ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ታላላቅ ሳይንቲስቶቿን እያሰረች በአገር ክህደት የምትከሰው ለምንድን ነው?
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አንድ በኩራት የሚናገሩለት ጉዳይ አያላቸው - ይህም የአገራቸውን ሃይፐርሶኒክ የተባለውን ሚሳኤል ከሌሎች ቀድማ መገንባቷ ነው። ይህ ሚሳኤል ከድምጽ ከአምስት እጥፍ በላይ በመጓዝ ቀዳሚ እንደሆነ ይነገርለታል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከዚህ ጀርባ ያሉ በርካታ የሩሲያ የፊዚክስ ሊቃውንት በአገር ክህደት ተከሰው እስር ቤት ታጉረዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግን ይህንን ከልክ ያለፈ እርምጃ ነው ይሉታል።
ከታሰሩት አብዛኞቹ በዕድሜ የገፉ ሲሆኑ፣ ሦስቱ ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። አንደኛው ከካንሰር ጋር ትግል ላይ ከነበሩበት የሆስፒታል አልጋ ተወስደው እስር ላይ ብዙም ሳይቆዩ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው።
የ68 ዓመቱ ምሁር ቭላዲላቭ ጋኪን ደግሞ በደቡባዊ ሩሲያ በቶምስክ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በፀጥታ ኃይሎች ተወረረ።
ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ጥቁር ጭንብል ያጠለቁት ታጣቂዎች ሊይዟቸው ሲመጡ ከቁም ሳጥናቸው ውስጥ ሳይንሳዊ ቀመሮችን የያዙ ወረቀቶችን በርብረው ይዘው መሄዳቸውን አንድ የምሁሩ ዘመድ ተናግረዋል።
የሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት ኤፍኤስቢ ስለምሁሩ እስር ሚስታቸው ታቲያናን ለማንም እንዳይናገሩ ስላስጠነቀቋቸው፣ ከአያታቸው [ጋልኪን] ጋር ቼዝ መጫወት ለሚያዘወትሩት የልጅ ልጆቻቸው ባለቤታቸው ለሥራ መጓዛቸውን ነው የነገሯቸው።
ከ2015 (እአአ) ጀምሮ 12 የፊዚክስ ሊቃውንት በሩሲያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ሁሉም ደግሞ ከሃይፐርሶኒክ ቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ወይም ቴክኖሎጂውን ከሚሠሩ ተቋማት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።
ሁሉም ደግሞ በከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል ተከሰዋል። ይህ ክስ ደግሞ የመንግሥት ምሥጢሮችን ለውጭ አገራት ማስተላለፍን ይጨምራል።
በሩሲያ የአገር ክህደት ክሶች የሚታዩት በዝግ ነው። በዚህ ምክንያት የክሳቸውን ጭብጥ በትክክል ማወቅ አዳጋች ነው።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት (ክሬምሊን) “ክሶቹ ከባድ በመሆናቸው” እና የአገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ስለሚሳተፍባቸው ተጨማሪ አስተያየት መስጠት አልችልም ብሏል።
ባልደረቦቻቸው እና የመከላከያ ጠበቆቻቸው ግን ሳይንቲስቶቹ በጦር መሳሪያ ግንባታ ውስጥ አልተሳተፉም ብለዋል። ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል የአንዳንዶቹ ጭብጥም ከውጭ አገራት ተመራማሪዎች ጋር በግልጽ መተባበር የሚሉ ናቸው ይላሉ።
