የተሰወረችው ‘የክሪፕቶ ንግሥት’ ቢልየነሮችን እና ልዑላንን እንዴት 3.2 ቢሊዮን ዶላር አጭበረበረች?

የክሪፕቶከረንሲ ዋጋ አሽቆልቁሏል። ገበያውም እጅግ እየተናጠ ነው።

የዲጂታል መገበያያዎች ዋጋ መቀነስ ገንዘባቸውን ካሳጣቸው አንዷ ደግሞ ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ናት።

ስለ ክሪፕቶከረንሲዎች በቅርበት ለሚከታተል ሰው ይሄ ስም አዲስ አይደለም።

በመላው ዓለም እጅግ አነጋጋሪ ከሆኑ መካከል ዶ/ር ሩጃ ትጠቀሳለች።

ዶ/ር ሩጃ 'ዋንኮይን' በተባለ ክሪፕቶከረንሲዋ ዓለም አቀፍ ዝናን አትርፋ ነበር። ቢልየነሮች በክሪፕቶከረንሲዋ ላይ ሃብታቸውን እንዲያፈሱ አሳምናም ነበር።

ኋላ ላይ ግን ዶ/ር ሩጃ አጭበርባሪ እንደሆነች ተደረሰባት።

ዛሬ በአሜሪካው የፌደራል የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ በጥብቅ ከሚፈለጉ 10 ወንጀለኞች አንዷ ናት።

ዶ/ር ሩጃን አገራት ለዓመታት በእግር በፈረስ ቢያፈላልጓትም ከ2017 ወዲህ የት እንዳለች አልተደረሰባትም።

በማጭበርበር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀሎች አሁንም ትፈለጋለች።

ከገንዘብ ማጭበርበር ጋር በተገናኘ ምናልባትም በዚህ ክፍለ ዘመን እንደ ዶ/ር ሩጃ የተወራለት ሰው አይኖር ይሆናል።

ዶ/ር ሩጃ የታዋቂው ዩኒቨርስቲ ኦክስፎርድ ምሩቅ ናት።

ከመላው ዓለም ቢልየነሮችን በክሪፕቶከረንሲዋ ማሳመን ችላለች።

ቢልየነሮቹ ገንዘባቸውን ካፈሰሱ በኋላ ግን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደተቀናቃኝ ክሪፕቶከረንሲ አስተላልፋ ተሰውራለች።

ከዱባይ ፍርድ ቤት ሾልኮ በወጣ ሰነድ ላይ አንድ ጠበቃ ዶ/ር ሩጃን “በታሪክ እጅግ ስኬታማዋ ወንጀለኛ” ብሏታል።

ከሰሞኑ ‘The Missing Cryptoqueen’ ወይም የተሰወረችው የክሪፕቶ ንግሥት በሚል መጽሐፍ ታትሟል።

ቢቢሲም እንዴት እንደተሰወች የሚያትት ተከታታይ ዝግጅት አቅርቧል።

የዱባይ ሰነዶች

ከዱባይ ፍርድ ቤት ሾልከው ከወጡት ሰነዶች መካከል የተወሰኑትን ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን ማጣራት ችሏል።

እነዚህ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፣ ዱባይ ዋነኛው የዶ/ር ሩጃ ገንዘብ ማስተላለፊያ አገር ነበረች።

ኤፍቢአይ ከዶ/ር ሩጃ ጋር ቅርበት ከነበራቸው አምስት አገራት አንዱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መሆኗን ገልጿል።

ሰነዱን አሹልኮ ያወጣው ጠበቃ ዶ/ር ጆናታን ሌቪ “በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች መሰወራቸውን የሚያሳይ መረጃ ነው” ይላል።

'ዋንኮይን' በተባለው የዶ/ር ሩጃ ክሪፕቶከረንሲ ምክንያት ገንዘብ ያጡ ሰዎች ጉዳያቸውን በሕንድ ውቅያኖስ ወደሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ግዛት ፍርድ ቤት ወስደዋል።

በታንዛኒያ እና ኢንዶኔዥያ መካከል የሚገኘው የዩኬ የሕንድ ውቅያኖስ ግዛት፣ የዋንኮይን የበይነ መረብ መረጃ ማከማቻ ዋና ማዕከል (web domain) የሚገኝበት ነበር።

ካሳ ጠያቂዎች ክሱን ወደዚህ ግዛት የወሰዱትም ለዚህ ነው።

ጠበቃው ዶ/ር ጆናታን እንደሚለው፣ በአብዛኛው በአረብኛ የተጻፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ደርሰውታል።

