በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ዛሬ [ረቡዕ ታህሳስ 14/2013] ንጋት ላይ በተፈፀመ ጥቃት ከ90 በላይ ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱ በበኩላቸው ጥቃቱ ስለመፈፀሙ መረጃው እንደሌላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ግን ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጠው የሟቾች ቁጥር እስካሁን ድረስ ባይታወቅም "በጣም ከፍተኛ መሆኑን" ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ተሰማርቶ ሰላም የማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ መለሰ አክለው ተናግረዋል።

ከጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተገኝተው ከመተከል ዞን ነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካባቢውን ወደ ሠላም የመመለሱ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ መናገራቸው ተዘግቦ ነበር።

ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ተከትሎ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቡለን ከተማ ነዋሪ ጥቃቱ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ሌሊት 11 ሰዓት አካባቢ መፈፀም እንደጀመረ ገልፀው፤ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ ነበር ብለዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት ነዋሪ ጨምረውም በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ለቅሶ ላይ መሆናቸውን ገልፈው፤ በጥቃቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ይናገራሉ።

"እስካሁን 100 አስክሬኖች ተገኝተዋል፤ የጠፉ አስክሬኖችም አሉ። ወደ ቡለንም 70 አስክሬኖች መጥተው ተመልክቻለሁ" ሲሉ የተመለከቱት ነዋሪ ገልጸዋል።

በጥቃቱም የጓደኛቸው አባት መገደላቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ "ቤት እየጠበቀ እያለ ነው ተኩሰው የገደሉት። አርሱ መሳሪያ ቢኖረውም፤ እነርሱ ብዙ ስለነበሩ እራሱን መከላከል አልቻለም" ሲሉ የተገደሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

ሌላ ያነጋገርናቸው ነዋሪ ደግሞ "ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነው ታጣቂዎች ወደ በኩይ ቀበሌ የገቡት" ይላሉ።

ጥቃቱ በከባድ መሳሪያ በመታገዘ ጭምር መፈፀሙን የገለፁት ነዋሪው፤ እስካሁን ድረስ ከ96 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና 28 ቤቶችና በርካታ የእህል ክምሮች መቃጣላቸውን አስረድተዋል።

ነዋሪው አክለውም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቡለን ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን በስፍራው ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አስክሬኖች በሸራ ተጠቅለው በየሜዳው ወድቀው ነው ያሉት፤ ገና ጫካ ያለው አልተሰበሰበም። ቡለን የመጡት ቁስለኞችም ከ20 በላይ ይሆናሉ። ሆስፒታል ሄጀ በዓይኔ ነው ያየኋቸው፤ በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉ አሉ" በማለትም ጥቃቱ በስለት፣ በመሳሪያና በቀስት መፈፀሙን ገልፀዋል።

በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎችን በተመለከተ እማንነታቸውን የሰጡት እኚህ ነዋሪ በዐይናቸው 96 አስክሬኖች መመልከታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው የአካባቢው ተወላጅ አይደሉም በተባሉ ነዋሪዎች ላይ መሆኑን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈጸም ወራት ተቆጥረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከፌደራልና ከክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ቅሬታቸውንም ሲያስረዱ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወያዩት ችግሩ በሌለበት አካባቢ ነው። ችግሩ ያለው ዲባጤ ቡለንን ጨምሮ በሦስት ወረዳዎች ነው። ከሦስቱ ወረዳዎች የተወከለና ሁኔታውን የሚያስረዳ ሰው እንኳን በውይይቱ አልተወከለም፤ ተወካዮች እንዳይሄዱም በክልሉ መንግሥት ተፅዕኖ ተደርጓል" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን የነዋሪውን ቅሬታ ግን ከክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ማረጋገጥ አልቻልንም።

የሆስፒታል ምንጮች

በመተከል የቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ እና ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይገለፅ የጠየቁ ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ወደ ሆስፒታላቸው ከቀኑ አምስት ሰዓት ጀምሮ በጥይት ተመትተው የቆሰሉ ሰዎች የመጡ ሲሆን ብዛታቸው እስከ አርባ ይደርሳል ብለዋል።

