ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ቢሊዮነር በጣሊያኗ ከተማ የሚያደርገው ሰርግ በተቃውሞ ምክንያት ቦታውን ለመቀየር ተገደደ
በጣልያኗ ቬኒስ ከተማ አክቲቪስቶች 'ባደረግነው ተቃውሞ አሜሪካዊውን ቢሊዮነር ጄፍ ቤዞስ እና የሠርግ ታዳሚዎቹን ፕሮግራሙ ሊካሄድ ከታቀደበት ዋና ሥፍራ ወደ ሌላ እንዲቀይሩ በማድረግ ድል አስመዝግበናል' አሉ።
ከዓለም ባለጸጋዎች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዱ ቤዞስ እና የትዳር አጋሩ የቲቪ አቅራቢዋ ላውረን ሳንቼዝ በቬኒስ የሚያደርጉት የሠርግ ድግስ በይፋ የተገለጸ አይደለም።
ሆኖም ይህ እጅግ ውድ የሠርግ መርሃ ግብር በቬኒስ እምብርት በሚገኝ አንድ ሥፍራ በሚደረግ ፕሮግራም እንዲጠናቀቅ ታቅዶ ነበር።
ሆኖም መርሃ ግብሩ ቀድሞ ሊካሄድበት ከነበረው የቬኒስ እምብርት ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወሩን የከተማ ባለስልጣናት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ታቀውሞውን አንድ የምክር ቤት አባል 'ቀልድ' ሲሉ ቢያወግዙትም ይህንን መርሃ ግብር የተቃወሙ አክቲቪስቶች ግን ድል አመስመዝግበናል ሲሉ ተደምጠዋል።
'ለ ቤዞስ ቦታ የለንም' በሚል የተዋቀረው የተቃውሞ ቡድን ውስጥ ተሳታፊ የሆ አንቶማሶ ቻቺያሪ የተባለ ነዋሪ "ይህንን በማድረጋችን ኩራት ይሰማናል። እኛ ምንም የተለየ ስልጣን ወይም ገንዘብ የለንም" ሲል ገልጿል።
አክሎም "በዓለም ላይ ያሉ ትልቅ አቅም ያላቸውን ቢሊየነሮችን ከከተማው ዞር ማድረግ የቻልን ተራ ዜጎች ነን " ብሏል።
የጋብቻ ድግሱ በዚህ ሳምንት ማብቂያ እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን ኪም ካርዳሽያን፣ ሚክ ጃገር እና ሊዎናርዶ ዲካፕሮን ጨምሮ ዝነኛና ባለጸጋ ሰዎች እንደሚታደሙ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው።
በርከት ያሉ የግል አውሮፕላኖች የጣልያኗን ቬኒስ ከተማ አየር መንገድ እንደሚሞሉት ይጠበቃል። የግል ጀልባዎችም በቬኒስ የወንዝ ዳርቻዎች ላይ ይታያሉ። በከተማዋ የሚገኙ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ሙሉ ክፍላቸው ቀድሞ የታያዘ ሲሆን የቀደሞ የአሜሪካ ባህር ኃይል ሠራተኞች ጥበቃውን እንዲቆጣጠሩ ተቀጥረዋል።
ሆኖም ይህ ፕሮግራም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ እየገጠመው ነው። አንዳንዶች ይህ የሠርግ ድግስ የከተማዋን የቱሪስት እንቅስቃሴዎች ይገታል በሚል ሲቃወሙት ሌሎች ደግሞ ባለሀብቱ ለትራምፕ ባለው ቅርበት ድግሱን እየተቹ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በከተማዋ በሚገኙ ድልድዮች 'ለቤዞስ ቦታ የለንም' የሚሉ ተቃውሞችን ያዘሉ 'ፖስተሮች' ተለጥፈው ታይተዋል።
ባለፈው ሰኞ ሌላ የተቃውሞ ቡድን ደግሞ "ቬኒስን ለሠርግህ መከራየት ከቻልክ ተጨማሪ ታክስ ክፈል" የሚል ጽሁፍ ይዘው ታይተዋል
ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዱ "እኛ እየተቃወምን ያለነው ሠርጉን ሳይሆን ሠርጉ ያስተላለፈውን የተሳሳተ መልዕክት ነው" ብሏል።
እንዲህ አይነት ትልቅ ስም ያላቸው ሰዎች በከተማዋ ሲገኙ ለከተማዋ ጠቃሚ ገቢ ያስገኛል ሲሉ የሚከራከሩት የከተማዋ ባለስልጣናት ታቃዋሚዎችን ኮንነዋል።
የከተማዋ ምክር ቤት አባል የሆኑ ሳይመን ቬንቱሮኒ "ተቃዋሚዎች የቬኒስ ባለቤት እንደሆኑ ነው የሚሰማቸው። እዚህ ማን ማግባት እንዳለበት ማንም መወሰን አይችልም" ብለዋል።
ጨምሮም "ተቃዋሚ ቡድኖቹ በጣም ትንሽ ቁጥር ነው ያላቸው የከተማዋን ነዋሪ መወከል አይችሉም" ሲሉ አክለዋል።
"ፕሮግራሙ 200 በጥንቃቄ የተመረጡ እንግዶች የሚታደሙት ነው። ለከተማዋም ትልቅ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያስገኛል" ያሉት ፖለቲከኛው ሁሉም ሁነቶች በግል ይዞታዎች ላይ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
ሆኖም ከተማዋ በሚጎርፍባት ከፍተኛ ቱሪስት ነዋሪዎች ዋጋ እየከፈልን ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
በተጨማሪም በአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት የከተማዋ የውሃ አካላት አደጋ ላይ ወድቀዋል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ።
የከተማዋ ባለስልጣናት ከተማዋን የሚጎበኙ ሰዎች በየቀኑ አምስት ዩሮ እንዲከፍሉ ህግ ቢያወጡም ቱሪስቶች ከተማዋን ከማጨናነቅ አልተገቱም ሲሉ አክቲቪስቶች ይናገራሉ።
የሠርጉ የመጀመሪያ እንግዶች ዛሬ ሀሙስ ወደ ከተማዋ እንደሚገቡና የውሃ አካላት ላይ ፕሮግራም እንደሚያደረጉ ቢጠበቅም ተቃዋሚዎች ግን መንገዶችን ለመዝጋት ማቀዳቸው ተሰምቷል።
በድግሱ ማብቂያ ቀን ቅዳሜ በርካታ ሰዎች የሚሳታፉበት ሠልፍ ለማድረግም ዕቅድ ይዘዋል።