ቡርኪናፋሶ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ሳይከፍሉ ቪዛ እንዲያገኙ ወሰነች

ቡርኪናፋሶ ወደ ግዛቷ የሚገቡ የየትኛውም የአፍሪካ አገር ዜጎች የቪዛ ክፍያ ሳያስፈልጋቸው በነጻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አስታወቀች።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ከመሩት የሚኒስትሮች ስብሰባ በኋላ ሲሆን፣ ዓላማውም ወደ አገሪቱ የሚገቡ የሰዎች እና የሸቀጦችን እንቅስቃሴ ማቀላጠፍ ነው።

"ከአሁን በኋላ ከየትኛውም የአፍሪካ አገር ወደ ቡርኪናፋሶ መግባት የሚፈልጉ ዜጎች ምንም ዓይነት የቪዛ ክፍያ አይጠበቅባቸውም" ሲሉ የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስትር ማሐማዱ ሳና ተናግረዋል።

ነገር ግን ወደ ቡርኪናፋሶ የሚገቡ አፍሪካውያን መንገደኞች በበይነ መረብ አማካይነት የቪዛ መጠየቂያ ማመልከቻ ማስገባት የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ይህም በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ተመርምሮ ምላሽ ይሰጠዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቡርኪናፋሶ ለአፍሪካውያን ጎብኚዎች የሚያስፈልገውን የቪዛ ክፍያን ለማስቀረት ቀደም ሲል ከወሰኑት ከጋና፣ ከሩዋንዳ እና ከኬንያ ጋር ተቀላቅላለች።

ቀደም ሲልም የምዕራብ አፍሪካ አገራት ዜጎች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ ቡርኪናፋሶ መግባት የሚችሉ ሲሆን፣ ነገር ግን በቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ማኅበር በመውጣቷ ይህ ሊቀየር ይችላል።

ተጎራባች በሆኑት ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ ወታደራዊ መንግሥታት ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከማኅበሩ በመታገዳቸው የራሳቸውን ኅብረት ፈጥረዋል።

ወጣቱ ወታደራዊ መኮንን ሻምበል ትራኦሬ በአውሮፓውያኑ 2022 የቡርኪናፋሶን መሪነት በመፈንቅለ መንግሥት ከያዙ በኋላ ምዕራባውያንን እና ቅኝ ግዛትን አጥብቀው በመተችት የአፍሪካ አንድነት እንቅስቃሴን ያቀነቅናሉ።

በመላው አህጉሪቱም ዝናቸው እየነኛ ሲሆን፣ ትራኦሬን የሚመለከቱ የተለያዩ መረጃዎች እና ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ይሠራጫሉ፤ አንዳንዶቹም ሐሰተኛ እና የተጋነኑ ናቸው።

ኢብራሂም ትራኦሬ ባለፉት ሦስት ዓመታት የሥልጣን ቆይታቸው ወቅት ፈላጭ ቆራጭ የአመራር ሥርዓትን በመከተል፣ ተቃዋሚዎቻቸውን የሚይዙበት መንገድ እና በአገሪቱ ያለውን የእስላማዊ አማጺያን እንቅስቃሴን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ይተቻሉ።

በሳህል አካባቢ እንዳሉት ጎረቤቶቿ ሁሉ ቡርኪናፋሶም ለዓመታት ከታጣቂ እስላማዊ ቡድኖች ጋር ስትፋለም ቆይታለች። በአሁኑ ጊዜም ከአገሪቱ አጠቃላይ ግዛት 40 በመቶ የሚደርሰው በእነዚህ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ይገኛል።

በትራኦሬ የሚመራው የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መንግሥት ከሩሲያ ጋር አዲስ ወዳጅነት መሥርቶ በአገሪቱ መረጋጋት ለማስፈን ቃል ቢገባም ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ሁኔታው እየተባባሰ ነው።

ቡርኪናፋሶ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ቪዛ በነጻ እንዲያገኙ የሚያዘው ውሳኔን በተመለከተ ከወታደራዊ መንግሥቱ የማስታወቂያ አገልግሎት የወጣው መግለጫ ቡርኪናፋሶ ከአፍሪካ አንድነት እንቅስቃሴ እሳቤ ጋር ያላትን ትስስር የሚያንጸባርቅ እና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክቷል።

"ለአፍሪካውያን የተከፈተው አዲሱ የቪዛ ሥርዓት ቱሪዝምን ለማስፋፋት፣ የአገሪቱን ባሕል ለማስተዋወቅ እና ትኩረት እንድታገኝ ለማድረግ ነው" ብሏል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከአህጉሪቱ ለሚመጡ የሌሎች አገራት ዜጎች የሚያስፈልገውን የቪዛ ቅድመ ሁኔታ እያላሉት ቢሆንም፤ ጥናቶች ግን በአፍሪካ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ከአፍሪካውያን ይልቅ ለምዕራባውያን ጎብኚዎች ቀላል ነው።

በአፍሪካ ውስጥ ለሚደረግ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር የአፍሪካ ኅብረት በአባል አገራቱ ላይ ግፊት እያደረገ ነው።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ጋና የየትኛውንም የአፍሪካ አገር ፓስፖርት የያዙ አፍሪካውያን ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ ግዛቷ እንዲገቡ ፈቅዳለች።

ቀደም ብሎ ደግሞ ኬንያ ወደ ግዛቷ ለመግባት የሚፈልጉ ሰዎች ቀድመው በበይነ መረብ አማካይነት በማመልከት ብቻ ያለቪዛ ወደ አገሯ እንዲገቡ የሚያደርግ አሠራር ጀምራለች።

ሩዋንዳም በበኩሏ አፍሪካውያን ጎብኚዎች ያለቪዛ መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችታለች።