ጀርመናዊው ነርስ የሥራ ጫና ለማቅለል በሚል 10 ሰዎችን በመግደሉ እድሜ ልክ ተፈረደበት

ከመድሃኒት ብልቃጥ መድሃኒት የሚስብ መርፌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጀርመን በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይሰራ የነበረ ነርስ 10 ሕሙማን በመግደል እና 27 ሰዎች ላይ ደግሞ የግድያ ሙከራ በማድረግ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የእድሜ ልክ እስር ተፈረደበት።

አቃቤ ሕግ ሥሙን በይፋ ያልገለፀው ይህ ነርስ ሥራውን ለማቅለል በሚል የሕመም ማስታገሻ ወይንም የእንቅልፍ መድሃኒት የተሰጣቸው አዛውንት ሕሙማንን መድሃኒት በመስጠት እንዲሞቱ አድርጓል ብሏል።

ነርሱ ይህንን ወንጀል የፈጸመው እንደ አውሮፓውያኑ ከታሕሳስ 2023 እስከ ግንቦት 2024 በምዕራብ ጀርመን በዉርሴለን ባለ ሆስፒታል ነው።

መርማሪዎች ነርሱ በሙያው ላይ እየሰራ በቆየባቸው ዓመታት የታዩ አጠራጣሪ ጉዳዮች ላይም ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ነርሱ በዉርሴለን በሚገኘው ሆስፒታል እአአ በ2007 የነርስነት ሙያ ስልጠና ከወሰደ እና ካጠናቀቀ በኋላ ከ2020 ጀምሮ ተቀጥሮ ይሰራ ነበር ብሏል።

አቃቤ ሕግ አቻን ለሚገኘው ፍርድ ቤት ሲያስረዳ ከፍተኛ እንክብካቤ በሚፈልጉ ታማሚዎች ላይ "ቁጣ" እና ርህራሄ ማጣት ማሳየቱን እንዲሁም ራሱን "የሕይወት እና የሞት ጌታ" በማድረግ አቅርቧል ሲል አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱ አክሎም የለሊት ፈረቃ ሥራውን ለማቅለል በሚል ሕሙማኑን ከፍተኛ መጠን ያለው ሞርፊን እና ሚዳዞላም የተሰኙ መድሃኒቶች በመውጋት ሕይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል ብሏል።

የሕክምና ባለሙያው በቁጥጥር ሥር የዋለው እአአ በ2024 ነበር።

ፍርድ ቤቱ የእድሜ ልክ ፍርዱን ሲሰጥ ግለሰቡ የፈፀመው ወንጀል "በወንጀሉ ክብደት የተነሳ" በተለይ ከ15 ዓመት በፊት ቶሎ እንዳይፈታ ሲል ክልከላ አስቀምጧል።

የሕክምና ባለሙያው ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ ነው።

አቃቤ ሕግ ለኤኤፍፒ እንደተናገረው ተጨማሪ ተጎጂዎች የሆኑ ሊኖሩ የሚችሉ ሰዎችን ለመለየት ቁፋሮ እየተካሄደ ሲሆን በዚህም የተነሳ ግለሰቡ በድጋሚ ለፍርድ ሊቀርብ ይችላል።

ይህ ወንጀል እአአ በ2019 በሰሜናዊ ጀርመን በሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች 85 ታካሚዎችን በመግደል ወንጀል ተከሶ የእድሜ ልክ እስራት ከተቀጣው የቀድሞ ነርስ ኒልስ ​​ሆጌል ጋር ተመሳሳይነት አለው።

ግለሰቡ እአአ ከ1999 እስከ 2005 ባሉት ጊዜያት በስሩ ለነበሩ ሕሙማን ለልብ ሕመም የሚሰጥ መድሃኒት በከፍተኛ መጠን በመስጠት እንዲሞቱ ማድረጉ ተገልጾ ነበር።

በዘመናዊ ጀርመን ታሪክ ውስጥ በርካታ ግድያ የፈፀመ የሕክምና ባለሙያ ነው ተብሎ ነበር።