በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 'የሸኔ ታጣቂዎች' ከ40 በላይ ሰዎች መግደላቸውን ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ተናገሩ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሸኔ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሕጻናትና ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን በምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመው ቅዳሜ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም. ነው።

የቡለን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ማሩ በጥቃቱ 36 ሰዎች ስለመገደላቸው መረጃ እንዳላቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ የአካባቢው ሚሊሻ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት 40 ሰዎች መቅበራቸውን እና እሁድ ዕለት ደግሞ ወደ ቡለን ለሕክምና የሄዱ ሁለት ሰዎች ሞተው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከቤንሻንጉል ክልል ቡለን እና ወንበራ ወረዳን የሚያካትተው የሽናሻ ልዩ የምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ ደግሞ ጥቃቱ ቅዳሜ ለሊት 11 ሰዓት ጀምሮ መፈጸሙን እና ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባሉ ዶ/ር መብራቱ ለቢቢሲ ሲናገሩ በኩጂ ቀበሌ ከተማ ላይ ነዋሪዎች "እንቅልፍ ላይ እያሉ ታጣቂዎች ገብተው" ተኩስ መክፈታቸውን እና ነዋሪዎች "ተደናግጠው ሲወጡ እና በተኙበት ያገኟቸው ላይ ግድያ ፈጽመዋል" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በጥቃቱ የቤተሰባቸው አባላት የተገደሉባቸው አንድ ግለሰብ ታጣቂዎቹ 41 ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ሄደው የሞቱትን ጨምሮ ቁጥራቸው ወደ 42 የሚሆኑ ነዋሪዎች በጥቃቱ መገደላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ በኩጂ ከተማ መሃል በመግባት በፈጸሙት ጥቃት "ወደ 40 ሰዎች መገደላቸውን ቆስለው ሆስፒታል ከገቡት ውስጥ የሞቱ መኖራቸውን" መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር መብራቱ አክለውም "31 ሰዎችን አስከሬን ቆጥሬያለሁ ያለ ሰው አናግሬያለሁ" በማለት ሟቾቹ የተገደሉት "በየቤታቸው ደጃፍ ላይ፣ መንገድ ላይ" በተገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው እና ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደፈጸሙት በተነገረው በዚህ ጥቃት "ከአንድ ዓመት ሕጻን ጀምሮ እስከ 80 ዓመት አዛውንት ሴቶች ነፍሰጡሮች" እንደሚገኙበት የምክር ቤት አባሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከ40 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ይህንን ጥቃት በተመለከተ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ሆነ ከፌደራል መንግሥት አስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ጥቃቱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ሸኔ) ታጣቂዎች መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጀው ይህ ታጣቂ ቡድን እስካሁን ድረስ ፈጽሟል ስለተባለው ግድያ እና ስላደረሰው ጥቃት ያለው ነገር የለም።

የቢቢሲ አፋን ኦሮሞ አገልግሎት ከቡድኑ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

'ከእኛ ቤት ብቻ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል'

ኅዳር 13/2018 ዓ.ም. ማለዳ 12 ሰዓት አካባቢ በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት ስምንት የቤተሰቦቻቸው አባላት መገደላቸውን የተናገሩት አንድ የከተማው ነዋሪ "በአንድ መቃብር ውስጥ ሦስትም አራትም ሰዎች" በጋራ መቀበራቸውን ይናገራሉ።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ እና በአካባቢው ለረዥም ጊዜ መኖራቸውን የሚናገሩት እኚህ የቡለን ወረዳ ነዋሪ "ከእኛ ቤት ውስጥ የወንድሜ ሚስት፣ ሁለት ልጆቿ፣ አንጋፋ ወንድማችን የአባታችን ምትክ፣ ልጁን... በሠራተኝነት የሚኖሩ ሁለት በአጠቃላይ ከእኛ ቤት ውስጥ ስምንት ሰው ነው የተገደሉት" ብለዋል።

በአካባቢው በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎች 41 መሆናቸውን እንደሚያውቁ የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ ሟቾቹን የሚቀበሩበት ሬሳ ሳጥን መጥፋቱን በሐዘን ይገልጻሉ።

በአንድ ጉድጓድ "ሦስት ሦስት፣ አራት አራት፣ አምስት አምስት እየሆኑ ነው የተቀበሩት" ሲሉም በጅምላ መቀበራቸውን ያስረዳሉ።

አካባቢው ላይ ስጋት በመኖሩ ምንጊዜም እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ነዋሪው፣ ዕለቱ የጾም መያዣ ዕለት ስለነበር ነዋሪው ወደ ቅርጫ መከፋፈል በሄደበት ወቅት ጥቃቱ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

በጥቃቱ ሕጻናት መገደላቸውን የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ "የታላቅ ወንድማችን የሁለት ዓመት ልጅ፣ የሌላው የወንድሜ ልጅ አንድ ዓመት ከ7 ወር ሌሎች ደግሞ የ14 እና የ15 ዓመት ልጆች ናቸው" ብለዋል።