ተቺዎች ግን የሩሲያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት (ኤፍኤስቢ) የውጭ ሰላዮች የጦር መሳሪያ ምሥጢሮችን ለማግኘት እየሞከሩ ነው የሚል ስሜት ለመፍጠር ይፈልጋል ብለዋል።
ሃይፐርሶኒክ የሚባሉት መሳሪያዎች በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዙ እና ከተተኮሱ በኋላ በጉዞ ላይ እያሉ አቅጣጫ በመቀያየር የአየር መከላከያዎችን ማምለጥ የሚችሉ ሚሳኤሎች ናቸው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ሁለት ዓይነት ሃይፐርሶኒኮችን እንደተጠቀመች ተናግራለች። የመጀመሪያው ከአውሮፕላን የሚተኮሰው ኪንዣል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዚርኮን ሚሳኤል ናቸው።
ኪየቭ አንዳንዶቹን የኪንዣል ሚሳኤሎችን መትታ መጣሏን መናገሯ በመሳሪያዎቿ ብቃት ላይ ጥያቄ አስነስቷል።
ሩሲያ የመሳሪያቀውን ግንባታ እና ጥቅም ላይ የማዋል ቴክኖሎጂው በአንድ በኩል ስታጧጡፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እስሩን ቀጥላበታለች።
ጋልኪን ከታሰሩ በኋላ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በርካታ ጥናቶችን አብረዋቸው የሠሩት ሌላኛው ሳይንቲስት ቫሌሪ ዝቬጊንሴቭም በተመሳሳይ ቀን ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።
መንግሥታዊው የዜና ወኪል ታስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ዝቬጊንሴቭ ለእስር የተዳረጉት በአውሮፓውያኑ 2021 በኢራን የጥናት መጽሔት ላይ ባወጡት ጽሑፍ ሊሆን ይችላል።
በመጽሔቱ ከታተመው እና ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን አውሮፕላኖች በሚመለከተው የጥናት ጽሑፍ ላይ የጋልኪን እና የዝቬጊንሴቭ ስም ተጠቅሷል።
ኤፍኤስቢ በ2022 ዝቬጊንሴቭ የሚሠሩበት ተቋም ዳይሬክተርን እና የድሞው በአየር ላይ በከፍተኛ ፍጥነት መጓዝን የሚመለከቱ ጥናቶች የሚደረጉበት ቤተሙከራ የቀድሞ ኃላፊ የሆኑትን ሁለት ባልደረቦቻቸውን አስሯል።
የቲዮሬቲካል እና አፕላይድ ሜካኒክስ ተቋም ሠራተኞች የታሰሩትን ሦስት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በመደገፍ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል።
አሁን ከኢንስቲትዩቱ ድረ-ገጽ በተነሳው በዚህ ደብዳቤ ላይ፤ የታሰሩት ሠራተኞች “በአስደናቂ ሳይንሳዊ ውጤቶች” የሚታወቁ እና “ምንጊዜም ለአገራቸው ጥቅም ታማኝ ሆነው የቀጠሉ” ሲሉ ባልደረቦቻቸው ገልጸዋቸዋል።
ለሕዝብ ይፋ ያደረጓቸውን ሥራዎቻቸውን በተመለከተም ምሥጢራዊ መረጃ ይዘው ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ በተቋሙ የባለሙያዎች ቡድን በተደጋጋሚ ተመርምረው ምንም ጥሰት አልተገኘባቸውም ብሏል።
የሩሲያ የሰብአዊ መብቶች እና የሕግ ድርጅት ጠበቃ የሆኑት የቭጌኒ ስሚርኖቭ “ሃይፐርሶኒክ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ለመወርወር ሰበብ ሆኖ እየቀረበ ያለ ርዕስ ነው” ብለዋል።
ስሚርኖቭ በሥራቸው ምክንያት የመንግሥት የበቀል እርምጃን በመሸሽ በ2021 ከሩሲያ ወደ ቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራግ አምረተው መኖር ከመጀመራቸው በፊት በአገር ክህደት የተከሰሱ ሳይንቲስቶችን እና ሌሎችንም ፍርድ ቤት ቆመው ተከላክለዋል።