የቢትኮይን ስምምነት

የሃብታም ነጋዴ ልጁ ሼኽ ሳዑድ ከቢትኮይን ጋር ስምምነት መፈጸሙን ጠበቃው ያገኘው ሰነድ ይጠቁማል።

እአአ በ2015 ሼኽ ሳዑድ፣ 230,000 ቢትኮይኖች የያዘ ሜሞሪ ስቲክ ለዶ/ር ሩጃ መስጠቱ ተገልጿል።

እነዚህ ቢትኮይኖች በወቅቱ 48.5 ሚሊዮን ዩሮ ያወጣሉ።

ዶ/ር ሩጃ በምላሹ 50 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ በሦስት የማሻረቅ ባንክ ቼክ ለሼኽ ሳዑድ ሰጥታለች።

ይህ ስምምነት ተፈጽሟል ከመባሉ በፊት የዱባዩ ማሻረቅ ባንክ የዶ/ር ሩጃን የሒሳብ ቁጥር ዘግቷል።

የሒሳብ ቁጥሯ የተዘጋው ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር የማስገባት ሙከራ ተደርጓል በሚል ነው።

የሒሳብ ቁጥሯ በመዘጋቱ ምክንያት ለሼኽ ሳዑድ የሰጠችውን የማሻረቅ ባንክ ቼክ ይዞ ገንዘብ መውሰድ አልተቻለም።

በ2020 የዱባይ ባለሥልጣኖች የዶ/ር ሩጃ ገንዘብ ላይ የጣሉትን ዕቀባ አንስተዋል።

ወቅቱ ዋንኮይን ሐሰተኛ ክሪፕቶከረንሲ ነው ተብሎ በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት የተፈረጀበት ነበር።

ከዚህ ውሳኔ በፊት የቀድሞው የዶ/ር ሩጃ ሀብት ኃላፊ ማርክ ስኮት በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሕገ ወጥ ገንዘብን በዋንኮይን አማካይነት ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ተፈርዶበታል።

ቢቢሲ ለምን የዶ/ር ሩጃ የዱባይ የሒሳብ ቁጥር ዕገዳ እንደተነሳ የአገሪቱን ዐቃቤ ሕግ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

በ2022 በተገኘ የዱባይ ፍርድ ቤት ሰነድ መሠረት፣ ሼኽ ሳዑድ የዶ/ር ሩጃ ፈንድ ይገባኛል ጥያቄ አንስቷል።

ሼኽ ሳዑድ ይህንን ጥያቄ ባቀረበበት ወቅት ዶ/ር ሩጃ ከሕዝብ ዕይታ ተሰውራ ነበር።

ዶ/ር ሩጃ እና ሼኹ

ሼኽ ሳዑድ እምብዛም በአደባባይ ስለማይታይ ስለሱ መረጃ ማግኘት ያስቸግራል።

2017 ላይ ‘ኢንተርገቨርመንታል ኮላቦሬቲቭ አክሽን ፈንድ ፎር ኤክሰለንስ’ በሚል ተቋም የትምህርት ጥራትን ለመደገፍ እንደሚሠራ የሚጠቁም ተንቃሳቃሽ ምሥል ላይ ታይቷል።

የዱባይ ሰነዶች ሾልከው ከወጡ በኋላ ግን ከተቋሙ ድረ ገጽ ላይ “ሼኽ አል ቃሲሚ የተቋሙ ዋና ጸሐፊ ናቸው” የሚለው ጠፍቷል።

ሼኽ ፈይሰል ቢን ሱልጣን ቢል ሳልማን አል ቃሲሚ፣ የሼኽ ሳዑድ አባት ናቸው።

ከሰሞኑ የተጀመረ አንድ ክሪፕቶከረንሲ ሼኹ “ዋና ኃላፊ ነው” ይላል።

ዶ/ር ሩጃ ከሼኽ ፈይሰል ቢን ሱልጣን ቢል ሳልማን አል ቃሲሚ ቤተሰብ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበራት የዱባይ ሰነዶች ይጠቁማሉ።

በ2015 ማሻረቅ ባንክ ለዶ/ር ሩጃ በጻፈው ደብዳቤ፣ የሒሳብ ቁጥሯን እንደሚዘጋው አስታውቋል።

ከ11 ቀናት በኋላ በአሜሪካ ፍርድ ቤት የቀረበ ኢሜል እንደሚጠቁመው፣ ዶ/ር ሩጃ ለአንድ የዋንኮይን የሥራ አጋሯ ከማሻረቅ ባንክ 50 ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ጽፋለች።

