ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አነጋጋሪዎቹን ምስጢራዊ ሰነዶች ‘ያሾለከው’ አሜሪካዊ የአየር ኃይል አባል ክስ ተመሰረተበት
ምስጢራዊ የመረጃ እና የመከላከያ ሰነዶችን አሾልኮ አውጥቷል የተባለው አሜሪካዊው የአየር ኃይል አባል ክስ ተመሰረተበት።
የ21 ዓመቱ ጃክ ቴሼራ ቦስተን በሚገኘው ፍርድ ቤት አርብ ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም. ሲቀርብ እጆቹ በካቴና ታስሮ እና የማረሚያ ቤት የመለያ ልብስ ለብሶ ነበር።
በዕለቱ ችሎት ላይም በፍርድ ቤቱ ውስጥ “እወድሃለሁ ጃክ” የሚል ድምጽ የተሰማ ሲሆን፣ ተከሳሹም “እኔም እወድሃለሁ አባቴ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ጃክ ቴሼራ ምስጢራዊ እና ያልተፈቀደለትን የመከላከያ መረጃን በማውጣት ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 15 ዓመት የሚዘልቅ እስር ይጠብቀዋል።
በተጫማሪም ምስጢራዊ ሰነዶች እና መረጃዎችንም ሕጉ ሳይፈቅድለት በመያዝ ክስም ይጠብቀዋል።
ሰነዶችን አሾልኮ በማውጣት ክስ እስከ 10 ዓመት የሚቆይ እስር እንዲሁም ያልተፈቀደለትን መረጃዎችን በመያዝ ደግሞ አምስት ዓመት በድምሩ የ15 ዓመት እስር እንደሚጠብቀው ነው የተገለጸው።
ከሰሞኑ ከፔንታገን በደርዘን የሚቆጠሩ ሾልከው የወጡ ሰነዶች የዩክሬንን ጦርነትን አስመልክቶ አሜሪካ ያላት ግምገማ እንዲሁም አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት እና የምታደርጋቸውን ስለላዎች ይፋ አድርገዋል።
እነዚህ ያፈተለኩ መረጃዎች አሜሪካንን ያሳፈሩ ሲሆን፣ በአገሪቱ ምስጢራዊ መረጃዎች አጠባባቅ እና ደኅንነት ላይም ጥያቄዎችን አስነስተዋል።
ጃክ ቴሼራ ሐሙስ ዕለት ማሳቹሴትስ በሚገኘው የወላጆቹ ቤት እያለ ነበር በታጠቁ የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ወኪሎች በቁጥጥር ስር የዋለው።
ጃክ ቴሼራ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የሕግ አስከባሪ አካላት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ መረጃዎቹን በሚያሾልከው ምንጭ ላይ ለመድረስ ያደረጉትን ምርመራ አድንቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ለወደፊቱም ምስጢራዊ መረጃዎችን ለመጠበቅ እና እንዳይወጡ ለማድረግ የአሜሪካ ጦር እና የስለላ ድርጅት ጥብቅ መመሪያ ማስተላለፉን ተናግረዋል።
ሾልኮ የወጣው መረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ዲስኮርድ በተሰኘው መልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ሲሆን፣ ይህንንም ጃክ በበላይነት ይቆጣጠር ነበር ተብሏል። የዲስኮርድ አባላት አብዛኛውን ጊዜ ስለ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እና ጦርነቶች ይወያያሉ።
የኤፍቢአይ ልዩ ወኪል ፓትሪክ ሉኬንሆፍ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምስክርነት ተጠርጣሪው እነዚህን ምስጢራዊ ሰነዶች በታኅሣሥ ወር መለጠፍ እንደጀመረ ተናግረዋል።
የመጀመሪያዎቹ መረጃዎች ጽሁፎች የነበሩ ሲሆን፣ በኋላ ግን ፎቶግራፎችንም ማውጣት እና መለጠፍ መጀመሩን ተናግረዋል።
የፔንታገን ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ የተረዱትም ከዚህ መተግበሪያ ውጭ መረጃዎቹ በመለጠፋቸው ነበር።
ጃክ የማሳቹሴትስ የአየር ኃይል ብሔራዊ ዘብ የደኅንነት ክንፍ ባልደረባ ሲሆን፣ የሥራ ድርሻውም የአሜሪካ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ኮሚዩኒኬሽን ነበር።