የሳተላይት ምሥሎች እና የዶክተር ምስክርነት በትግራይ ያለውን የረሃብ ቀውስ አመለከቱ

በሰሜን ኢትዮጵያ በድርቅ፣ ሰብል ባለመሰብሰቡ እና ከጦርነቱ በኋላ በቀጠለ አለመረጋጋት ምክንያት ሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱ ተነግሯል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሀብ እንደተጋለጡ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ ቢቢሲ ከሳተላይት ምሥሎች ባጣራው መረጃ መሠረት በትግራይ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እየተከሰተ ነው።

ወርሀ ሐምሌ ለወትሮው የአካባቢው ገበሬ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ ሰብል የሚዘራበት ወሳኝ የሚባል ወቅት ነው።

ከታች በምሥሉ የሚታየው ቆሪር በተሰኘው ሥፍራ የሚገኝ ግድብ እና የውሃ ማጠራቀሚያ ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

ይህ አነስተኛ ሐይቅ ሰው ሠራሽ ግድብ ያለው ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2023 የተነሳው ፎቶ ላይ በግልፅ ይታያል። ምሥሉ ላይ እንደሚታው ከግድቡ ጀርባ በታቆረው ውሃ የለማ መስክ አለ።

እንዲህ ያሉ የታቆሩ ግድቦች እስከ 300 አርሶ አደሮች የሚጠቀሟቸው ሲሆን ስንዴ፣ አትክልት እና በክልሉ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ማሽላ ይበቅልበታል።

በምስሉ ላይ እንደሚስተዋለው በሰኔ 2024 ውሃ ማቆሪያው ደርቆ፤ የእርሻ ቦታውም ተራቁቶ ይታያል።

በቂ ዝናብ ካልዘነበ የመስኖ ሥራ ማካሄድ የማይታሰብ ነው፤ የአካባቢው አርሶ አደሮች ደግሞ ከዚህ መስኖ ውጪ መኖር አይችሉም።

“ምንም እንኳን ግድባችን ውሃ ባይኖረውም፤ መሬታችን ግን የትም አይሄድም” ይላሉ ይህን መስኖ ተጠቅመው ቲማቲም፣ ሽንኩርት እና ማሽላ ያመርቱ የነበሩት አርሶ አደር ድምፁ ገብረመድኅን።

“ምንም ቢሆን ተስፋ አንቆርጥም፤ አንድ ቀን ወደ ግብርና ሥራችን እንመለሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”

ምግብ እና ሰላም

የትግራይ ክልል ሕዝብ ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን እንደሚሆን ይገመታል።

እስከ አውሮፓውያኑ 2022 መጨረሻ ድረስ በትግራይ ክልል ኃይሎች እና በፌዴራለ መንግሥት እንዲሁም አጋሮቹ መካከል በተካሄደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ክልሉ መረጋጋት ርቆት ቆይቷል።

በጦርነቱ ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ ሲገመት፣ በረሃብ እና በጤና አገልግሎት እጦር ምክንያት በርካቶች እንደረገፉ ይነገራል።

በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ እና ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ በርካታ ካምፖች ተቋቁመዋል።

አሁን ጦርነቱ ቢቆምም ጥቂት ከሚባሉ ወደ ቀያቸው ከተመለሱ ስደተኞች በቀር በርካቶች ካምፖች ውስጥ መቆየትን መርጠዋል። በክልሉ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት አርሶ አደሮች ሰብል መሰብሰብ ባለመቻላቸው በእርዳታ የሚሰጥ የምግብ አቅርቦት ላይ ጥገኛ ሆነዋል።

ከመጠለያዎቹ መካከል ከቆሪር በስተምዕራብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሽሬ አካባቢው የተቋቋመው ካምፕ አንዱ ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች የተቋቋመው ይህ መጠለያ ከ30 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች እርዳታ ያቀርባል።

በሳተላይት ምሥሉ ላይ የሚታዩት ሰማያዊ መጠለያዎች በዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) የቀረቡ ሲሆኑ፣ ነጭ ቀለም ያላቸው ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) የተተከሉ ናቸው።

