የቻይና የስለላ ፊኛዎች በእስያ ሰማይ ላይ መታየታቸውን አዳዲስ ምስሎች አሳዩ

ፊኛ
የምስሉ መግለጫ, በታይዋን ሰማይ ላይ የተነሳውና የስለላ ነው ተብሎ የተጠረጠረው የቻይና ፊኛ

በጃፓን እና በታይዋን ላይ የተደረገውን በረራ ጨምሮ የቻይና የስለላ ፊኛ ፕሮግራምን በተመለከተ የወጣ አዲስ መረጃ በቢቢሲ ፓናሮማ ተጋለጠ።

ጃፓን ፊኛዎች በግዛቷ ሲበሩ መመልከቷን ያረጋገጠች ሲሆን፣ ወደፊትም ፊኛዎቹን መትታ ለመጣል መዘጋጀቷን ገልጻለች።

ቻይና ግን በቢቢሲ ለቀረበው መረጃ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠችም።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የቻይና የስለላ ፊኛ በአሜሪካ የባሕር ዳርቻ ላይ ተመትቶ መጣሉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር።

ቻይና ጥር ወር መጨረሻ ላይ በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ሰማይ ላይ የታየው ፊኛ የአየር ሁኔታን ለመሳሰሉ ሳይንሳዊ ምርምር የሚያገለግል የሲቪል የአየር መርከብ መሆኑን ጠቅሳ፣ ያጋጠመው ክስተት ያልታሰበ ነው ብላ ነበር።

በአሜሪካ የስለላ ተቋም (ሲአይኤ) የቀድሞው የምሥራቅ እስያ ተንታኝ የሆኑት ጆን ኩልቨር ይህ የአንድ ጊዜ በረራ ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት ያህል ሲካሄድ የነበረ መሆኑን ለቢቢሲ ፓናሮማ ተናግረዋል።

ተንታኙ ጨምረውም “የቻይና ፊኛ በተለየ የሚሰሩት ለእንዲህ ዓይነት የረጅም ጊዜ ተልዕኮ ነው። እናም አንዳንዶቹ ዓለምን ያሰሱ ይመስላል” ብለዋል።

ቢቢሲ በሳተላይት የተነሱ በርካታ መረጃዎችን ከሚመረምረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) ድርጅት - ሳይንቴቴክ ጋር በመሥራት ፊኛዎቹ ምሥራቅ እስያን ሲያቋርጡ የሚያሳዩ በርካታ ምስሎችን ማግኘት ችሏል።

የድርጅቱ መሥራች የሆኑት ኮሪይ ጃስኮልስኪ እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 2021 አንዲት ፊኛ በጃፓን ሰሜናዊ ክፍል ስታቋርጥ የሚያሳይ መረጃ አግኝተዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ምስሎች ከዚህ ቀደም ይፋ አልተደረጉም።

ጃስኮልስኪ ፊኛው ከሞንጎሊያ በስተደቡብ ከቻይና የተነሳ መሆኑንም ያምናሉ። ቢቢሲ ግን ይህንን ማረጋገጥ አልቻለም።

ባለፈው የካቲት ወር በሰሜናዊ አትላንቲክ ውቅያኖስ ተመትቶ የወደቀው የቻይና ፊኛ ክፍል በአሜሪካውያን ከባሕር ሲወጣ

የፎቶው ባለመብት, TYLER THOMPSON/US NAVY

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው የካቲት ወር በሰሜናዊ አትላንቲክ ውቅያኖስ ተመትቶ የወደቀው የቻይና ፊኛ ክፍል በአሜሪካውያን ከባሕር ሲወጣ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጃፓን የአሜሪካ የቅርብ አጋር ስትሆን ከሌሎች የውጭ አገራት በበለጠ በርካታ የአሜሪካ ኃይሎች በጃፓን ሰፍረው ይገኛሉ።

የጃፓን የመከላከያ ሚኒስቴር ባልደረባ ዩኮ ሙራካሚ፣ መንግሥት በየዕለቱ ያለውን ሁኔታ ለመከታተል ሁሉንም ጥንቃቄዎች እያደረገ እንደሆነ እና በጃፓን ግዛት የሰዎችን ሕይወት እንዲሁም ንብረት ለመጠበቅ ፊኛዎቹን መትቶ እንደሚጥል ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በበኩሉ የቻይና ፊኛዎች የስለላ ሥራ ለመሥራት መረጃ አነፍናፊ መሳሪያ የታጠቁ ናቸው ብሏል።

ጨምሮም በአሜሪካ ሰማይ ላይ ከዚህ ቀደም የተገኘው በራሪ ፊኛ መረጃ ለመሰብሰብ እና መልከአ ምድራዊ ቦታን በተመለከተ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ በርካታ አንቴናዎች እንደነበሩት አስታውሷል።

ቻይና ሌሎች ፊኛዎችን አሰማርታ መሆኑን ለማጣራትም የቢቢሲ ፓናሮማ የምርመራ ቡድን መጀመሪያ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ፣ ከዚያም በቀጠናው ዩፎዎችን (በራሪ አካላትን) የተመለከቱ ዘገባዎችን ተመልክቷል።

በዚህም በ2021 መስከረም ወር መጨረሻ በዋና መዲናዋ ታይፔ ሰማይ ላይ የነበረ ፊኛን የሚያሳዩ እና በታይዋን የአየር ሁኔታ አገልግሎት የተነሱ ሁለት ፎቶግራፎችን አግኝተዋል።

ከዚያም ጃስኮሊስኪ እነዚህን ፎቶግራፎች ከሳተላይት ምስሎች ጋር እንዲያመሳክሩት ተደርጓል።

“በ90 ሰከንድ ውስጥ በታይዋን የባሕር ዳርቻ ፊኛውን ማግኘት ችለናል” ብለዋል ጃስኮሊስኪ።

ከዚህም በተጨማሪ ቢቢሲ ፓናሮማ ከስለላ ፊኛዎቹ እስከ ምስጢራዊ ፖሊስ ጣቢያዎች ጨምሮ ሌሎች መረጃዎችን በመመልከት የቻይናን ዓለም አቀፍ የደኅንነት ዘመቻ ሥራን መርምሯል።

የታይዋን መንግሥት ፊኛው የአየር ሁኔታ መከታተያ ነው ብሎ እንደሚያምን ለቢቢሲ ፓናሮማ ቢገልጽም፣ ጃኮልስኪ ግን በዚህ አይስማሙም።

“የፊኛው መጠን እና የሚበርበት ከፍታ በአሜሪካ እና በጃፓን ላይ ሲንሳፈፍ ከነበረው ፊኛ ጋር የሚመሳሰል ነው” ብለዋል።

ታይዋን እራሷን እንደ ሉዓላዊ አገር የምትመለከት ሲሆን፣ ቻይና ግን የራሷ አማጺ ተገንጣይ ግዛት እንደሆነች እና አስፈላጊ ከሆነ በኃይል እንደምትጠቀልላት ስትገልጽ ቆይታለች።

ባለፈው ዓመትም የቻይና ጦር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ስጋት የፈጠረችባት ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ቻይና ታይዋንን የምታጠቃ ከሆነ አሜሪካ ታይዋንን እንደምትከላከል መናገራቸው ይታወሳል።