217 ጊዜ የኮቪድ ክትባትን የተከተቡት ጀርመናዊ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው

አንድ የ62 ዓመት ጀርመናዊ ግለሰብ በህክምና ከሚመከረው በተቃራኒ እራሳቸውን ከኮቪድ-19 ለመከላከል 217 ጊዜ ክትባቱን መውሳዳቸውን ዶክተሮች ገለጹ።

ግለሰቡ ይህን ያህል መጠን ያለውን የበሽታውን መከላከያ ክትባት በግላቸው በመግዛት ቤታቸው ውስጥ የወሰዱት በ29 ወራት ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ ለየት ያለ ጉዳይም በታዋቂው የህክምና መጽሔት ‘ዘ ላንሴት’ ላይ ተዘግቧል።

በጀመርመኑ ኤርላንገን-ኑረምበርግ ዩኒቨሲርቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች እንዳሉት ግለሰቡ በሽታውን ለመከላከል አንድ ሰው ከሚያስፈልገው ጊዜ በላይ ቢከተቡም ምንም ዓይነት ጎጂ ውጤት አልገጠማቸውም።

ይህ ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው በአንድ ጋዜጣ ላይ ከወጣ በኋላ መሆኑን የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው የማይክሮባየሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ ዶ/ር ኪሊያን ሾበር “ግልሰቡን በዩኒቨርስቲው ውስጥ ምርመራ እንዲያደርግ ፈቃደኛ ነበሩ” ብለዋል።

በዚህም ግለሰቡ የደም እና የምራቅ ናሙና ለምርመራ ተየሰጠ ሲሆን፣ በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ ከዚህ ቀደም በላብራቶሪ በረዶ ቤት ውስጥ የተቀመጠ የግለሰቡን የደም ናሙና ለንጽጽር ተጠቅመዋል።

ከግለሰቡ የተገኙትን ናሙናዎች በመጠቀም በበርካታ የኮቪድ-19 ክትባት ወቅት የሰውዬው በሽታን የመከላከል ተፈጥሯዊ ሥርዓት ምን ዓይነት ምላሽ እንዳለው በምርመራው ለመረዳት እንደተጠቀሙበት ዶ/ር ሾበር ተናግረዋል።

ከሚያስፈልጋቸው በላይ ክትባቱን በወሰዱት ግለሰብ ላይ ምርመራ የጀመረው የሚኖሩባት ማግደበርግ ከተማ ዐቃቤ ሕግ የ130 ክትባቶችን ማስረጃዎች ሰብስቧል።

ዐቃቤ ሕጉ የማጭበርበር ድርጊቶች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ምርመራ እያካሄደ ቢሆንም፣ በግለሰቡ ላይ ግን የወንጀል ክስ አልመሠረተም።

የኮቪድ-19 ክትባቶች በተከታቢው ላይ በሽታውን የማያስከትሉ ሲሆን፣ ከዚያ ይልቅ ግን ሰውነ ቫይረሱን እንዴት መዋጋት እንዳለበት ለማለማመድ የሚረዱ ናቸው።

ሳይንሱ እንደሚለው በክትባቱ ውስጥ ያሉ ይዘቶች ወደ ሰውነት ከገቡ በኋላ ለህዋሳቶች የቫይረሱን የዘረ መል ቅንጣቶች እንዲያውቁ ያደርጋሉ።

በዚህም አጠቃላዩ ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት ቫይረሱን በመለየት ወደ ሰውነት በሚገባበት ጊዜ እንዲት መዋጋት እና ማስወገድ እንዳለበት ስለሚያውቅ በሽታውን መከላከል ይቻላል።

ነገር ግን ከሚመከረው በላይ ጀርመናዊው ግለሰብ እንዳደረጉት በተደጋጋሚ ክትባቱን መውሰድ በሽታን የመከላከል አቅምን ከሚገባው በላይ በማነቃቃት የተወሰኑ ህዋሳት እንዲዳከሙ ሊያደርግ እንደሚችል ዶ/ር ሾበር ይናገራሉ።

ቢሆንም ግን 217 ጊዜ የኮቪድ ክትባትን በተከተቡት የ62 ዓመቱ ግለሰብ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ውጤት ስለመከሰቱ ተመራማሪዎች ማስረጃ አላገኙም።

በተጨማሪም አስካሁን ድረስ ግለሰቡ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ምልክት አልተገኘም።

ይህንን ከስተት ተከትሎ ተመራማሪዎች ሰዎች የበለጠ በሽታውን የመከላከል አቅምን ይገነባል በሚል ከሚያስፈልጋቸው በላይ ክትባት መውሰድ እንደሌለባቸው መክረዋል።

“በአሁኑ ወቅት ባለው የጥናት ውጤት መሠረት አንድ ሰው ለኮቪድ-19 መከላከያ ሦስት ጊዜ ብቻ መከተብ ሲኖርበት፣ ተጋላጭ የሆኑት ደግሞ በመደበኝነት ከሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ክትባቶች ውጪ መውሰድ አያስፈልጋቸውም” ሲል ዩኒቨርስቲው በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።

የኮቪድ-19 ክትባት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከሦስት ጊዜ ሳይበልጥ የሚሰጥ ሲሆን፣ አንዳንድ በሽታን የመከካከል አቅማቸው ክፉኛ የተዳከመ ሰዎች ግን በሌሎች ጊዜዎች ተጨማሪ ክትባት በባለሙያዎች ምክር ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

የኮቪድ-19 ክትባቶች በሚወሰዱበት ጊዜ የጎንዮሽ ህመሞች ሊኖሯቸው ይችላሉ። በስፋት የሚታየው ደግሞ መርፌው በተወጋበት ክንድ ላይ የቁስለት ስሜት ማጋጠም ነው።