በጥይት፣ በስለት እና በቀስት ተመትተው ወደ ቡለን ሆስፒታሉ ከመጡ የትቃቱ ሰለባዎች መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እንደሚገኙበት አክለው ገልፀዋል።

ወደ ሆስፒታሉ የመጡት ሰዎች በጥይት እንዲሁም በቀስት መመታታቸውን የሚናገሩት ቢቢሲ ያናገራቸው የጤና ባለሙያ፤ ሆስፒታል ከደረሱት መካከል አንዲት ታዳጊ ሕጻን መሞቷን አረጋግጠዋል።

ግጭት በተከሰተበት አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ወደ ሆስፒታል ከመጡ ሰዎች መስማታቸውን የገለፁት የሕክምና ባለሙያው፣ ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የመጡት የጥቃቱ ሰለባዎች በጥቃት ፈጻሚዎቹ ተከበው ተኩስ የተከፈተባቸው ነዋሪዎች ያሰሙትን የድረሱልን ጩኸት ሰምተው የሄዱት መሆናቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።

የቡለን መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በተደጋጋሚ በአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች ጥቃት የሚደርስባቸውን ሰዎች ተቀብሎ የሚያክም ሲሆን መሰረታዊ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት በፀጥታ ችግር ምክንያት እንዳልቻለ የሕክምና ባለሙያው ተናግረዋል።

ለሆስፒታሉ ግዢ የሚፈፀመው ባሕር ዳር እንደነበር የገለፁት ባለሙያዎች ከቡለን-ቻግኒ ያለው መንገድ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ዝግ በመሆኑ ይህንን ማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን ገልፀዋል።

በዚህ የተነሳም በሆስፒታሉ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ለመጡ ሰዎች ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት እየተገሩ እንደሆነ ጨምረው አመልክተዋል።

በአካባቢው ካለፈው ዓመት ማብቂያ ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ እንደሚደርስ የሚናገሩት የሕክምና ባለሙያው እንዲህ በጅምላ ጉዳት ደርሶባቸው በርካታ ሰዎች ለህክምና ሲመጡ የአሁኑ ሁለተኛው መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ ብዙ ሰዎች የተጎዱት ከሳምንታት በፊት ከቡለን ወደ ቻግኒ የሚሄድ መኪና ላይ ጥቃት በደርሰበት ወቅት ብዙ ሰዎች በተገደሉና ወቅት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የመተከል ዞን ውስጥ በታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ወራትን አስቆጥሮ፤ አሁንም ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ለሞትና ለጉዳት እየተዳረጉ ይገኛሉ።

ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰነውና በሰባት ወረዳዎች በተዋቀረው የመተከል ዞን የተለያዩ ብሔረሰቦች ይኖራሉ። በዋናነት የጉሙዝ፣ የሽናሻ፣ የአማራ፣ የአገው፣ የኦሮሞና የበርታ ብሔሮች ይገኙበታል።

በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማንነትን የለየና በተወሰኑት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችና ከዚህ በፊት የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የአካባቢው ባለስልጣናት ጥቃቱን የሚፈጽሙት ኃይሎችን "ጸረ ሠላም" ከማለት ውጪ ማንነታቸውና የጥቃቱ አላማ በግልጽ አይታወቅም። በተለያዩ ጊዜዎች በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች የተለያየ ቁጥር ያላቸው በጥቃቶቹ ተሳትፈዋል የተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በአካባቢው ለወራት በዘለቀው ጥቃት ሳቢያ ጸጥታውን ለመቆጠጠርና በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች ለማስቆም ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ የፌደራል መንግሥት ጦር ሠራዊትና የክልሉ የጸጥታ አካላት የተካተቱበት ኮማንድ ፖስት ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች መዋቀሩ ይታወሳል።

ነገር ግን አሁንም ድረስ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው። አሁን የተፈጸመውና ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት በአካባቢው ከተፈጸሙት ሁሉ የከፋው እንደሆነ ይነገራል።