ጥቃቱን ያደረሰው የሸኔ ቡድን ነው የሚሉት እኚህ ነዋሪ "በተኙበት ቦታ ላይ" ቤታቸውን ሰብረው ገብተው ግድያውን መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ነዋሪ የተፈጸመውን ግድያ "አሰቃቂ" ሲሉ ጠርተው የተገደሉት ሰዎች ቀብር ቅዳሜ ዕለት መፈጸሙን ተናግረዋል።

በቀበሌው ሚሊሻ መሆናቸውን የገለፁ ግለሰብ ደግሞ በጥቃቱ ስለተገደሉ ሰዎች ተጠይቀው ሲመልሱ "ሴት አስራ አምስት፣ ሕጻናት 16፣ አዛውንቶች 4፣ ሚሊሻ 5" በማለት በታጣቂዎቹ የተገደሉትን ሰዎች በፆታ እና በዕድሜ ዘርዝረዋል።

ቅዳሜ ዕለት 40 ሰዎች መቅበራቸውን የተናገሩት እኚህ ነዋሪ፣ እሁድ ዕለት ደግሞ ለተሻለ ሕክምና ወደ ሌላ ስፍራ ከተላኩት መካከል ሁለት ሰዎች ሞተው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በጥቃቱ የሚጠቡት ስድስት ሕጻናት መገደላቸውን ገልጸው፣ በአጠቃላይ ሕጻናት በሚል የመደቧቸው ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች መሆኑን ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹን ለመከላከል ሲታኮሱ ከሞቱ ከአምስት ሚሊሻዎች ውጪ አጠቃላይ የተገደሉት ነዋሪዎች በተኙበት በቤታቸው ሳሉ መሆኑን እኚህ የሚሊሻ አባላት ይናገራሉ።

አክለውም ከሟቾቹ መካከል ነፍሰጡሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢው ሚሊሻ ለቢቢሲ ጥቃቱ ስለደረሰበት ሁኔታ ሲያስረዱ በቀበሌው ማለዳ ላይ ጥበቃ እያደረጉ በነበረበት ወቅት "ባአር የሚባል ወንዝ አለ ወንዙን ተከትለው ለግድብ ተብሎ የተሠራ ቦይ አለ እኛን ወደ ኋላ አስቀርተው በጎን ሾልከው ወደ ውስጥ ገቡ" ሲሉ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የመጡበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ በኋላ ላይ ቆርጠው ካስቀሯቸው የሚሊሻ አባላት ጋር ተኩስ መክፈታቸውን እና በመንደር የሚገኝ የሚሊሻ አባላትም ወጥተው ተኩስ መክፈታቸውን ይናገራሉ።

በኋላ ላይ ወደ አንድ ጎጥ ሰርገው በመግባት ይህንን ግድያ ፈጽመዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ጥቃቱን የፈጸሙት ሸኔዎች ናቸው የሚሉት እኚህ ሚሊሻ፣ ከዚህ በፊትም በአጎራባች ጎዶሬ ቀበሌ ጥቃት በከፈቱበት ወቅት ከጭላንቆ እና ከበኩጂ ሚሊሻዎች ተውጣጥተው በመሄድ መከላከላቸውን ይናገራሉ።

ታጣቂዎቹ ከግድያ ባሻገር ሱቆችን እንዲሁም ከብቶችን ዘርፈው የነበረ ቢሆንም ከቀበሌ ዝቅ ብሎ "ግሽባቦ የሚባል አካባቢ ተኩስ ተከፍቶባቸው" እንስሳቶቹን ጥለው መሄዳቸውን ተናግረዋል።

በ2013 ዓ.ም. በተፈፀመ ጥቃት አካባቢያቸውን ለቅቀው መሄዳቸውን ያስታወሱት ሚሊሻው ከተመለሱ በኋላ ቤት ያልተቃጠለ እና ያልፈረሰበት ወደ ቤቱ ሲገባ ቀሪው ግን በሸራ ውስጥ አንደሚኖር ያናገራሉ።

"እነዚህም ደግሞ አሁንም መጥተው አቃጥለው ሄዱ" ሲሉ ቤቶችም መቃጠላቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን ጥቃት በማንሳት "ወላጅ አልባ ሆነናል" ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ እገልጻሉ።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት እሁድ ዕለት ወደ አካባቢው መግባቱን ጨምረው ተናግረዋል።

"ከሚሊሻ ኃይል በላይ ነው"

ጥቃቱ የደረሰው የክልሉ መንግሥት ሚሊሻዎችን፣ ፖሊስ፣ የአድማ ብተናን አሰማርቶ ቡድኑ ላይ ዘመቻ እያካሄደ ባለበት ወቅት መሆኑን የቡለን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ገልጸዋል።

አካባቢው ሁልጊዜም "በስጋት" ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገሩት የወረዳው አስተዳዳሪ የሸኔ ታጣቂዎች ከወረዳው ቀበሌዎች "በአምስት፣ በሰባት፣ በ10 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ይገኛሉ" ብለዋል።