“ከአንድ የዱባይ ሼኽ ጋር እየተነጋገርኩ ነው። ለተቋማችን የሚጠቅም ንግግር ነው” ብላም ለሥራ ባልደረባዋ ኢሜይል ልካለች።

በኢሜይሏ የጠቀሰችው የትኛውን የዱባይ ልዑል እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለም።

ዶ/ር ሩጃ ከሼኽ አል ቃሲሚ ጋር የተነሳችው ፎቶም ተገኝቷል።

ቤተሰቡ ከዶ/ር ሩጃ ጋር ስላለው ግንኙነት ዝርዝር መረጃ ቢቢሲ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የአል ቃሲሚ ቤተሰብ በዱባይ እና ራስ አል ካሚሃ ድንበር ላይ የሚገኘውን ሻራጃን ያስተዳድራል።

የዱባይ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት ዶ/ር ሩጃ፣ የትምህርት ጥራት ላይ ይሠራል በተባለው ተቋም ውስጥ “ልዩ አማካሪ” ተብላለች።

ተቋሙ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ትስስር አለው ይባላል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ በበኩላቸው ይህ ተቋም ከድርጅቱ ጋር በመደበኛ መንገድ ትስስር እንደነበረው የሚጠቁም ሰነድ አልተገኘም።

ዶ/ር ሩጃ የዲፕሎማቲክ ማለፊያ መታወቂያ እንደነበራት ተደርሶበታል።

የተቋሙ አጋር መሥራች ሻሪር ራሂሞ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ግንኙነት አለን ቢልም ማስረጃ አላቀረበም።

ዶ/ር ሩጃ እና ሼኽ ሳዑድ የቢትኮይን ስምምነት ካደረጉ በኋላ ግንኙነታቸው እንደሻከረ ይታመናል።

አንድ ደብዳቤ ሼኽ ሳዑድ ዶ/ር ሩጃን ከተቋሙ አምባሳደርነት ማንሳታቸውን ይጠቁማል።

ኋላ ላይ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል የፍርድ ቤት ክስ ተመሥርቷል።

ሼኽ ሳዑድ በተቋሙ ውስጥ ስለነበረው ሚና እንዲሁም ከዶ/ር ሩጃ ጋር ስለነራቸው ግንኙነት ከቢቢሲ ለቀረበት ጥያቄ አልመለሰም።

ነገር ግን “ያላቸው መረጃ በአጠቃላይ መሠረተ ቢስ ነው” ብሏል።

በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ተካሄደ የተባለው የቢትኮይን ግዢ በስውር የልውውጥ መንገድ (cold-storage wallets) ስለተፈጸመ ለማጣራት አስቸጋሪ ነው።

ዶ/ር ሩጃ አሁንም ድረስ ይህ ቢትኮይን እጇ ላይ ከሆነ በቀላሉ ልታዘዋውረው አትችልም።

ምክንያቱም በአብዛኛው የቢትኮይን ልውውጦች ለሕዝብ ይፋ በሆነ መንገድ ነው የሚከናወኑት።

ክሪፕቶ የተባለ መጽሐፍ ያሳተመው ዴቪድ ብሪክ እንደሚለው፣ ቢትኮይን “ስውር ገንዘብ መለዋወጫ” መባሉ የተሳሳተ ነው።

የቢትኮይን ልውውጥን የሚከታተሉ የኮምፒውተር ቀመሮች (algorithms) እንዳሉም ያስረዳል።

“ጥቂት ቢልዮን ዶላሮች በቀላሉ ሊዘዋወሩ ይችላሉ ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል” ይላል ጸሐፊው።

ዶ/ር ሩጃ አሁንም ድረስ 230,000 ቢትኮይኖች እጇ ላይ ከሆኑ፣ ከፍተኛዋ የቢትኮይን ባለቤት ያደርጋታል።

በዚህም በ2021 የቢትኮይን ድርሻዋ ወደ 15 ቢሊዮን ያድግ ነበር ማለት ሲሆን፣ አሁን ባለው የቢትኮይን ዋጋ ማሽቆልቆል የተነሳ ድርሻዋ ወደ 5 ቢሊዮን ይወርዳል።

ዞሮ ዞሮ 5 ቢሊዮን ዶላር ተሰውራ ባለችበት እንድትቆይ የሚበቃ ገንዘብ ነው።