ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝደንት ኢሳያስ "የሶማሊያን ሰላም ማስጠበቅ ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ነው" አሉ
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመራ ያቀኑት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ከኤርትራው ፕሬዝደንት ጋር መወያየታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አስታወቁ።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገፃቸው ባሰፈሩት መግለጫ ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ ጉዳይ "ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን" ገልፀዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ከአንካራው ስምምነት በኋላ ወደ አስመራ አቅንተው ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሲመክሩ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ሚኒስትሩ የማነ እንዳስታወቁት ሁለቱ መሪዎች ረቡዕ ያደረጉት ውይይት "በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም ቀጣናዊና ዓለማ አቀፋዊ ትስስሮች ላይ ያተኮረ" ነው።
ሁለቱ መሪዎች ሶማሊያ በአፍሪካ ቀንድ "ታላቋ ሀገር" እንደመሆኗ ሰላሟን ማስጠበቅ ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ስለመሆኑ ውይይት ማድረጋቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ የአፍሪካ ቀንድ "ሁከት ከሚፈጥሩ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ራሱን መጠበቅ አለበት" ማለታቸው በማስታወቂያ ሚኒስትራቸው በኩል ተሰምቷል።
ፕሬዝደንቱ አክለው በኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ግብፅ መካከል የተፈረመው ስምምነት ዓላማው "በሶማሊያ መረጋጋት ማምጣት እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ሀገራትን የጋራ ጥቅም ማስጠበቅ" ነው ማለታቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ "ኤርትራ የሶማሊያ ጦር እንዲጠናከር ለምታደርገው እርምጃ" ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቱርክ አንካራ ተገናኝነተው በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ መስማማታቸው ይታወሳል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የአስመራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት በነገሠበት ወቅት ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ ነው በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት የተፈጠረው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ከደረሱት ስምምነት በኋላ ግብፅ ወታደሮቿን በአዲሱ የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ እንደምታካትት አሳውቃለች።
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ከሶማሊያ በቀረበልን ጥያቄ መሠረት" ወታደሮቻችን ወደ ሶማሊያ እንልካለን ብለዋል።
ባለፈው ሰኞ የሶማሊያ መንግሥት በጁባላንድ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ጦር ላይ ጥቃት ፈፅመዋል ሲል መክሰሱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ይህንን መግለጫ ተከትሎ በሰጠችው ምላሽ ግጭቱ የተፈጠረው "በሦስተኛ ወገን" ነው ብትልም ስም ከመጥቀስ ተቆጥባለች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዑካን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አግኝተው ተመልሰዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያው ግንኙነት መሻከሩ እየተገለጸ ባለበት ወቅት፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እንዲሁም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበው ግብፅ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ አስመራ ላይ የተፈረመው የሦስትዮሽ ስምምነት ከኢትዮጵያ አንጻር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ታኅሣሥ መባቻ ላይ በመንግሥታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ስለወቅታዊ ጉዳዮች ቃለ ምልልስ በሰጡበት ወቅት ግን ይህንን አስተባብለዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኤርትራ ከሦስት ጊዜ በላይ ጉብኝት አድርገዋል።