የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች የበረከት ጸሎቶችን ለመፍቀድ የቀረበውን ሀሳብ ደግፈዋል።












