ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራናውያን የድሮን ባለሙያዎች በክሬሚያ ይገኛሉ ስትል አሜሪካ አስታወቀች
ኢራን በዩክሬን የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃትን የሚያግዙ ወታደራዊ ባለሙያዎችን በሩሲያ ቁጥጥር ስራ ወዳለችው ክሬሚያ አሰማርታለች ሲል ዋይት ሃውስ አስታወቀ።
ኢራናውያኑ አሰልጣኞች እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ናቸው ሲሉ የአሜሪካ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ሰኞ ዕለት “ካሚካዜ” በሚባሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተመትታ ነበር። ድሮኖቹን ሩሲያ ብታሰማራም ኢራን ሠራሽ እንደሆኑ ይታመናል።
የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን በማቅረብ ኃላፊነት በወሰዱ የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣሏን ዩናይትድ ኪንግደም አስታውቃለች።
የዋይት ሃውስ ብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "የኢራን ወታደሮች በክሬሚያ እንዳሉ እና ሩሲያን እንደረዱ ገምግመናል።" ብለዋል።
"በአንጻራዊነት አነስተኛ" ቁጥር ያላቸው ኢራናውያን የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጡ ሲሆን ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን የሚያበሩት ደግሞ ሩሲያውያኑ ናቸው ብለዋል።
"ቴህራን አሁን በቀጥታ በመሬት ተሳታፊ ሆናለች። ተሳትፎዋም በዩክሬን ውስጥ በሲቪሎች እና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ተፅዕኖ ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች ማቅረብ ነው” ብለዋል ኪርቢ።
ኢራን ለሩሲያ በመወገን በዩክሬን ሕዝብ ላይ የምታቀርበውን እነዚህን መሣሪያዎች ለማጋለጥ፣ ለመከላከል እና ለመጋፈጥ አሜሪካ ሁሉንም ዘዴዎችን ትከተላለች ብለዋል።
ሰኞ ዕለት ጥቅም ላይ የዋሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች የኢራኑ ሻሄድ-136 መሆኑን ዩክሬን ገልጻለች።
ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ "ካሚካዜ" በመባል ይታወቃሉ። ድሮኑ ጥቃቱን ሲፈጸም አብሮ የሚፈነዳ ሲሆን ካሚካዜ የሚለውን ስያሜውን ያገኘው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮዎችን ከሚፈጽሙ የጃፓን አብራሪዎች ነው።
ሩሲያ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የዩክሬን ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመምታት እነዚህን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ተጠቅማለች። ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ የሃገሪቱን አንድ ሶስተኛ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አወድማለች።
በዚህ ምክንያትም ሐሙስ ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ በዩክሬን የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ላይ እገዳዎች ተጥለዋል።
የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ዩክሬንን ለማጥቃት ሩሲያ በመጠቀሟ በሦስት የኢራን ጄነራሎች እና በጦር መሳሪያ አቅራቢ ድርጅት ላይ ማዕቀብ መጣሏን ዩናይትድ ኪንግደም አስታውቃለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ ከሞስኮ "አጸያፊ" ጥቃቶች ትርፋማ ለመሆን የሚጥሩ “የጦር ነጋዴዎች” ብለዋቸዋል።
ማዕቀቡ ከደረሰባቸው መካከል የኢራን ጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል መሐመድ ሆሴን ባገሪ እና ሻሄድ አቪዬሽን ኢንደስትሪ የተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን አምራች ይገኙበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በደቡብ ዩክሬን በሚገኝ ቁልፍ ግድብ ላይ ሞስኮ ፈንጂዎችን ጠምዳለች ሲሉ ከሰዋል።
የካኮቭካ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰበት 80 ከተሞች በጎርፍ ሊጥለቀለቁ እንደሚችሉ እና የዛፖሪዝሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሚሆን ማቀዝቀዣ ውሃ ላይኖር ይችላል ሲሉ ዜለንስኪ ተናግረዋል።
ክሬሚያን ጨምሮ ደቡባዊ ዩክሬንም የውሃ አቅርቦት ሊያሳጣ ይችላል ተብሏል።