30 ሕሙማንን የመረዘው ፈረንሳዊ ዶክተር የዕድሜ ልክ እስር ተፈረደበት

ፍሬድሪክ ፔቺየር

የፎቶው ባለመብት, ARNAUD FINISTRE/AFP

የምስሉ መግለጫ, ፍሬድሪክ ፔቺየር

አንድ የቀድሞ በቀዶ ሕክምና ወቅት ማደንዘዣ የሚሰጥ ባለሙያ ሆን ብሎ 30 ታካሚዎችን በመመረዙ እና ከመካከላቸው አስራሁለቱ በመሞታቸው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

በምሥራቅ ፈረንሳይ ቤሳንኮን ከተማ የሚገኝ ፍርድ ቤት ፍሬድሪክ ፔቺየር በሕሙማን በደም ሥር በሚሰጥ ጠብታ ውስጥ የልብ ድካም ወይም የደም መፍሰስ የሚያስከትሉ ንጥረ ነገሮችን በመጨመር ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ፔቺየር ከመረዛቸው መካከል በዕድሜ ትንሹ የአራት ዓመት ልጅ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2016 የቶንሲል ቀዶ ሕክምና እየተደረገለት በነበረበት ወቅት ሁለት ጊዜ የልብ ድካም አጋጥሞት ተርፏል።

የሕክምና ባለሙያው ከመረዛቸው መካከል በዕድሜ የገፉት 89 ዓመታቸው ነበር።

"አንተ የሞት ዶክተር ነህ፣ መራዥ፣ ነፍሰ ገዳይ ነህ። ዶክተሮች አንገታቸውን እንዲደፉ ታደርጋለህ" ሲሉ ዐቃቤ ሕጎች ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

በተጨማሪም "ይህንን ክሊኒክ ወደ መቃብር ሥፍራ ቀይረኸዋል" ብለውታል።

ፔቺየር ለመጀመሪያ ጊዜ የወንጀል ምርመራ የተደረገበት ከስምንት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በወቀረቱ በቤሳንኮን በሚገኙ ሁለት ክሊኒኮች ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2008 እና 2017 መካከል ታካሚዎችን በመመረዝ ተጠርጥሮ ነበር።

የሕክምና ባለሙያው መጀመሪያ እንደመረዛት የምትጠረጠረው የ36 ዓመቷ ሳንድራ ሲማርድ ስትሆን፤ የአከርካሪ ቀዶ ሕክምና እያደረገች በነበረበት ወቅት ድንገተኛ የልብ ድካም አጋጥሟታል። በወቅቱ ራሷን ስታ የነበረ ቢሆንም ፔቺየር ጣልቃ ገብቶ ልትተርፍ ችላለች።

በደም ሥር በሚሰጥ ፈሳሽ (አይቪ) ከረጢቷ ላይ በተደረገ ምርመራ ከሚጠበቀው መጠን 100 እጥፍ የፖታሺየም ክምችት እንዳለው ታውቋል፤ ይህም የአካባቢው ዐቃቤ ሕግ ምርመራ እንዲያደርግ ምክንያት ሆኗል።

ሁለት ሳምንታት በፈጀው የችሎት ሂደት ወቅት ፔቺየር አንዳንድ የታመሙ ወይም የሞቱ ታካሚዎች ተመርዘው ሊሆን እንደሚችል አምኗል፤ ነገር ግን ምንም ዓይነት ጥፋት አልፈጸምኩም በማለት ተከራክሯል።

"ከዚህ በፊት ተናግሬዋለሁ፤ አሁንም እደግመዋለሁ፤ እኔ መራዥ አይደለሁም... ሁልጊዜም የገባሁትን ቃለ መሐላ አከብራለሁ"ብሏል።

ፔቺየር የፍርድ ሂደቱ እየታየ በነበረበት ወቅት ባለመታሰሩ ምክንያት ቢያንስ ለ22 ዓመታት በእስር ቤት ይቆያል።

ይግባኝ ለማቅረብ 10 ቀናት ያሉት ሲሆን፣ ይህም በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ችሎት ፊት እንዲቀርብ ያደርገዋል።