በደቡብ አፍሪካ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ገዢው ኤኤንሲ እየመራ ነው

የደቡብ አፍሪካ ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከጨቋኙ የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሰስ በኋላ ለሦስት አስርት ዓመታት ደቡብ አፍሪካን ያስተዳደረው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን (ኤኤንሲ) የሚገዳደር ፉክክር የታየበት የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ የመጀመሪያ ውጤት ይፋ ሆነ።

አስካሁን በቆጠራ ከተገኘው ከ22 በመቶዎቹ የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) 44 በመቶውን ድምጽ በማግኘት እየመራ ሲሆን፣ ዲሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) በ25 በመቶ ድምጽ ይከተላል።

ሥር ነቀል ለውጥ በአገሪቱ ሊመጣ ይገባል የሚለው የጁሊየስ ማሌማ ኢኤፍኤፍ 9 በመቶ እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ፓርቲ ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) ደግሞ ስምንት በመቶ በማግኘት ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ግንቦት 21 የተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ ቆጠራ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተጠናቆ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ሆኖም ከምርጫው በፊት የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት አገሪቱን በበላይነት ለ30 ዓመታት የመራው ኤኤንሲ ብቻውን መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን የፓርላማውን አብላጫ ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያጣ እንደሚችል ነው።

በርካታ መራጮች በአገሪቱ ውስጥ ለሰፈነው ከፍተኛ ሙስና፣ ወንጀል እና ሥራ አጥነት ገዢውን ኤኤንሲ ተጠያቂ ያደርጉታል።

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተደማጭነት ያለው የምርምር ተቋም እና ኒውስ24 የተባለው ድረ ገጽ ባወጡት የምርጫ ውጤት ትንበያ ኤኤንሲ ከአጠቃላዩ ምርጫ 42 በመቶ በማግኘት ከዚህ በፊት ከነበረው 57 በመቶ ያሽቆለቁላል ብለዋል።

ይህም ፓርቲው በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ከአንድ ወይም ከበርካታ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት እንዲመሠርት ሊያስገድደው ይችላል።

ዲኤ ነጻ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲን የሚያራምድ ሲሆን፣ ኢኤፍኤፍ እና ኤምኬ ግን መንግሥት የበለጠ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖረው እና ትላልቅ ተቋማት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ይፈልጋሉ። ስለዚህም ኤኤንሲ ጥምረት የሚፈጥር ከሆነ ፓርቲዎቹ ያላቸው አቋም ደቡብ አፍሪካ ወደፊት በምትከተለው አቅጣጫ ላይ ከፍተኛ ልዩነትን ሊያመጣ ይችላል።

ኤኤንሲ ከ45 በመቶ በታች ድምጽ የሚያገኝ ከሆነ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት በፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ላይ ስለመቆየታቸው ግልጽ ያለ ነገር የለም።

በደቡብ አፍሪካ የምርጫ ሥርዓት የአገሪቱ ዜጎች በቀጥታ ፕሬዚዳንቱን አይመርጡም። ከዚያ ይልቅ ግን የምክር ቤት አባላትን በመምረጥ እንደራሴዎቹ ፕሬዚዳንቱን ይመርጣሉ።

የደቡብ አፍሪካ ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ረቡዕ ዕለት በርካታ ረዣዥም ሰልፎች በአገሪቱ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ሲሆን፣ ይህም እስከ ምሽት ድረስ ቀጥሎ ነበር።

እነዚህ ረጃጅም ሰልፎች እና ወረፋዎች በአውሮፓውያኑ 1994 የተደረገውን እና ጥቁር ሕዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ መስጠት የቻሉበትን ታሪካዊ ምርጫ እንደሚያስታውስ በጆሃንስበርግ የሚገኙ አንድ የምርጫ አስፈጻሚ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚያንም ወቅት በተደረገው ምርጫ የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።

የምርጫ ጣቢያዎቹ ከምሽቱ 3፡00 ላይ ሲዘጉ በሺዎች የሚቆጠሩ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት እየተጠባበቁ የነበረ ሲሆን፣ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሁሉም እንዲመርጡ እንደሚደረግ ተናግረው ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ትልቁ የምርጫ ጣቢያ ጆሃንስበርግ ጆበርት ፓርክ ውስጥ ድምጽ የሰጡት ሲፊሶ ቡቴሌዚ “ነፃነት ትልቅ ነው፤ ነገርግን ሙስናን መታገል አለብን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለውጥ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በተለይም በወጣቱ ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሳ ሃሳብ ነው።

ከአናሳው ጨቋኝ ነጭ አገዛዝ መውደቅ በኋለ የተወለዱት ‘ቦርን ፍሪ’ የሚባሉት ትውልዶች አንዱ የሆነው አያንዳ ህሌክዋኔ ሦስት ዲግሪ ቢኖረውም አሁንም ሥራ ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል።

“ምናልባት ሥራ ባላገኝ እንኳን በሚል ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የፒኤችዲ ፕሮፖዛሌን እየሰራሁ ነው” ሲል የደርባን ከተማ ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጿል።

አያንዳ አሁንም አገሪቱ በዚህ ሁኔታ እንደማትቀጥል እና ሁኔታዎች እንደሚቀየሩ ተስፋ ሰንቋል።

በዘንድሮው የአገሪቱ ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 70 ፓርቲዎች እና 11 የግል ተወዳዳሪዎች ለፓርላማ እና ለክልል አስተዳደሮች ተወዳድረዋል።

ይህ የሚያሳየው በርካቶች በኤኤንሲ ተስፋ እንደቆረጡ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

“አገሪቷ ወደ ቀጣዩ የዲሞክራሲ ምዕራፍ እየገባች ነው። እናም ትልቅ ሽግግር ይሆናል” ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ሪቻርድ ካላላንድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በዚህም ወይ ተፎካካሪ እና በሳል ዲሞክራሲ እንሆናለን፤ ያለበለዚያም የበለጠ የተበታተንን እንሆናለን” ሲሉም ተንታኙ አክለዋል።

ዋናው ተቀናቃኝ ተቃዋሚ ፓርቲ ዲሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) ከሌሎች 10 ፓርቲዎች ጋር ስምምነት የፈረመ ሲሆን፣ ኤኤንሲን ከሥልጣን ለማባረር በቂ ድምጽ ካገኙ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት ተስማምቷል።

ነገር ግን ይህ የማይመስል ነገር እንደሆነ ተንታኞች ያስረዳሉ።

ኤኤንሲ ትልቅ ፓርቲ ሆኖ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ ሲሆን፣ ድጋፉ 50 በመቶ በታች ቢወርድ እንኳን ጥምር መንግሥት ለመምራት ትልቅ ስፍራ ይኖረዋል።

ባለፈው ምርጫ ኤኤንሲ 57.5 በመቶ ድምጽ ያገኘ ሲሆን፣ ዲኤ ደግሞ 21 በመቶ አግኝቷል።

ደቡብ አፍሪካውያን በቀጥታ ፕሬዚዳንታቸውን አይመርጡም። ከዚያ ይልቅ የፓርላማ አባላትን የሚመርጡ ሲሆን፣ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው ፓርቲም መንግሥት ይመሠርታል። ስለዚህ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሥልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ።

አርማ