14 ጓደኞቿን በመርዝ ገድላለች የተባለችው ታይላንዳዊት በሞት እንድትቀጣ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, EPA
14 ጓደኞቿኝ ሲያናይድ በተባለ መርዝ ገድላለች ተብላ የተጠረጠረችው ታይላንዳዊት በመጀመሪያው ክስ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ በሞት እንድትቀጣ ተወሰነ።
በዋና ከተማዋ ባንግኮክ የሚገኘው ፍርድ ቤት ሳራራት ራንግሲዉታፖርን የተባለችው የ36 ዓመት ተከሳሽ ባለፈው ዓመት ከሀብታም ጓደኛዋ ጋር ሽርሽር ወጥተው ሳለ ምግብ እና መጠጥ በመመረዝ ገድላታለች ተብላ ጥፋተኛ ሆናለች።
የሟች ዘመዶች እና ጓደኞች ግለሰቧ በተፈጥሯዊ መንገድ አይደለም የሞተችው በማለት ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ የሬሳ ምርመራ ተደርጓል። ምርመራው የሟች ሰውነት ውስጥ ሲያናይድ የተባለው መርዝ መገኘቱን አሳይቷል።
ፖሊስ ይህን ተከትሎ ሳራራትን በቁጥጥር ሥር ባዋለበት ወቅት ሌሎች ግድያዎች መፈፀማቸውን ማጣራት የቻለው።
ጉዳዩ እስከ አውሮፓውያኑ 2015 ድረስ የሚጓዝ ሲሆን ጥፋተኛዋ ዒላማ ካደረገቻቸው ሰዎች መካከል አንዷ መትረፏ ተነግሯል።
ፖሊስ እንደሚለው በታይላንድ መገናኛ ብዙኃን 'አም ሲያናይድ' የተሰኘ ቅፅል ስም የተሰጣት ሳራራት የቁማር ሱስ ያለባት ሲሆን ብድር የወሰደችባቸውን ጓደኞቿን በመግደል ጌጣጌጥ እና ጥሩ ገንዘብ የሚያወጡ ንብረቶቻቸውን ትዘርፋለች።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ነው ሳራራት እና ጓደኛዋ ሲሪፖርን ኻንዎንግ ወደ ምዕራብ ባንግኮክ ለሽርሽር ያቀኑት።
ኻንዎንግ ከሲራራት ጋር ምግብ ከበላች በኋላ ተዘልፈልፋ ትወድቃለች። ጓደኛዋ ራሷን ስታ ስትወድቅ ሳራራት ልታድናት ምንም ሙከራ አላደረገችም ይላሉ መርማሪዎች።
ምርመራው ሲጠናከር ሲያናይድ የተባለው መርዝ ቅሪት የኻንዎንግ ሰውነት እና ስልኳ ላይ የተገኘ ሲሆን ገንዘብ እና ቦርሳዎቿ ጠፍተው ነበር ይላል ፖሊስ።
“ልጄ ፍርድ አገኘሽ ዛሬ። ዛሬ በዓለም ፍትሕ ወርዷል” ሲሉ የልጃቸውን ፎቶ ከፍ አድርገው ይዘው የነበሩት የካንዎንግ እናት ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
እናት እንደሚሉት ውስጣቸው ካለው ንዴት የተነሳ ሳራራት ቀና ብለው ማየት ተስኗቸው ነበር። አልፎም ብይኑ ሲነበብ ሳራራት ፈገግ ብላ ነበር ይላሉ።
ሳራራት የቀረቡባትን ክሶች ታስተባብላለች።
የፖሊስ አባል የነበረው የተከሳሿ የቀድሞ ባል እና ጠበቃዋ ማስረጃ ሸሽገዋል በሚል የአንድ ዓመት ከአራት ወር እና የሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የቀድሞው ባሏ ቪቱን ባለፈው ዓመት ነው እጁን ለፖሊስ የሰጠው። ፖሊስ እንደሚለው ግለሰቡ ሳራራት የቀድሞ የፍቅር ጓደኛዋን መርዛ ስትገድለው ተባባሪ ሳይሆን አይቀርም።
ሳራራት ለኻንዎንግ ቤተሰቦች ሁለት ሚሊዮን የታይላንድ ባት ካሳ እንድትከፍል ተወስኖባታል። ገንዘቡ ወደ ዶላር ሲመነዘር 57 ሺህ ገደማ ይሆናል።
ሲያናይድ የተባለው ኬሚካል የኦክሲጅን ሴሎችን የሚጎዳ ሲሆን የልብ ድካም ሊያስከትል ይችላል። መደንዘዝ፣ ትንፋሽ ማጠር እና ማስመለስ ምልክቶቹ ናቸው።
ይህ ኬሚካል በዛ ተደርጎ ከተወሰደ ሳንባን የሚጎዳ እና ኮማ አስከትሎ በሰከንዶች ውስጥ ሊገድል የሚችል ሲሆን አነስተኛ መጠን ያለውም ቢሆን እጅግ አደገኛ ነው።
ታይላንድ ውስጥ ያለመንግሥት ፈቃድ ይህን ኬሚካል ይዞ መገኘት እስከ ሁለት ዓመት እስር ሊያስቀጣ ይችላል።












