የሚስቱ የቆዳ ቀለም ጠቆር ያለ ነው በሚል አቃጥሎ የገደለው ህንዳዊ የሞት ቅጣት ተፈረደበት

የተገደለችው ላክሽሚ

የህንድ ፍርድ ቤት የባለቤቱ የቆዳ ቀለም ጠቆር ያለ ነው በሚል አቃጥሎ የገደለውን ግለሰብ የሞት ቅጣት ፈረደበት።

ላክሽሚ የተባለችው ግለሰብ ከመሞቷ በፊት ባለቤቷ "የቆዳዋ ቀለም ጠቆር ያለ" ነው በሚል በተደጋጋሚ ያሰቃያት እንደነበር ተናግራ ነበር።

በሰሜን ኡዳፑር ከተማ ዳኛ የሆኑት ራሁል ቹድሪ ግድያው "ታይቶ እንዲሁም ተሰምቶ የማይታወቅ" እንዲሁም "በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ" ወንጀል ሲሉ ፈርጀውታል።

የሞት ቅጣት የተፈረደበት ኪሻንዳስ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው ንጹህ መሆኑን እና ብይኑን በመቃወም ይግባኝ እንደሚሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ከስምንት ዓመታት በፊት የተፈጸመው የዚህ ግድያ ውሳኔ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መደረሱን ተከትሎ በማህበረሰቡ ውስጥ ስር የሰደደውን ቀይ የቆዳ ቀለም የመውደድ አባዜ መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም።

በግለሰቧ ላይ ጥቃት የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ ሰኔ 24/ 2017 ምሽት እንደነበር ቢቢሲ ከፍርድ ቤት ውሳኔው መረዳት ችሏል።

ላክሽሚ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቷ ከማለፉ በፊት ለፖሊስ፣ ለዶክተሮች እና ለመርማሪ የተናገረችው ምስክርነት በዚህ ውሳኔ ላይ ሰፍሯል።

ከተጋቡበት ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ ባለቤቷ "ካሊ" ወይም ጥቁር እያለ ይጠራት እንዲሁም በቆዳ ቀለሟም ሲያሸማቅቃት እንደነበር መናገሯ ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተገደለችበት ምሽት ባለቤቷ ቡናማ ፈሳሽ የያዘ ጠርሙስ ይዞ መጥቶ ቆዳዋን ለማቅላት የሚረዳት መድኃኒት እንደሆነ ነገራት።

ፈሳሹን ሰውነቷ ላይ ያፈሰሰው ሲሆን እሷም የአሲድ ሽታ አለው ብላ ስታማርር በእሳት የተያዘውን ሰንደል ለኮሰባት።

ሰውነቷ በእሳት መያያዝ ሲጀምር የቀረውን ፈሳሽ በላይዋ ላይ ደፍቶ ሮጦ ሸሸ።

የባለቤቷ ወላጆች እንዲሁም እህቱ ወደ ሆስፒታል ለህክምና ቢወስዷትም ህይወቷ አልፏል።

"ይህ ልብን የሚሰብር አረመኔያዊ ወንጀል በላክሽሚ ላይ የተፈጸመ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም" ሲሉ ዳኛ ቹድሃሪ በውሳኔያቸው ላይ ተናግረዋል።

ኪሻንዳ "እሷ እየተቃጠለች በነበረበት ወቅት የቀረውን ፈሳሽ በላይዋ ላይ በመድፋት ከመጠን በላይ ያለፈ ጭካኔን አሳይቷል" ብለዋል ዳኛው።

"በጤናማ እና በሰለጠነ ማህበረሰብ ውስጥ ሊታሰብ የማይችል የሰውን ልጅ ህሊናን የሚረብሽ ወንጀል ነው" ሲሉ ዳኛው በውሳኔያቸው አሳውቀዋል።

አቃቤ ህግ ዲኔሽ ፓሊዋል በበኩላቸው ውሳኔው "ታሪካዊ" እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸው፤ ለሌላው ማህበረሰብ ማስተማሪያ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው አክለዋል።

"በ20ዎቹ መጀመሪያ የምትገኝ አንዲት ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላለች። እህት፣ ልጅ ነበረች። የሚወዷት ሰዎች ነበሩ። እኛ ልጆቻችን መታደግ ካልቻልን፤ ማን ይቻለዋል?" ሲሉ አክለዋል።

አቃቤ ህግ የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ውሳኔውን ለከፍተኛ ፍርድ ቤት መተላለፉን ገልጸው፤ ነገር ግን ግለሰቡ ይግባኝ ለማለት የ30 ቀናት ጊዜ እንዳለው ገልጿል።

የኪሻንዳስ ጠበቃ ሱሬንድራ ኩመር ሜናሪያ በበኩላቸው የላክሽሚ ሞት ድንገተኛ እንደሆነና በደንበኛቸው ላይ የቀረበበት ክስ ሃሰተኛ እንዲሁም ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌለም ተናግረዋል።