ፅብቅተይ ተኽላይ ከአምስት ልጆቿ ጋር በመጠለያ ጣቢያው ትኖራለች። ባለቤቷ በጦርነቱ ምክንያት ተገድሏል።

“እንስሳቶች ነበሩን። በክረምት ወራት ሰብል እንዘራ ነበር” ስትል ባለፈው ግንቦት ለቢቢሲ ተናግራለች። “ብቻ በአጭሩ መልካም የሚባል ሕይወት ነበረን። አሁን ግን ምንም ነገር የለንም።”

ፅብቅተይ በተጠለለችበት ካምፕ ምግብ በማብሰል እና ዳንቴል በመሥራት ገቢ ለማግኘት ትሞክራለች። ልጆቿ ግን ለልመና ተዳረገዋል።

“ቢያንስ መሬቴን አገኛለሁ የሚል ተስፋ አለኝ። መሬታችን ላይ የበቀለ ምግብ መቼም ከእርዳታ ምግብ እጅጉን ይሻላል” ትላለች።

“ወደ ቀያችን መመለስ ከቻልን፤ ልጆቻችን ቢያንስ ሥራ ይሠራሉ፤ አሊያም ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ለዚህ ነው ከዚህ አስከፊ ከሆነ ሕይወት ብንላቀቅ ልጆቻችን የተሻለ ሕይወት ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ የማደርገው።”

መቀንጨር የተጋረጠባቸው ሕፃናት

ከሽሬ ከተማ በስተደቡብ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እንዳባጉና ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል የሚያገለግሉ ዶክተሮች ያደረባቸውን ስጋት ለቢቢሲ ያጋራሉ።

“በተለይ በቅርብ ወራት በርካታ ሕፃናት ለሕክምና ወደ እኛ ይመጣሉ” ይላሉ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ገብረክርስቶስ ግደይ።

ዶክተሩ እንደሚናገሩት አንዲት አበባ የሻለም የተባለች የ20 ዓመት ወጣት በቂ ምግብ ባለማግኘቷ ምክንያት ጊዜዋ ሳይደርስ ለመገላለገል ተገዳለች።

ሆስፒታል ውስጥ ያገኘናት አበባ “ባለቤቴ ለትምህርት ብሎ ሄዷል፤ እኔ ብቻዬን ነኝ፤ በገንዘብም እርዳታ ሊያደርግልኝ አልቻለም። ራሴንም ሆነ ልጄን የምመግበት አቅም የለኝም” ትላለች።

በሆስፒታሉ እርዳታ እያገኙ ከነበሩ በደርዘን የሚቆጠሩ ሕፃናት መካከል ከመጠለያው የመጡ ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያው ከሚገኙ ከተሞች የመጡም ይገኙበታል።

“እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ የምንደርስበት አቅም የለንም” ይላሉ ዶ/ር ገብረክርስቶስ።

ዝናብ ጥበቃ

ክልሉ በጣም ወሳኝ የሚባለው ወቅት ላይ እየደረሰ ነው። ይህ ወቅት “የረሃብ ዘመን” ተብሎ ይጠራል የሚሉት የትግራይ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኃላፊ ዶ/ር ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

ይህ ወቅት ለወትሮው የምግብ አቅርቦት የሚሳሳበት ጊዜ ቢሆንም ገበሬዎች ለጥቅምት ወር ሰብል ስብሰባ ዘራቸውን የሚተክሉበት ነበር።

“2.1 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። 2.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ አስተማማኝ የማይባል የምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው” ሲሉ ኃላፊው ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት በነበረው በቂ ያልሆነ ዝናብ ምክንያት የትግራይ ክልል እና አጎራባቹ የአፋር ክልል በድርቅ ተመትተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ በከባድ ዝናብ ምክንያት የተከሰተ ጎርፍ የእርሻ መሬት እና የጋማ ከብቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።

በአብዛኛው የትግራይ ክልል በጥር እና የካቲት ወራት የጣለው ዝናብ ከሌላው ጊዜ ያነሰ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን በመጋቢት ወር የጣለው ዝናብ የተሻለ ነው።