በእስር ላይ ካሉት ሳይንቲስቶች መካከል አንዳቸውም የሚያካነውኑት ምርምር እና ሥራ ከመከላከያው ዘርፍ ጋር ምንም ግንኙነት እንዳልነበራቸው እና ያጠኑ የነበረው በከፍተኛ ፍጥነት ምክንያት ብረት እንዴት ቅርጹ ሊቀየር እንደሚችል ወይም የአየር ነውጥ ተጽእኖን መሆኑን ተናግረዋል።
“ይህ ደግሞ የሮኬት ግንባታ ሳይሆን ስለአካላዊ ሂደቶች ጥናት ነው” ብለዋል። ግኝቶቹንም የጦር መሳሪያ ገንቢዎች ኋላ ላይ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
የተመራማሪዎቹ እስር የጀመረው ከጥቂት ዓመታት በፊት በቭላድሚር ላፒጂን ነው። አሁን 83 ዓመት የሆነቻው ላፒጂን በአውሮፓውያኑ 2016 ታስረው ከአራት ዓመታት በኋላ በምህረት ተፈትተዋል።
እኚህ በእስር የቆዩት ግለሰብ ለ46 ዓመታት ያህል ለሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ዋና የምርምር ተቋም በሙያቸው አገልግለዋል።
ላፒጂን ለቻይናውያን በላኩት የኤሮዳይናሚክስ ቀመር ሶፍትዌር ምክንያት ነው ተከሰው የተፈረደባቸው። ተመራማሪው በተቋሙ በኩል ሙሉውን ሶፍትዌር ለመሸጥ ከተደረገው ንግግር ጋር በተያያዘ ማሳያውን ብቻ መላካቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን ያጋሩት መረጃ ምንም ዓይነት ምሥጢራዊ መረጃ እንዳልያዘ እና “ለማንም ክፍት በሆኑ ህትመቶች ላይ በተደጋጋሚ የቀረበ” ምሳሌ ብቻ ነው ብለዋል።
ላፒጂን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሃይፐርሶኒክስ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁሉ “ከጦር መሳሪያ ግንባታዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም።”
በሳይቤሪያ የሚገኘው ሌዘር ፊዚክስ ኢንስቲትዩት ሳይንቲስት የሆኑት ዲሚትሪ ኮልከር በእስር ላይ የሚገኙ ሌላ ምሑር ናቸው። እአአ በ2022 በከፍተኛ የጣፊያ ካንሰር ምክንያት ሆስፒታል እያሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
የተከሰሱት በቻይና ባደረጓቸውንሙያዊ ንግግሮች ላይ የተመሠረተ ነው ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። ነገር ግን ያቀረቡት ንግግር ይዘት በኤፍኤስቢ ይሁንታን ያገኘ እና አብሯቸውም የደኅንነት ተቋሙ ወኪል ተጉዞ ነበር።
ኮልከር በታሰሩ በሁለተኛው ቀን በ54 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በእስር ላይ የሚገኙት ሳይንቲስቶች ባልደረባ የሆኑ ግለሰብ “በአገሪቱ መንግሥት መዋቅር ውስጥ አለመግባባት አለ” ይላሉ።
ሳይንቲስቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጽሑፎችን ማሳተም እና ከውጭ አጋሮች ጋር መተባበር ይጠበቅባቸዋል፤ ነገር ግን “ኤፍኤስቢ ደግሞ ከውጭ ሳይንቲስቶች ጋር መገናኘት እና በውጭ አገራት ሙያዊ መጽሔቶች ላይ ሥራን ማሳተም ደግሞ እናት አገርን መክዳት ነው ብሎ ያስባል” ብለዋል።
የቲዮሬቲካል እና አፕላይድ ማቲማቲክስ ተቋም ሳይንቲስቶችም ተመሳሳይ ስሜት አላቸው። “ሥራችንን እንዴት እንደምንቀጥል አናውቅም” በማለት በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል።
"ዛሬ የተሸለምንበት ነገር . . . ነገ ለወንጀል ክስ ምክንያት ሆኖብናል።”
ሳይንቲስቶች በአንዳንድ የምርምር ዘርፎች ለመሳተፍ እንደሚፈሩ፤ ችሎታ ያላቸው ወጣት ሠራተኞችም ከሳይንሱ እየራቁ ነው ሲል አስታውቋል።
