በጦርነት እና በክፍፍል የተፈተነው ህወሓት መሰረዝ የፖለቲካ ሕይወቱ ