በጉበቷ ውስጥ እርግዝና ተፈጥሮ ሳይታወቅ የተሰቃየችው እናት፤ እንዲህ ያለው እርግዝና እንዴት ይፈጠራል?

የ35 ዓመቷ ሳርቬሽ ታምማ አልጋ ከያዘች ቆይታለች።
"ያለማቋረጥ ያስመልሰኝ ነበር። ሁልጊዜም ድካም እና ሕመም ነበረኝ" ትላለች።
ሳቬሽ መጀመሪያ በተደረገላት የአልትራሳውንድ ምርመራ ሕመሟ ምን እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም።
እርሷም "ምን እንዳመመኝ ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ነበር" ትላለች።
በሕንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ከቡላንድሻህር አውራጃ የመጣችው ሳርቬሽ ሕመሟ መጀመሪያ ላይ የሆድ ኢንፌክሽን መሆኑ ስለተጠረጠረ የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት እንድትወስድ ተደረገ።
መድኃኒቱን አንድ ወር ከወሰደች በኋላ ለውጥ ስላላየች ተመልሳ ሄደች።
በዚህ ጊዜ ግን በተደረገላት ምርመራ ዶክተሯ ያየውን ነገር ማመን አልቻለም። ለእርሷም ቢሆን ዱብ ዕዳ ነው የሆነባት።
ዶ/ር ኬኬ ጉፕታ በሕንድ ላለፉት 20 ዓመታት የራጅ ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል። የሳርቬሽን የምርመራ ውጤት ሲመለከት ግን እጅግ መደነቁን መሸሸግ አልቻለም።
ከዚህ በፊት በኤምአርአይ ምርመራ አጋጥሞ የማያውቀው እና በሳርቬሽ ላይ የታየውን የምርመራ ውጤት ሲናገር "በቀኝ ጉበቷ በኩል የ12 ሳምንት እርግዝና ያሳያል" ነበር ያለው።
"የምርመራ ውጤቱን የተለያዩ ክፍሎች በተደጋጋሚ በመውሰድ ትክክለኛ እርግዝና መሆኑን ለማረጋገጥ ጥሬያለሁ" ይላሉ ዶክተሯ።

እንዲህ ዓይነት እርግዝና የሚፈጠረው ከወንዴ ዘር ጋር የተገናኘው እና የዳበረው የሴቷ እንቁላል ከማህጸን ውጪ፣ ብዙ ጊዜ በማህጸን ቱቦ ውስጥ ማደግ በሚጀምርበት ወቅት ነው።
እርግዝና አንዳንድ ጊዜ በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ማለትም በእንቁላል ማኩረቻ (ኦቫሪ)፣ የሆድ እቃ ወይም የማህጸን ጫፍ ላይ ይከሰታል።
ከ80 እርግዝናዎች ውስጥ አንዱ ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ የእናቲቱን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥልም ይችላል።
ሳርቬሽ ጽንሱ በማህጸኗ ውስጥ ከማደግ ይልቅ በጉበቷ ላይ ነበር ማደግ የጀመረው።
ጉበት ደግሞ ከደም ውስጥ መርዛማ ነገሮችን በማስወገድ የስኳር መጠንን እና የደም መርጋትን በመቆጣጠር ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ኢንትራሄፓቲክ (intrahepatic) የሚባለው በጉበት ውስጥ የሚፈጠረው ከማህጸን ውጪ እርግዝና በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት በመሆኑ ሳርቬሽ የዓለም አቀፍ የሕክምና ማኅበረሰብ ትኩረት እንድታገኝ አድርጓታል።

ማገገም
ጥንዶቹ ያለፉባቸው ሦስት ወራት ለመላው ቤተሰባቸው በጣም ፈታኝ እንደነበር እና ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራሉ።
ቢቢሲ እርሷን ለማግኘት በዳስቱራ መንደር ወደሚገኘው የሳርቬሽ ቤት አምርቶ ነበር።
በአልጋዋ ላይ እረፍት እያደረገች ቢሆንም ሕመሟ ግን አልቀነሰም።
ሆዷ ላይ 21 ቦታዎች ላይ ያሉትን ስፌቶች ለመሸፈን ሰፊ የሆነ ፋሻ ታስሮላታል።
መታጠቢያ ቤት ለመጠቀም፣ አልጋ ላይ ለመቀመጥ እና ልብስ ለመቀየር በባልዋ ፓራምቪር መታገዝ አለባት።
ሳርቬሽ በተለይ በዶክተሮች የተነገራትን መቀበል በጣም ከባድ እንደሆነባት ተናግራለች።
ምክንያቷ ደግሞ የወር አበባ ዑደቷ የተለመደ እና ጤናማ ነበር።
በእንደዚህ ዓይነት ከማህጸን ውጪ እርግዝና ሴቶች ብዙ ደም ይፈስሳቸዋል።
ዶ/ር ኬኬ ጉፕታ "ስለዚህ እርግዝና መከሰቱን ለማወቅ ጊዜ ይወስዳል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ከበርካታ ምርመራዎች በኋላ ዶክተሮቿ ጽንሱን ለማስወገድ ከቀዶ ሕክምና ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ወሰኑ። ጽንሱ ማደጉን ከቀጠለ ጉበቷ ተቀድዶ ለህልፈት ትዳረጋለች የሚል ስጋት ነበራቸው።
ከሕክምናው ውስብስብነት የተነሳ ጥንዶቹ ለቀዶ ሕክምና ወደ ሕንድ ዋና ከተማ ዴልሂ እንዲሄዱ ቢመከሩም ወጪውን መሸፈን ግን አልቻሉም።
ፓራምቪር "እኛ ድሆች ነን፤ እና ወደ ዴልሂ ሄደን ወጪውን መሸፈን አንችልም ነበር" ብሏል።
በመጨረሻም ሰርቬሽ ከሦስት ወራት ሕመም በኋላ፣ ዶክተሮች በምትኖርነት አካባቢ በሚገኝ የግል ሆስፒታል ውስጥ 90 ደቂቃ የፈጀ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ተስማሙ።

ጉበት ላይ የሚፈጠር እርግዝና
አንዲት ሴት እንቁላሏ ከእንቁላል ማኩረቻዋ (ኦቫሪ) ወጥቶ ከወንዴ ዘር ጋር ሲገናኝ እና ሲዳብር እርግዝና እንደሚፈጠር የማህጸን እና የጽንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ማምታ ሲንግ ይናገራሉ።
ይህ የዳበረ እንቁላል በማህጸን ቱቦዎች በኩል ጽንሱ ወደ ሚያድግበት ወደ ማህጸን ይሄዳል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ይላሉ ዶ/ር ሲንግ፣ ይህ የዳበረ እንቁላል ወደ ማህጸን ከመድረስ ይልቅ በማህጸን ቱቦ ውስጥ ይቀራል ወይም በጣም አልፎ አልፎ ከሌላ አካል ላይ ይጣበቃል።
ለሳርቬሽ ጽንሱ ከጉበቷ ጋር ተጣብቋል። ጉበቱ ለጽንሱ ያለው የደም አቅርቦት ጥሩ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ለጽንሱ "ምቹ" ሆኖ ማገልገሉን ዶ/ር ሲንግ ያስረዳሉ።
ነገር ግን ውሎ ሲያድር የጤና እክል መፈጠር ጀመረ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ አንድ በመቶ የሚጠጉት እርግዝናዎች ከማህጸን ውጪ የሚከሰቱ ናቸው የሚሉት ደግሞ ሌላኛዋ የጽንስና የማህጸን ሕክምና ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሞኒካ አናንት ናቸው።
"ከሰባት እስከ ስምንት ሚሊዮን ከሚሆኑት እርግዝናዎች መካከል አንዱ ብቻ ከማህጸን ውጪ ጉበት ላይ ሊከሰት እንደሚችል ይገመታል" ብለዋል።
ከሳርቬሽ በፊት፣ ዶ/ር አናንት በዓለም አቀፍ ደረጃ 45 በጉበት ላይ የተከሰቱ እርግዝናዎች ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ በሕንድ ውስጥ ነበር የተከሰቱት። የመጀመሪያው እርግዝና በአውሮፓውያኑ 2012 በሕንድ ዴልሂ መከሰቱን ተመዝግቦ ይገኛል።
በሕክምና ተቋም ውስጥ ከማህጸን ውጪ የተፈጠረ እርግዝና በሦስት ዓይነት የምርመራ ዘዴ ይለያል።
የምርመራ መንገዶቹም ሽንት፣ ደም እና አልትራሳውንድ ናቸው።
እናቶች ወደ ሕክምና ተቋም ለመሄድ በዘገዩ ቁጥር ለተለያዩ ችግሮች እና ጉዳቶች የመጋለጥ ዕድላቸው ይጨምራል። ከጉዳቶቹ መካከል በቀዶ ሕክምና የማህጸን ቱቦ እንዲወጣ ሊያደርግ (ሊያሳጣ) ይችላል።
ጽንስ ሆድ ውስጥ እንዲፈነዳ ወይም በሆድ ውስጥ ደም እንዲፈስ ያደርጋል። ሆድ ውስጥ ደም ሲፈስ ደግሞ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ደም ሊያልቅ ይችላል። ይህም የእናትን ሕይወት ያሳጣል።