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ ምንም እንኳ የቡለን ወረዳ ቀበሌዎችን የሸኔ ታጣቂዎች ተቆጣጥረው ባያውቁም በአጎራባች ወረዳዎች ግን ከ4 ቀበሌ እስከ 12 ቀበሌ ድረስ ተቆጣጣረው እንደሚገኙ ተናግርዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር መብራቱ ግን ከዚህ በተለየ የሸኔ ታጣቂዎች በድባጤ፣ በወንበራ እና በቡለን ወረዳዎች ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ የተወሰኑ አካባቢዎች ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳደር አካባቢውን ከሸኔ ስጋት ነጻ ለማድረግ በሚል ዘመቻዎችን በጀመረበት ወቅት በተደረገ ውጊያ ታጣቂዎቹ የበላይነት አግኝተው ግድያዎችን መፈጸማቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ "የጅምላ ጭፍጨፋ" ተፈጽሞ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር መብራቱ ወደ 251 ሰዎች በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸውንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸውን የምክር ቤት አባሉ እና የወረዳው አስተዳዳሪ ቢናገሩም የሸኔ ታጣቂዎች ግን ከአካባቢው ብዙም ርቀው አለመሄዳቸውን ገልጸዋል።

ከጥቃቱ በኋላ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ስፍራው በመድረስ ሁኔታውን እያረጋጋ መሆኑን አቶ ነመራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግድያው በአሰቃቂ ሁኔታ መፈጸሙን የገለፁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ፣የተፈጸመው በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው "ሸኔ" መሆኑንም ተናግረዋል።

በአካባቢው ከስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ የሸኔ ታጣቂዎቹ እንደሚንቀሳቀሱ እና የተወሰኑ ቀበሌዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ዶ/ር መብራቱ ተናግረዋል።

የቡለን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነመራ በቅርቡ የተፈፀመው ጥቃት "ከሚሊሻ ኃይል በላይ" እንደነበር ተናግረዋል።

'የሸኔ' ታጣቂዎች ሚሊሻዎች ከሚይዙት መሳሪያ የተለየ የታጠቁ መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ "ቆመው አይዋጉም። ተኩሰው ይሮጣሉ" በማለት ውጊያው "የደፈጣ" መሆኑን አብራርተዋል።

በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

በአካባቢው በታኅሣሥ 2013 የጉሙዝ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።

ከሰሞኑ ጥቃቱ በፊት የበኩጂ ወረዳ እና ቀበሌ ለክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ኃይል ይላክልን የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበርም ተናግረዋል።

የቡለን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ማሩ ወረዳው 22 ቀበሌዎች እንዳሉ እና የሸኔ ታጣቂዎች እስካሁን ድረስ የትኛውንም ቦታ አለመያዛቸውን ተናግረዋል።

የወረዳው አጎራባች በሆነው ድባጤ ግን ከስምንት እስከ 12 ቀበሌዎች፣ በወንበራ አራት ቀበሌዎች ውስጥ ይገኙ እንደነበር እና በቅርቡ መከላከያ በሸኔ የተያዙ የወንበራ ቀበሌዎችን ነፃ ማውጣቱን ገልጸዋል።

ከአርባ በላይ ሰዎች የተገደሉበት ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ከአስር በላይ የሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹን "በሕገወጥ መንገድ ሀብት ለማካበት ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው" ያሉት አቶ ነመራ፣ በአካባቢው ያለን "ወርቅ እንዘርፋለን፤ ይህ ወርቅ የሚገባው ለእኛ ነው" የሚል አስተሳሰብ ይዘው ይንቀሳቃሳሉ ሲሉ ይከስሷቸዋል።

አክለውም ሕዝቡን "ለማባበል እና ለመያዝ" በአካባቢው የሚኖረው ኦሮሞ "የኢኮኖሚ እና የሥልጣን ተጠቃሚ አይደለም" በሚል እንደሚቀሰቅሱም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ታጣቂዎቹ "መተከል ለእኛ ነው የሚገባው" የሚል የግዛት ማስፋፋት እንቅስቃሴም ያደርጋሉ ብለዋል።

አስተዳዳሪው የቡለን ከተማም ሆነ የአጎራባች ቀበሌዎች ነዋሪዎች ሁሌም "24 ሰዓት" ታጣቂዎች ጥቃት ይፈጽማሉ በሚል በተጠንቀቅ እና በስጋት እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

የአካባቢው አስተዳደርም የሸኔ ታጣቂዎች በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደሚገኙ፣ በዚህም የተነሳ ወረዳውን ከሸኔ ታጣቂዎች ለማጽዳት በሚል ዘመቻዎችን እያካሄዱ እና አሁንም ያንን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከመከላከያ፣ ከፖሊስ፣ ከአድማ ብተና እና ከሚሊሻ የተውጣጣ ኃይል በዘመቻው ላይ ተሳታፊዎች ናቸው ብለዋል።