ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ንግድ ባንክ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ያልመለሱ የ565 ደንበኞቹን ስም ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ሌሊት በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ አጋጥሞት በነበረው ችግር ምክንያት ያለአግባብ የተወሰደውን ገንዘብ አልመሰሉም ያላቸውን ድንበኞቹን ስም ዝርዝር ይፋ አደረገ።
ባንኩ ዛሬ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. ገንዘብ ያለመለሱ ናቸው ያላቸው የ565 ሰዎች ስም ዝርዝር፣ የሂሳብ ቁጥር እና ሂሳባቸው የተመዘገበበትን ቅርንጫፍ ይፋ አድርጓል።
ባንኩ ይፋ ካደረገው ዝርዝር መመልከት እንደሚቻለው የማይገባቸውን ገንዘብ ወስደው ካልመለሱት መካከል በርከት ያሉት በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ የሚገኘው የጂግጂጋ ቅርንጫፍ ደንበኞች ይገኙበታል።
ከጂግጂጋ በተጨማሪ በሶማሌ ክልል የሚገኙት ፋፈን፣ ፊቅ፣ ደገሃቡር እና ኢፍቲን ቅርንጫፎች በአንጻራዊነት የተጠየቁትን ገንዘብ ያልመለሱ በርከት ደንበኞች የሚገኙባቸው ቅርንጫፎች ናቸው።
ይህ ክስተት ማጋጠሙን ተከትሎ ከፍተኛ መጠን ያለው ብር አንቀሳቅሰዋል በሚል ስማቸው በባንኩ ሲጠቀስ የቆዩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲሆኑ፣ ዩኒቨርስቲዎቹም ተማሪዎቻቸው የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የሲስተም ብልሽቱን ተከትሎ ባንኩ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት እንደበር አስታውቀው ነበር።
ከዚህ መካከል ሦስት አራተኛውን ማለትም ከ620 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲመለስ መደረጉንም አሳውቀዋል።
ባንኩ ገንዘብ ያልመለሱ ሰዎችን ስም ዝርዝርን ይፋ ያደረገው “ጤናማ ባልሆነ” ያልሆነ ባለው መንገድ ብር የወሰዱ እና ያዘዋወሩ ሰዎች ተመላሽ እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ጥሪ ሳይቀበሉ ከቀሩ በኋላ ነው ተብሏል።
አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ከምሽቱ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ባጋጠመው እና ለአምስት ሰዓታት ያህል በቆየው ችግር ምክንያት 801.4 ሚሊዮን ብር ከባንኩ መወሰዱን የባንኩ ፕሬዝዳንት ዛሬ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመውን ችግር ተጠቅመው የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ በማንቀሳቀስ ተሳተፈዋል የተባሉ 15 ሺህ የሚሆኑ የሂሳብ ቁጥሮች መገኘታቸውን እንዲሁም በዕለቱም 238,293 የገንዘብ ዝውውር መደረጉን የባንኩ ፕሬዝዳንት አሳውቀዋል።
ከዚህም ውስጥ ባለፉት አስር ቀናት አላግባብ ከባንኩ ከተወሰደው 622.9 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ማስመለስ መቻሉን ባንኩ ገልጿል።
ነገር ግን አሁንም 567 የሚሆኑ የባንኩ ደንበኞች ከ9.8 ሚሊዮን ብር በላይ የራሳቸው ያልሆ ገንዘብ አለመመለሳቸውም ተገልጿል።
ባንኩ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ እንዳስታወቀው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ከባንኩ የወሰዱ ደንበኞች አስካለፈው ቅዳሜ ድረስ በፈቃደኝነት የሚመልሱ ከሆነ በሕግ እንደማይጠይቃቸው አስታውቆ ነበር።
ነገር ግን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የራሳቸው ያልሆነውን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ ያለሆኑትን ደንበኞች ስም እና ፎቷቸውን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ ዛሬ ስም ዝርዝራቸውን ይፋ ያደረጋቸው ደንበኞቹን ጉዳይ ወደ ሕግ ከመውሰዱ በፊት አሁንም የወሰዱትን ገንዘብ እስከ መጪው ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም. ድረስ እንዲመልሱ ተጨማሪ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።
ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎችን በመጠቀም የደንበኞቹን ሙሉ ስም እና ፎቶግራፍ በማውጣት በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በመውሰድ ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ለሚመለከታቸው የሕግ አካል እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
እንዲሁም ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር በቀጣይ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እና የአስተዳደር ሕጋዊ እርምጃዎች እንደሚያስወስድ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግሩ ካጋጠመው በኋላ ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገበት ባለፉት ቀናት ከመግለጽ ተቆጥቦ ቢቆይም፣ የተለያዩ ምንጮች የገንዘቡን መጠን ከመቶ ሚሊዮኖች አስከ ቢሊዮኖች እንደሚደርስ ሲገልጹ ነበር።
ከ80 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱ ውስጥ በደንበኞች እና በቅርንጫፎች ብዛት እንዲሁም በገንዘብ አቅም ቀዳሚ የሆነ ግዙፍ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም ነው።
እንደ ስታቲስታ መረጃ ከሆነ በሃብት ብዛት በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ቀዳሚ የሆነው ንግድ ባንክ እአአ 2022 አጠቃላይ ንብረቱ 23 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
አንድ ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ ሃብት መሰብሰብ የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱ ዋነኛ ተቋማት ከሚባሉት ጥቂት መንግሥታዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።
በእአአ 2020/21 የበጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያገኘው ባንኩ፣ በዚሁ የበጀት ዓመት 735 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ማድረግ መቻሉን ይፋ አድርጎ ነበር።