የቡርኪና ፋሶ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከለክል ህግ አጸደቀ

የቡርኪና ፋሶ የሽግግር ፓርላማ፤ ካቢኔው ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል በሚያደርግ መልኩ የሀገሪቱን ቤተሰብ ህግ ለማሻሻል ያሳለፈውን ውሳኔ በመከተል ይህንን ድርጊት የሚከለክል አዋጅ አጸደቀ።

ሰኞ ዕለት በሙሉ ድምጽ የጸደቀው አዲሱ አዋጅ የተመሳሳይ ጾታን ግንኙነት ውስጥ የተገኙ ሰዎችን እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ ደንግጓል።

የቡርኪና ፋሶ ሕግ የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ እየወሰዱት ያለው ሰፊ እርምጃ አንድ አካል ሆኖ ተቆጥሯል።

የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር ኤዳሶ ሮድሪጌ ባያላ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መሰጡት መግለጫ፤ "ሕጉ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲሁም የገንዘብ ቅጣት" እንደሚጥል አስታውቀዋል።

ሕጉን ሲጥሱ የተያዙ የውጭ ዜጎችም ሀገር እንዲወጡ ሊደረግ እንደሚችልም ተናግረዋል።

ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠበቀው ቀጣይ ሂደት የሀገሪቱ ወታደራዊ መሪ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ ፊርማ እንደሆነ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ካፒቴን ትራኦሬ በአውሮፓውያኑ 2022 የሀገሪቱን ሥልጣን የተቆጣጠሩት የቀድሞውን ወታደራዊ መሪ ሌተናል ኰሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባን ከሥልጣን አስወግደው ነው።

ከሳህል ሀገራት አንዷ የሆነችው ቡርኪና ፋሶ ከዚህ ቀደም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ከፈቀዱ 22 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ነበረች።

ከ54ቱ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ በተወሰኑት ውስጥ ይህ አይነቱ ድርጊት በሞት ወይም ለረጅም ዓመታት በሚቆይ እስር ያስቀጣል።

በ1960 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ያገኘቸው ቡርኪና ፋሶ በብሪታንያ ቅኝ እንደተገዙ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ፀረ ተመሳሳይ ጾታ አፍሪቃሪያን የሆኑ ህጎችን አላወጣችም ነበር።

የሀገሪቱ ህዝብ ወግ አጥባቂ እና ሃይማኖተኛ ሲሆን የትኛውንም እምነት የማይከተሉ የቡርኪና ፋሶ ዜጎች ቁጥር ከአጠቃላዩ የህዝብ ብዛት ከ10 በመቶ በታች ነው።

አዲሱ የቡርኪና ፋሶ ሕግ በመላው አህጉሪቱ እየጨመረ የመጣው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ የሚወሰድ እርምጃ የሚያስቀጥል ነው።

ባለፈው ዓመት የቡርኪና ፋሶ አጋር የሆነችው እና በመንግሥት ግልበጣ ወደ ስልጣን በወጣ ወታደራዊ ቡድን የምትተዳደረው ጎረቤት ሀገር ማሊም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርግ ሕግ አውጥታለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፀረ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አቋማቸውን ያጠናከሩ አገራት ከፍተኛ ተቃውሞና ትችት እያጋጠማቸው ነው።

የዓለም ባንክ ኡጋንዳ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርግ ህግ ማውጣቷን ተከትሎ ለሀገሪቱ የሚሰጠው ብድር ላይ እገዳ እንደጣለ ይታወሳል።

ኋላ ላይ ግን እገዳው እንዲነሳ ተደርጓል።

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከለክሉ ህጎችን ካፀደቁ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ሌላኛዋ ናይጄሪያ ናት። የጋና ፓርላማም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ አዋጅ ቢያፀድቅም በወቅቱ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሕጉ ላይ አልፈረሙም።

ከሁሉም ሃገራት መካከል እጅግ ከባድ የሆኑ ቅጣቶችን ያወጣቸው ኡጋንዳ ነች።

ኡጋንዳ ህጻናት እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ባሳተፈ የተመሳሳይ ጾታ ድርጊት ውስጥ የተገኙ ሰዎችን በሞት ትቀጣለች።

በስምምነት ላይ የተመሰረተ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውስጥ የተገኙ ሰዎች ደግሞ ዕድሜ ልክ እስራት ይፈረድባቸዋል።