የቫግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መጨረሻ ምን ይሆን?

የቭገኒ ፕሪጎዢን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰኔ 24/2023 ቅጥረኛው የቫግነር ቡድን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የሩስያዋን ሮስቶቭ-ኦን-ዶን በቁጥጥር ሥር አዋለ።

ጥቂት ቆይቶ እስከ አፍንጫው ታጥቆ ወደ ሞስኮው ይገሰግስ ጀመር። በመንገዱም የሩሲያ አውሮፕላኖች መትቶ ጣለ።

ምንም እንኳ የቫግነር መሪ የቭገኒ ፕሪጎዢን ዓላማችን መፈንቅለ መንግሥት አይደለም ይበል እንጂ አመፁ ለፑቲን አስተዳደር ከባድ አደጋን የጣለ ነበር።

ይህ ወታደራዊ አመፅ የኒውክሌር ባለቤቷ ሩሲያን ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ሊወስዳት ይችል ነበር።

ቫግነር፤ ዩክሬን ውስጥ ስኬታማ ወታደራዊ ኃይል ነበር። ከእሥር ቤት የመጡና ልምድ ያላቸው ወታደሮች የተውጣጡበት ቫግነር ለአባላቱ ከመንግሥት ወታደሮች የተሻለ ክፍያ ይፈፅማል።

ፑቲን ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንታ መንገድ ላይ ቆመዋል።

ቫግነር ወታደራዊ አመፅ መጥራቱ ወደፊት የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ማሳያ ነው። ወዲህ ደግሞ ይህ ቅጥረኛ ቡድን በዩክሬና በክሬምሊን ጠቀሜታው ሲቸር ቆይቷል።

ቅጥረኛው ቡድን ወደ ሊቢያ፣ ሶሪያና በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ተሰማርቶ የሩሲያን ስትራቴጂክ ጫና ሲያስፋፋ ቆይቷል።

ነገር ግን ይህ ቅጥረኛ ቡድን ምንም ቢሆን ከክሬምሊን ጋር ግንኙነት እንዳለው ይፋ አያደርግም።

በቅርቡ ፑቲን ቅጥረኛው የቫግነር ቡድን በመንግሥት ቢሊዮን ዶላሮች የሚደገፍ ቡድን መሆኑን አምነዋል።

የከሸፈውን ወታደራዊ አመፅ ተከትሎ፤ ክሬምሊን የቫግነር ወታደሮች በመንግሥት ደመወዝ እንዲካተቱ እስከ ፈረንጆቹ ሐምሌ 1 ድረስ ጊዜ ገደብ ሰጥቷል።

ይህን አናደርግም ካሉ ደግሞ ወደቤታቸው፣ አሊያም ወደ ቤላሩስ ማምራት እንዲችሉ ፈቅዷል።

ፕሪጎዢን የት ነው ያለው?

ፕሪጎዥኒን እንደጫነች የታመነች አንዲት አውሮፕላን በያዝነው ሳምንት ወደ ቤላሩስ ዋና ከተማ ሚንስክ አቅንታለች።

የቤላሩሱ መሪ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የቫግነሩ መሪ ሚኒስክ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።

ነገር ግን ይህች አውሮፕላን ሴይንት ፒተርስበርግ ቆማ ወደ ሞስኮው ተመልሳለች።

ሰውዬው አሁን የት ነው ያለው? የቫግነር ቅጥረኛ ቡድንን ከቤላሩስ ሆኖ ይመራል ወይ? ምንም እንኳ የቀድሞው አለቃው ፑቲንን ቢክድም።

አሁንም ለሩሲያ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ፑቲን ለሰውዬው ይቅርታ ያደርጉለታል፤ አሊያም ያምኑታል ማለት ከባድ ነው።

የቫግነር ወታደሮችስ?

ቫግነር በዩክሬን ያለው ቆይታ ያበቃል ይመስላል። ቢሆንም አንዳንድ የቀድሞ የቫግነር ወታደሮች የሩሲያን ኃይል ተቀላቅለው ወደ ዩክሬን ሊሄዱ ይችላሉ።

የቤላሩሱ መሪ ሉካሼንኮ ለቫግነር ወታደሮች ማረፊያ የሚሆን ቦታ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።

የቫግነር ወታደሮች ቤላሩስ ውስጥ ከአሲፖቪቺ ከተማ 21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ ሊሰፍሩ እንደሚችሉ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ዩክሬን ሰሜናዊ የድንበር ክፍሏን መጠበቅ ግድ ይላታል። የፖላንድ፣ ላትቪያ እና ሉቱዌኒያ ጎረቤት ሃገር ቤላሩስ የሰፈረው ቫግነር ቡድን ሊያስፈራቸው ግድ ይላል።

ምን ያክል የቫግነር ተዋጊዎች ወደ ዩክሬን ይዘምታሉ? ምን ያክሉስ ወደ ቤላሩስ ይሄዳሉ? የትኞቹስ የወታደራዊ ቦታቸውን ይሰቅላሉ? ግልፅ አይደለም።