ከአርሰናል እና ከዩናይትድ ማን ያሸንፋል? - የክሪስ ሱቶን ግምት

አርሰናል በያዝነው የውድድር ዘመን ብቸኛውን ሽንፈት የቀመሰው በኦልድ ትራፈርድ ሜዳ በማንቸስተር ዩናይትድ ነው። እነሆ ሁለቱ ቡድኖች ድጋሚ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል። ማን ድል ይቀናው ይሆን?

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱቶን የዚህን ግጥሚያ እና የሌሎች የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምቶችን እንዲህ አስቀምጧል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በኤሪክ ቴን ሃግ አሠልጣኝነት ዘመን ነገሮች እየቀኗቸው ይመስላል።

የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያዎቹን ጨዋታዎች ተሸንፈው ቢጀምሩም በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በተከታታይ ፍልሚያዎችን በድል በመወጣት ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

ሱቶን ትላንት ሐሙስ የተካሄደውን ማንቸስተር ሲቲ እና የቶተንሃም ጨዋታን ገምቶ ነበር። ሱቶን ሲቲ 3 ለ 1 ያሸንፋል ሲል ነበር የገመተው። ሲቲ ጨዋታውን 4-2 አሸንፏል።

እሑድ

የእግር ኳስ ተንታኙ ሱቶን ሊድስ ከብሬንትፈርድ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጎል ይንበሸበሻል ሲል፣ ውጤቱ ደግሞ 2 ለ 2 ነው ይሆናል የሚል ትንበያ አስቀምጧል።

ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ያጠበቡት ሲቲዎች እሑድ አመሻሹን ከዎልቭስ ይጫወታሉ።

ሱቶን ሲቲ ፍልሚያውን 2 ለ 0 እንደሚረታ አልጠራጠራም ሲል ገምቷል።

የዚህ ሳምንት ተጠባቂው ጨዋታ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው አርሰናል ከማንቸስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ግጥሚያ ነው።

መልካም አቋም ላይ የሚገኙት ራሽፈርድ፣ ፈርናንዴዝ እና ኤሪክሰን በዚህ ጨዋታ ጎልተው ሊወጡ እንደሚችሉ ሱቶን ይገምታል።

ነገር ግን በተከታታይ የቢጫ ካርድ በማየቱ ምክንያት ከአርሰናል ጋር በሚኖረው ጨዋታ የማይሰለፈው ካዜሚሮ ለዩናይትድ ትልቅ ጉዳት እንደሆነ ያወሳል።

ምንም እንኳ ዩናይትዶች በዚህኛው የውድድር ዘመን ወደ ቀደመ አቋማቸው የተመለሱ ቢመስሉም፣ አርሰናል ግን ከፍ ያለ መነቃቃት ላይ እንዳለ ሱቶን ይናገራል።

ግምት፡ አርሰናል 3 - 1 ዩናይትድ

ሰኞ

ባለፈው እሑድ በአርሰናል 2 ለምንም የተረቱት ቶተንሃም ሆትስፐሮች ሐሙስ ምሽት ወደ ኤቲሃድ አቅንተው 4 ለ 2 ተሸንፈው ተመልሰዋል።

ቶተንሃም ሰኞ ምሽት ወደ ፉልሃም ተጉዘው ወደ ድል ለመመለስ ሙከራ ያደርጋሉ።

ነገር ግን የፉልሃም ጨዋታ ለስፐርስ ቀላል እንደማይሆን ሱቶን ይተነትናል።

ሱቶን እንደሚገምተው ፉልሃም ጨዋታውን 2 ለ 1 አሸንፈው አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ላይ እየበረታ የመጣውን ጫና ያከሩታል።

ፉልሃምን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ከቶተንሃም ከፍ ብለው አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ይችላሉ።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን አርሰናል በ47 ነጥብ ይመራል። አንድ ተጨማሪ ጨዋታ የተጫወተው ሲቲ በ42 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ኒውካስል፣ ቶተንሃም እና ፉልሃም በተከታታይ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ቅዳሜ

ሊቨርፑል ከቼልሲ

ሁለቱም ክለቦች በያዝነው የውድድር ዘመን ደካማ ብቃት እያሳዩ ነው የሚለው ሱቶን፣ የዚህን ጨዋታ ውጤት መገመት እንደሚከብድ ይገልጻል።

ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት በብራይተን አራት ለምንም መረምረሙ ይታወሳል። ነገር ግን በኤፍ ኤ ዋንጫ ዎልቭስን በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሻግሯል።

ቼልሲዎችም ቢሆኑ የዘንድሮ አቋማቸው አስተማማኝ አይደለም የሚለው ሱቶን፣ ሁለቱም ቡድኖች ሦስት ነጥብ ማግኘት እንደናፈቃቸው ይናገራል።

ክሩስ ሱቶን በቅዳሜው ጨዋታ ቼልሲ እና ሊቨርፑል 1 ለ 1 በመሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተው ይወጣሉ ብሎ ተንብዮ የነበረ ሲሆን፣ በውጤቱም ትንበያው ብዙም ሳይርቅ ሁለቱቡድኖች ያለግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

በሌሎች የቅዳሜ ግጥሚያዎች ኖቲንግሃም ፎረስት በርንመዝን 1 ለ 0 ያሸንፋብሎ ነበር ነገር ግን 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።

ብራይተን ሌይስተርን 2 ለ 1 ይረታል ብሎ ሁለት አቻ ሆነዋል። ሳውዝሃምፕተን ከአስተን ቪላ 1 ለ 1 ይወጣሉ ቢልም አስቶን ቪላ 1 ለ 0 አሸንፏል።

በተመሳሳይ ክሪስታል ፓላስ ከኒውካስትል 1 ለ 1 ይለያያሉ ሲል ቢገምትም ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ሱቶን ዌስትሃም ከኤቨርተን የሚያደርጉት ግጥሚያ ያለምንም ግብ ይጠናቀቃል የሚል ግምቱን ቢያስቀምጥም ዌስትሃም 2 ለ 0 አሸናፊ ሆኗል።