ሁለት ተጫዋቾችን ከጀርመን ያስፈረመው ዩናይትድ የብራይተን አጥቂን ሊወስድ ይችላል ተባለ

ትናንት በኮሚኒቲ ሺልድ የዋንጫ ጨዋታ በማንቸስተር ሲቲ የተሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ፣ የብራይተን አጥቂ ኤቫን ፈርጉሰንን ሊያስፈርም ይችላል ተባለ።

ደይሊ ስታር ጋዜጣ ዛሬ እንዳስነበበው ዩናይትድ የ19 ዓመቱን የብራይተን አጥቂ በ50 ሚሊዮን ፓወንድ ወጪ ለማዘዋወር አማራጩን እያጤነ ነው።

ዴይሊ ስታር ቼልሲ ሌላኛው የኤቫን ፈርጉሰን ፈላጊ ነው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ከባየር ሙኒክ ማቲያስ ዴ ሊክት እና ኑሴር ማዝራዊ ለማዘዋወር መስማማቱን ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።

ዩናይትድ ለሁለቱ ተከላካዮች በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን ፓዎንድ ይከፍላል።

ማንቸስተር ኢቪኒንግ ኒውስ ደግሞ ዩናይትድ እንግሊዛዊው የቀኝ ተመላላሹን አሮን ዋን-ቢሳካን በ5.6 ሚሊዮን ፓዎንድ ለዌስት ሃም ሽጧል ሲል ዘግቧል።

የዩናይትድ አማካይ ካሰሚሮ ወደ ሳዑዲ ሊያቀና ይችላል ያለው ደግሞ ሜትሮ ነው። ምንም እንኳ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ብራዚላዊው የ32 ዓመት አማካይ በዩናይትድ ይቆያል ቢሉም፤ ካሰሚሮ በዚህ የውድድር ዘመን ከዩናይትድ ሊለያይ ይችላል ተብሏል።

ሌላኛው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ አስተን ቪላ ፖርቹጋላዊውን ጃኦ ፌሊክስ ከአትሌቲኮ ማድሪድ የማምጣት ፍላጎት አለው ተብሏል።

ሚረር በዘገባው እንዳለው አትሌቲኮ ማድሪክ የ24 ዓመቱን አጥቂ አሳልፎ የሚሰጠው የሚጠይቀውን ከፍ ያለ ገንዘብ ከቪላ የሚያገኝ ከሆነ ብቻ ነው ብሏል።

ፔድሮ ኔቶን በ54 ሚሊዮን ፓዎንድ የሸጡት ዎልቭሶች ፤ ፋቢዮ ሲልቫን እንዲሁ በ17 ሚሊዮን ፓዎንድ ለመሸጥ ዝግጁ መሆናቸው ተዘግቧል።

ቲምቶክ የተባለው ድረ-ገጽ ኢስፓኞል፣ ጂኖአ፣ ቫሌንሺያ እና ዎልፍስበርግ የ22 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ፈላጊ ክለቦች ናቸው።

ቦርንመዝ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ በሆነ ገንዘብ አጥቂውን ሶላንኬን ለሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተነሃም ሽጧል። ሰፐርስ 65 ሚሊዮን ፓዎንድ በሚድርስ ገንዘብ ሶላንኬን በስድስት ዓመት ውል አስፈርሟል።

የሊቨርፑሉ ፋቢኦ ካርቫላህ የለንደኑን ክለብ ብሬንትፎርድን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

ጣሊያናዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ አማካይ አጥቂው ተጫዋች ንቦቹን ለመቀላቀል ከስምምነት መድረሱን ገልጾ ሊቨርፑል እንዲሁ 20 ሚሊዮን ፓዎንድ ይቀበላል ብሏል።