ይህ ደብዳቤ ያልተለመደ የሕዝባዊ ድጋፍ ምሳሌ ነበር። ሳይንቲስቶቻቸው የታሰሩባቸው ሌሎች ተቋማት ግን አስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።
በሌሎች ላይ የቀረቡት ክሶችም ከዓለም አቀፍ ትብብር ጋር የተያያዙ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል።
በጉዳዩ ላይ የሠሩት ጠበቃው ስሚርኖቭ እንደተናገሩት ከሆነ በሌሎች ሁለት ሳይንቲስቶች ላይ የተደረገው ምርመራ ሄክሳፍላይ ከተባለ የአውሮፓ ሃይፐርሶኒክ ሲቪል አውሮፕላን ለመገንባት ከሚሠራ ፕሮጀክት ጋር የተያያዘ ነው።
አሁን የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት በአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ የሚመራ እና በ2012 የተጀመረ ነበር።
ኤጀንሲው ለቢቢሲ እንደገለጸው በሩሲያ እና በአውሮፓ አካላት መካከል በተደረገው የትብብር ስምምነት መሠረት “ሁሉም ቴክኒካዊ አስተዋጽኦዎች እና የመረጃ ልውውጦች አስቀድመው ስምምነት የተደረገበት እና የሚታወቅ ነው” ብሏል።
ምንም እንኳን የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛው ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ ቢያዝም ባለፈው ዓመት በሁለቱም ሳይንቲስቶች ላይ የ12 ዓመት እስር ተፈርዶባአዋል።
የጠፈር ተሽከርካሪ በድጋሚ ወደ ምድር ከባቢ አየር ሲገባ ካለው የኤሮዳይናሚክስ ጥናት ጋር የተያያዙ ሌሎች እስሮችም ነበሩ።
ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ኅብረት በገንዘብ የሚደገፍ እና በቤልጂየሙ በቮን ካርማን የፍሉድ ዳይናሚክስ ተቋም የሚተዳደር ነበር።
የኤፍኤስቢ መርማሪዎች ከሳይንቲስቶች አንዱ ቪክቶር ኩድሪያቭሴቭ ወደ ቮን ካርማን ኢንስቲትዩት በላከው ምርምር ውስጥ የተተኳሽ አረር የሚመስለው ሾጣጣ ቅርጽ አሳስቧቸው እንደነበር ባለቤታቸው በሞት የተለይዋቸው ኦልጋ ገልጸዋል።
እአአ ከ2011 እስከ 2013 የዘለቀው መርሃ ግብር “ወታደራዊ ምርምርን እንደማያካትት በግልጽ አስቀምጧል” ብሏል ተቋሙ። በኩድሪያቭሴቭ ቡድን “ምሥጢራዊ መረጃን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ፍንጭ ማግኘት አልቻልኩም” ብሏል።
የሰብዓዊ መብትተሟጋች ቡድኖች ተመሳሳይ ነገር እየተደጋገመ መሆኑን ተመልክተዋል።
የኤፍኤስቢ መኮንኖች ከጠበቃው ስሚርኖቭ ጋር በግል ባደረጉት ውይይት ላይ እንዳረጋገጡላቸው የሃይፐርሶኒክ ምሥጢሮችን አሳልፎ የመስጠትን ጉዳዮች ያነሱት “የባለሥልጣናትን ፍላጎትን ለማርካት” መሆኑን ተናግረዋል።
የኤፍኤስቢ ሰላዮች የፑቲንን “ፍላጎት ለማሟላት” የውጭ አገር ሰላዮች የሩሲያን የሚሳኤል ምሥጢሮችን እያደኑ ነው የሚል ስሜት ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው ጠበቃው ያምናሉ።
ይህ ጉዳይ የተነሳው የአገር ክህደት ክሶች በስፋት እየተደመጡ ባሉበት ወቅት ነው።
የሩሲያ የፖለቲካ እስረኞችን የሚደግፍ ሥራን የሚመሩት ሰርጌይ ዴቪዲስ፣ በተለይ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ “የስለላ ስጋት እና የማግለል ከባቢ ተፈጥረሯል” ይላሉ።
