ቻይና ወደ ሰማይ እንደላከችው የሚጠረጠር ግዙፍ የስለላ ፊኛ አሜሪካን አሳስቧል

ግዙፍ የስለላ ፊኛ ከርቀት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቻይና እንደሆነ የተገመተው ይህ ግዙፍ ፊኛ ረቡዕ ዕለት በሞንታና ግዛት በረራዎችን አስተጓጉሎ ነበር።

አሜሪካ በሰማይ ላይ እየተንሳፈፈ ነው ያለችው ግዙፍ የስለላ ፊኛ “ክትትል እያደረግንበት ነው” ስትል አስታወቀች።

አሜሪካ ይህ ግዙፍ ፊኛ ምንነት ያሳሰባት የቻይና እንደሆነ ከጠረጠረች በኋላ ነው።

የፔንታገን ባለሥልጣናት እንዳሉት ከሆነ ፊኛው ለስለላ ቅኝት የተላከ ሳይሆን አይቀርም።

ነገሩ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ አሜሪካ ወታደራዊ ምሥጢሮቿ ይገኙበታል በሚባልበት የሞንታና ግዛት ምዕራባዊ ክፍል ፊኛው ቅኝት ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ይህ ፊኛ አውሮፕላኖች ከሚበሩበት ከፍታ በላይ ጫማ እየበረረ በመሆኑ የአየር ጉዞዎችን አላስተጓጎለም።

ይሁንና አሜሪካ ፊኛውን መትቶ ለመጣል ፍላጎት አላሳየችም፤ ምክንያቱም ውስጡ ምን እንዳለና ስብርባሪ ሰዎች ላይ አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ነው።

ቻይና በጉዳዩ ላይ ለጊዜው ያለችው ነገር የለም።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዚህ ፊኛ ጉዳይ ላይ የደኅንነት አማካሪዎቻቸው ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

ይህ ግዙፍ ፊኛ ሞንታና ግዛት ሰማይ ላይ ከመታየቱ በፊት በአላስካና ካናዳ ሰማዮች አንዣቧል ብለዋል የፔንታገን ባለሥልጣናት።

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ የአሜሪካ መከላከያ ከፍተኛ ባለሥልጣን የአሜሪካ መንግሥት ለጥንቃቄ በሚል ተዋጊ ጄቶችን በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆኑ አዟል። ከጄቶቹ መሀል ዘመናዊዎቹ ኤፍ-22 የተሰኙት ይገኙበታል።

ጄቶቹ በተጠንቀቅ እንዲሆኑ የተፈለገው ምናልባት ጆ ባይደን ይህ ፊኛ እንዲመታ ትእዛዝ ሊሰጡ ይችላሉ በሚል ነው።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጆርጆ ኦስቲን በጉዳዩ ላይ ረቡዕ ዕለት ፊሊፒንስ ለጉብኝት ከመሄዳቸው በፊት ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።

ይሁንና ፊኛው ተመትቶ እንዲወድቅ የሚለው ሐሳብ ለጊዜው እንዲቆይ ብለዋል።

ጥቂት ሕዝብ ተሰበጣጥሮ ይኖርበታል የሚባለው ሞንታና ግዛት አሜሪካ ካሏት ሦስት የሚሳኤል ማቆያዎች እንዲሁም የማልምስቶርም የአየር ኃይል ጣቢያ መገኛ ነው።

አንድ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጉዳዩን አሜሪካ በዋሺንግተን ዲሲ እና በቤጂንግ ላሉ የቻይና ኤምባሲዎች እንዳነሳች ተናግረዋል።

እኚሁ ባለሥልጣን አንድ አውሮፕላን አብራሪ ይህን ግዙፍ ፊኛ ከተመለከተ በኋላ ሪፖርት ማድረጉን ይህም የሚያሳየው የፊኛውን ግዝፈት እንደሆነ ገልጠዋል።

አሜሪካ ለክፉም ለደጉም ይህ ፊኛ አሁን የት አየር ክልል እንደሚገኝ በትክክል እየተከታተልኩት ነው ብላለች።

የሞንታና ነዋሪዎች ይህን ግዙፍ ፊኛ የሩቅ ምሥል በተራቀቁ ካሜራዎች ያነሱት ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ካጋሩት በኋላ ዩፎ ሳይሆን አይቀርም በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

የሲአይኤ አለቃ የሆኑት ዊሊያም በርንስ ቻይና ከምንጊዜም በላይ የአሜሪካ ጂኦፖለቲካ ተገዳዳሪ እየሆነች መምጣቷን አልካዱም።

ይህ ግዙፍ የስለላ ፊኛ ጉዳይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊከን ከሚቀጥለው ሳምንት በቻይና የሚያደርጉትን ጉብኝት ጥላ እንዳያጠላበት ተሰግቷል።

ብሊንከን ከቻይናው ሺ ዢንፒንግ ጋር ተገናኝተው በታይዋን ጉዳይ እንዲሁም ኮቪድ-19 ጨምሮ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።