አሜሪካ ከናይጄሪያ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የቪዛ ዕገዳ ጣለች

የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ በናይጄሪያ የሚካሄደውን ምርጫ “ዴሞክራሲያዊ ሂደት እያደናቀፉ ነው” ባለቻቸው በስም ባልተጠቀሱ የአገሪቱ ዜጎች ላይ የቪዛ ዕገዳ መጣሏን አስታወቀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ይህ በተወሰኑ የናይጄሪያ ዜጎች ላይ የተጣለውን ዕገዳ መንግሥታቸው ናይጄሪያ ለመደገፍ ያለውን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።

እርምጃው “ናይጄሪያውያን ሙስናን ለመዋጋት፣ ዴሞክራሲን ለማጠናከር እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ለመደገፍ አሜሪካ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል” ብለዋል።

አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት ስለተወሰደው እርምጃ ሲያብራሩ ዕገዳው የተጣለባቸው ግለሰቦች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ክልከላ ተጥሎባቸዋል።

“በናይጄሪያ የዴሞክራሲ ሂደትን በማደናቀፍ ተሳትፈዋል ወይም ተባብረዋል ተብለው የታመኑ በሚለው ፖሊሲ መሠረት ቪዛ አይሰጣቸውም” ብለዋል።

ዲፕሎማቱ ጨምረውም ዕገዳው በግለሰቦቹ ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንም ሊያካትት ይችላል።

በተጨማሪም ውሳኔው አሁን ዕገዳ በተጣለባቸው ሰዎች ላይ የሚያበቃ እንዳልሆነ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

“በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ወቅት እና ከምርጫው በኋላ በናይጄሪያ የዲሞክራሲ ሂደትን በማደናቀፍ ተሳትፈዋል የሚባሉ ግለሰቦች በዕገዳው ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።”

አንቶኒ ብሊንከን እርምጃውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የመንግሥታቸው የቪዛ ዕገዳ ኢላማ ያደረገው የናይጄሪያ ሕዝብን ወይም መንግሥትን አይደለም ብለዋል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት የቪዛ ዕቀባ እርምጃ ይፋ የሆነው በናይጄሪያ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ሮልፍ ኦልሰን ተመሳሳይ ሃሳብ ከሰነዘሩ ከሁለት ወራት በኋላ ነው።

ባለፈው መስከረም እና ጥቅምት ወር ላይ በኤዶ እና ኦንዶ ግዛቶች የተካሄደው የገዢዎች ምርጫ በተቃረበበት ጊዜ፣ የአሜሪካ መንግሥት ተመሳሳይ የቪዛ ዕቀባ በአንዳንድ ሰዎች ላይ መጣሉን አሳውቆ ነበር።

በመጪው የካቲት ወር አጋማሽ ላይ በናይጄሪያ አጠቃላይ ምርጫ ይካሄዳል ተብሏል።