ድርጅታቸው በሩሲያ እንዳይንቀሳቀስ ከታገደ በኋላ ከሊትዌኒያ ሆነው ሃሳበቸውን ያካፈሉት ዴቪዲስ፤ ኤፍኤስቢ እየሠራ መሆኑን ለማሳየት “የሪፖርት ማቅረቢያ ስታቲስቲክስ ጉዳዮችን እንደሚፈጥር” እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ነገር ግን በሳይንቲስቶች ላይ ከሚፈጸመው እስራት ጀርባ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናሉ። ለምሳሌ ለመንግሥት የጨረታ ውድድር ወይም በሃይፐርሶኒክስ ውስጥ በተሳተፉ ሁሉም ሳይንቲስቶች ላይ የክሬምሊን ደስተኛ ያለመሆን ሊሆን ይችላል።
ስሚርኖቭ አክለውም ኤፍኤስቢ አንዳንድ ጊዜ ተጠርጣሪዎች የቀረበባቸውን ክስ ካመኑ እና ሌሎች ላይ ከጠቆሙ ቀለል ያለ ያለ ቅጣት እንዲጣልባቸው ቃል ይገባል።
ኩድሪያሴቭ ጥፋተኛነታቸውን የሚቀበሉ እና ሌሎች ላይ የሚጠቁሙ ከሆነ ፍርዱ እንደሚቀልላቸው ተነግሯቸው እንደተበረ ባለቤታቸው ተናግረዋል።
ነገር ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከመታየቱ በፊት በ2021 በ77 ዓመታቸው በሳንባ ካንሰር ሕይወታቸው አለፈ።
ጡረተኛው የኤፍኤስቢ ጄኔራል አሌክሳንደር ሚኻይሎቭ እንደሚሉት ኤፍኤስቢ የወታደራዊ ቴክኖሎጂን “ምሥጢራዊነት ማረጋገጥ አለበት።”
ጨምረውም ከታዋቂው የአገሪቱ ተቋም ሦስት ሳይንቲስቶች መካከል ግንቦት ወር ላይ የ14 ዓመት እስር እንደተፈረደባቸውን አናቶሊ ማስሎቭ ዓይነት ከባድ ቅጣት ሲጣል “በማያጠራጥር ሁኔታ ጠንካራ መሠረት” ሊኖር ይገባል ብለዋል።
ጄኔራል ሚኻይሎቭ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በአገር ክህደት ክስ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ የነጻነት እና የዲሞክራሲ መስፋፋትን ተከትሎ ነው።
ይህም በሶቭየት ዘመን የነበረው የአስተሳሰብ እንዲለወጥ ምክንያት ሆኗል በማለት፣ በዚያ ዘመን የመንግሥት ምሥጢርን ሊያውቁ የሚችሉ ሰዎች “በጥንቃቄ የሚመረጡ” ሲሆን፣ እነሱም ምሥጢር ማውጣት “ምን ሊያስከትል እንደሚችል የተረዱ ናቸው” ይላሉ።
አክለውም “አንዳንድ ሰዎች በጣም ያወሩ እና መረጃዎችን ሲያወጡ ታይተዋል።”
ጋልኪን በተመለከተ፣ ጭምብል ለባሾቹ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ወኪሎች ከቤታቸው ከወሰዷቸው ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗል። የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት በብቸኝነት ታስረው ማሳለፋቸውን ዘመዳቸው ተናግረዋል።
ባለቤታቸው ታቲያና በመስታወት በተለየ ክፍል ውስጥ ሆነው በስልክ ሊያናግሯቸው እንደሚችሉ ተናግረው። “በየቀኑ እዚያ ስለሚቀመጥ” በቅርቡ እሳቸውም ለመታሰር ለመጠየቅም አስበው ነበር።
“በተመሳሳይ እዚያው እስር ቤት እንዲያስቀምጡኝ ልጠይቃቸው እችላለሁ። አንድን ሰው መጠርጠር ብቻ በቂ ስለሆነ፣ ይህ በጣም ቀላል ነው።”
ሩሲያ ውስጥ የታሰሩ ሌሎች ሳይንቲስቶች?
- አሌክሳንደር ሺፕሉክ፣ የቲዮረቲካል እና አፕላይድ ማቲማቲስ ተቋም ዳይሬክተር፣ በ2022 ተይዘው ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ
- አሌክሳንደር ኩራኖቭ፣ የቀድሞ የሴንት ፒተርስበርግ ሳይንሳዊ ምርምር ተቋም የሃይፐርሶኒክ ሲስተምስ ዳይሬክተር፣ በ2021 በቁጥጥር ስር ውለው በ2024 ሰባት ዓመታት የተፈረደባቸው
- ሮማን ኮቫሊዮቭ፣ የቭላድሚር ኩድሪየቭሴቭ ባልደረባ የነበሩ፣ በ2020 የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በ2022 ሕይወታቸው አለፈ።