ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአሜሪካ የ9/11 ሽብር ጥቃት ተከሳሾች መካከል አንዱ ለፍርድ ለመቅረብ ብቁ አይደለም ሲል ፍርድ ቤት በየነ
ከ22 ዓመት በፊት በአሜሪካ ከተፈጸመው የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ክስ ከተመሰረተባቸው አምስት ተከሳሾች መካከል አንደኛው ለፍትህ ለመቅረብ ብቁ አይደለም ሲል በጓንታናሞ ቤይ በሚገኝ የጦር ፍርድ ቤት በይኗል።
ተከሳሹ ራመዚ ቢን አል ሺቢህ በተደረገለት የጤና ምርመራ ከአስቃቂ አጋጣሚዎች በኋላ የሚመጣ የአእምሮ ጤና መታወክ እንደገጠመው ተነግሯል።
የተከሳሹ ጠበቃ ደንበኛዬ በሲ አይ ኤ ተሰቃይቷል ሲል ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ተከሳሹ ትላንት አርብ ችሎት እንዲቀርብ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር።
በኩባ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር በተደረገ ቸሎት ዳኛው ኮሎኔል ማቲው ማኮል ከአንድ ወር በፊት ተከሳሹ አልሺብ ራሱን ለመከላከል በሚችልበት የጤና ሁኔታ እንዳልነበር አስታውሰው የህክምና ባለሙያዎች ያቀረቡትን ውጤት ተቀብለዋል።
ኒውዩርክ ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ ተከሳሹ የአእምሮ ጤና መታወክ እንደገጠመው የሐኪሞች ቦርድ ድምድሟል።
በዚህም ሳቢያ አል ሺቢህ ችሎት ለመቅረብ አልያም የጥፋተኝነት ውሳኔን ለመቀበል ብቁ እንዳይሆን አድርጎታል ሲል ፍርድ ቤት በይኗል።
ተከሳሹ ያለበት የአእምሮ ጤና ሁኔታ “የችሎቱን ሂደት እንዳይረዳ ወይም በሂደቱ በፍላጎት ተባባሪ እንዳይሆን አድርጎታል” ሲል የወታደራዊ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ሪፖርት አመላክቷል።
ይህ ተከሳሽ ትላንት አርብ የ9/11 ጥቃት ዋነኛ አቀነባባሪ እንደሆነ የሚታመነውን ካሊድ ሼክ ሞሃመድን ጨምሮ ከሌሎች አራት ተከሳሾች ጋር ትላንት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቅ ነበር።
ሆኖም ችሎቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ኮሎኔል ማቲው ማኮል አልሻቢህን ከክሱ ውጪ አድርገውታል።
የሌሎቹ ተከሳሾች ችሎት ግን በመርሃ ግብሩ መሰረት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
አምስቱ ተከሳሾች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2001 በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ፣ በአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታገን፣ እና በፔንስልቬንያ በተጠለፈ አውሮፕላን ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች የተገደሉበት የሽብር ጥቃት እንዲፈጸም አሲረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
አሁን በአእምሮ የጤና መታወክ ምክንያት ከፍርድ ሂደት ውጪ የሆነው የ51 ዓመቱ የመናዊ አልሺብህ እንደ አውሮፓውያኑ በ2002 ነበር በፓኪስታን በቁጥጥር ስር የዋለው።
ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ ለጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ተላልፎ ተሰጥቷል።
የተከሳሹ ጠበቃ ደንበኛው በሲ አይ ኤ ስቃይ እንደደረሰበት ተናግሯል።
“ኤጀንሲው የምርመራ ቴክኒክ እያለ በሚጠራው ተግባር” ደንበኛውን እንቅልፍ ማሳጣት፣ በውሃ መድፈቅና መደብደብን ጨምሮ የተለያዩ እንግልቶችን አድርሶበታል ብሏል።
የተከሳሹ የአእምሮ ጤና ጉዳይ ከአውሮፓውያኑ 2008 የመጀመሪያው የችሎት ውሎው ጀምሮ መነጋገሪያ እንደነበር ነው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት።
አልሺሃይብ በጀርመን ሃምቡርግ የሚገኝ የአልቃይዳ ህዋስን በመርዳት በኒውዮርክ ‘ዎርልድ ትሬድ ሴንተር’ በተሰኘው መንታ ህንጻ ላይ የተከሰከው አውርፕላን እንዲጠለፍ አድርጓል የሚል ክስ ነበር የቀረበበት።
በኩባ የአሜሪካ ባህር ሃይል ወታደራዊ ሰፈር የሚገኘው ጓንታናሞ የ9/11 ጥቃት ከደረሰ በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ 2002 በወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የውጪ ሀገራት ዜግነት ያላቸው የሽብር ተጠርጣሪዎች እንዲታሰሩበት ነበር የተቋቋመው።
የጓንታናሞ ካምፕ መቋቋም የቡሽ አስተዳደር ‘በሽብር ላይ የከፈተውን ጦርነት’ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ሆኖም በዚሁ ስም በጓንታናሞ እስረኞች ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል፤ ያለ ፍርድም ለረጅም ጊዜ ይቆያሉ የሚል ትችትም ይሰነዘራል።