በቱኒዝያ በሺዎች የሚቆጠሩ የተፎካካሪ የፓርቲ አባላት ፕሬዚዳንት ሳዒድን ለመቃወም አደባባይ ወጡ

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በቱኒዚያ ዋና ከተማ ጎዳናዎች ላይ የሃገሪቱን ፕሬዚዳንት ለመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።

እርስ በእርስ ጭምር የሚቃረኑ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የተቃውሞ ሰልፎቹን በመዲናዋ ቱኒዝ አካሂደዋል።

የተቀናቃኝ ፓርቲዎቹ ከ2011 ህዝባዊ አመጽ በኋላ የተገኘውን ዲሞክራሲያዊ ጉዞ እየቀለበሱ ነው ያሏቸውን ካይስ ሰኢድን "አምባገነን" ሲሉ አውግዘዋል።

የምግብ እና የነዳጅ እጥረት ለፈጠረው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስም ተጠያቂነት አለባቸው ብለዋል።

የፕሬዝዳንት ሰኢድ ተቺዎች መፈንቅለ መንግሥት ከማድረግ ባለፈ ቱኒዚያን ወደ በአንድ ሰው የሚመራ ፍጹም አምባገነናዊነት ለመመለስ ሞክረዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ጠቅላይ ሚኒስትሩን አሰናብተው ፓርላማውን ካገዱ በኋላ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ፕሬዝዳንቱ የአንድ ሰው አገዛዛቸውን የሚያፀድቀውን ህገ-መንግስት እንዲያልፍ ቢሞክሩም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምጽ ውድቅ ተደርጓል።

አዲሱ ህገ መንግስት በአውሮፓውያኑ 2011 ከተካሄደው የአረብ አብዮት በኋላ የተረቀቀውንና የቱኒዚያ የቀድሞ አምባገነን መሪውን ዚነ አል-አቢዲን ቤን አሊን ከስልጣን ያስወገደውን ተክቷል።

ይህ የሃገሪቱ መሪ ሙሉ የሥራ አስፈጻሚውን እንዲቆጣጠር፣ የሠራዊቱ የበላይ አዛዥ እንዲሆን እና ያለ ፓርላማው እውቅና መንግስትን የመሾም አቅም ሰጥቷቸዋል።

ፕሬዚዳንት ሰኢድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውድቀትን ለመስበር አስፈላጊ ነበር ብለው ይሞግታሉ።

ማሻሻያዎቹም የ2011 አብዮትን መንፈስ ያማከሉ እና ወደፊትም የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ደጋፊዎቹ ውሳኔውን በደስታ ተቀብለዋል። ሃገሪቱ ብልሹ አሠራርን እና ሙስናን ለመቅረፍ ጠንካራ መሪ ትፈልጋለች በማለት ነው የሚደግፉት።

ቅዳሜ ዕለት በማእከላዊ ቱኒዝ ሰልፈኞች “ውረድ፣ ውረድ” ሲሉ ተደምጠዋል።

የተቃውሞ ሰልፉን ከጠሩት መካከል አንዱ የሆነው ናሽናል ሳልቬሽን ፎሮንት የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት የቱኒዚያን ፓርላማ ከፍተኛ ወንበር የያዘውን ኤናህዳን የያዘ ነው። ​​ሰኢድ ፓርላማውን በኋላ ላይ በትነዋል። 

የቱኒዚያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኤናሃዳ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አሊ ላራይድ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ሰልፉ “በካይስ ሰኢድ የስልጣን ዘመን ላይ ያለው ቁጣ” የሚያሳይ ነው።

“ስልጣን እንዲለቁ እየነገርናቸው ነው።“

አክለውም ተስፋ መቁረጥ፣ ድህነት እና ሥራ አጥነት እያደገ መሆኑን ጠቅሰው ሰኢድ በስልጣን ላይ ከቆዩ "ቱኒዚያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አይኖራትም” ብለዋል።

ናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንትስልጣኑ የተገደበ አዲስ አዲስ ፓርላማ ለመምረጥ በታህሳስ ወር በሚካሄደው ምርጫ እንደማይሳተፍ አስታውቋል።

የኢናሃዳ ርዕዮተ ዓለም ጋር ተቀናቃኝ የሆነው የፍሪ ዴስቶሪያን ፓርቲም በተመሳሳይ ቅዳሜ በዋና ከተማዋ የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጅቷል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች በመስከረም ወር 9.1 በመቶ የደረሰውን የዋጋ ግሽበት ምክንያት የውሃ ወጪን መጨመሩን ለማስመልከት ባዶ ጀሪካኖችን ይዘው ነበር።

በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ጡረተኛው ሰኢድ “ምንም እየሠራ አይደለም፣ ነገሮችም እየባሱ ነው” ብለዋል።

በኤንናዳ የሚመራውን ሰላማዊ ሰልፍ ወደ 1 ሺህ 500 የሚጠጉ ሰዎች የተቀላቀሉ ሲሆን ወደ 1 ሺህ 000 የሚጠጉት ደግሞ በፒዲኤል ተቃውሞ ላይ ተገኝተዋል ሲል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኤኤፍፒተናግሯል።

በአውሮፓውያኑ 2011 የተካሄደው የቱኒዚያ አብዮት ከአረብ አብዮት ብቸኛው እና ስኬታማው እንደሆነ ቢነገርም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋትን አላመጣም።