ፖለቲካዊ ውጥረት

በተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ዎርልድ ፒስ ፋውንዴሽን የተሰኘው ተቋም ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል፤ “ረሃብ በጨለማ እያገጠጠ ነው” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። አክለው ለተከሰተው አደጋ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ይናገራሉ።

“ረሃብ ሰው ሰራሽ ነው። ለዚህ ነው ረሃቡን የፈጠሩት ሰዎች ማስረጃ የሚደብቁት እና ኃላፊነታቸውን የማይቀበሉት” ይላሉ።

ደ ዋል እንደሚሉት ዘንድሮ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በ1984 (እአአ) ከተሰተው እና አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ረሃብ ጋር የሚመሳል ነገር አለው።

“በ1984 የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት የተቀረው ዓለም እንዲያይለት የፈለገው በአብዮቱ ምክንያት የፈነጠቀውን ብልፅግና ነበር። የውጭ የእርዳታ ድርጅቶች ሕፃናት በረሃብ ምክንያት ሲሞቱ የሚያሳይ ምሥል ቢቢሲ ላይ እስኪያዩ ድረስ ረሃብ አለ የሚለውን ማስጠንቀቂያ መቀበል አልሻቱም።”

የእርዳታ ድርጅቶች በዝናብ እጥረት፣ በአለመረጋጋት እና እርዳታ ለማድረስ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ መገመት ችለዋል።

ፊውስ ኔት የተሰኘው የርሃብ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የመረጃ ሥርዓት እንደሚለው የተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች እንዲሁም የትግራይ ጎረቤት የሆኑት የአፋር እና የአማራ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የፌዴራል መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች አሉ የሚባሉ የምግብ አቅርቦት እጥረቶችን በተለመከተ የሚወጡ ሪፖርቶችን አይቀበልም።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት ሽፈራው ተክለማርያም በተደረገ ይፋዊ ማጣራት “በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የረሃብ አደጋ እያንዣበበ ነው የሚለው እውነት አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

አክለው ባለሥልጣናት አገሪቱ ያጋጠማትን ችግር ለመቅረፍ “የተቻላቸውን እያደረጉ ነው” ብለው “አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ” ቅድሚያ እየተሰጠ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለይ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በተራድዖ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት የተቀዛቀዘ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት በጦርነቱ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ የነበረበት የምግብ እርዳታ እንዳይደርስ ተደርጓል የሚል ቅሬታ ሲያሰማ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2021 በትግራይ ክልል ረሃብ ተከስቷል በሚል የወጣውን ሪፖርት መንግሥት ማስተባበሉ የሚታወስ ሲሆን “በአገሪቱ ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገቡ ናቸው” ያላቸውን ሰባት ነባር የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞችን ማባረሩ አይዘነጋም።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ፤ የመንግሥት ኃይሎች እና ሌሎች ታጣቂዎች ሰብዓዊ አቅርቦት እየሰረቁ መሆናቸውን የሚያመለክት መረጃ በማግኘታቸው ለኢትዮጵያ የሚቀርበውን የምግብ እርዳታ አቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።

በእርዳታ ተቋማቱ አማካይነት የሚቀርበው የምግብ እርዳታ ድጋሚ መሠራጨት የተጀመረው ባለፈው ኅዳር ነው።

ባለፈው የካቲት የአገሪቱ እምባ ጠባቂ ተቋም የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በረሃብ ምክንያት 400 ሰዎች ሞተዋል የሚል መረጃ ካወጣ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ውስጥ በረሃብ እየሞቱ ያሉ ሰዎች የሉም” ብለው ነበር።

የዩኤስኤአይዲ ቃል አባይ “አደጋ ላይ ላሉ ሰዎች የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታ እንዲጨምር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የእርዳታ ድርጅቶችን እንጠይቃለን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ዩኤንኦቻ) “አሁን ያለውን ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀልበስ እየቀረበ ያለው እርዳታ በቂ አይደለም” ብሎ፤ ነገር ግን ያለው አቅርቦት “በጣም ለሚያስፈልጋቸው” እየተሰጠ እንዳለ ጠቁሟል።