ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኡጋንዳ የ70 ዓመቷ አዛውንት መንታ ልጆችን ተገላገሉ
በኡጋንዳ የ70 ዓመቷ አዛውንት መንታ ልጆችን መውለዳቸውን የወለዱበት ሆስፒታል አስታወቀ።
ሳፊና ናሙክዋያ የተባሉት አዛውንት ማርገዝ የቻሉት አይቪኤፍ ተብሎ በሚጠራው በሳይንዳዊ ድጋፍ እርግዝና እንዲፈጠር የሚያደርግ ድጋፍ ካገኙ በኋላ መሆኑን ሆስፒታሉ አስታውቋል።
በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የሚገኘው የሴቶች ሆስፒታል እና የወሊድ ማዕከል አዛውንቷ ወንድ እና ሴት ልጆችን መገላገላቸውን ገልጾ ይህም እናቲቱን በአፍሪካ በዕድሜ ትልቋ አርግዘው መውለድ የቻሉ ሴት ያደርጋቸዋል ብሏል።
ሳፊና ናሙክዋያ በቀዶ ሕክምና ሁለት ልጆቻቸውን ከተገላገሉ በኋላ ሆስፒታሉ በፌስቡክ ገጹ ላይ የአዛውንቷ ታሪክ የሚየሳየው “ትልቁ ነገር የሕክምና ስኬት ሳይሆን የሰው ልጅ ጥንካሬን ነው” ብሏል።
ናሙክዋያ ኤንቲቪ ለተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ በእርጅና ዘመናቸው ልጅ ሲወልዱ ይህ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ እና ከሦስት ዓመት በፊት እአአ 2020 ላይ ሴት ልጅ ወልደው እንደነበረ ተናግረዋል።
አዛውንቷ በእርግዝና ጊዜ በርካታ ችግሮች እንዳጋጠሟቸው ጠቅሰው፤ የትዳር አጋራቸውም ጥሏቸው እንደሄደ ተናግረዋል።
“መንታ ልጅ መጸነሱን ወንዶች መስማት አይፈልጉም። እዚህ ሆስፒታል ከገባው ጀምሮ ባለቤቴ መጥቶ አላየኝም” ብለዋል።
ናሙክዋያ ለማርገዝ የሕክምና ድጋፍን ፈልገው መንታ ልጆችን ቢገላገሉም እነዚህን ልጆች እንዴት አድርጌ እንደማሳድግ ግራ ገብቶኛል ብለዋል።
ይሁን እንጂ እናቲቱ ልጆቼ በማግኘቴ ለዓመታት ልጅ አልባ በመሆኔ ሲደርስብኝ ከቆየው መገለል እና ሃሜት ገላግሎኛል ብለዋል።
“አንድ ግዜ አንድ ወጣት ልጆች ሳልወልድ እንድሞት በእናቴ የተረገምኩ መሆኔን ተናግሮኝ ነበር” በማለት ይደርስባቸው የነበረውን ጫና ያስታውሳሉ።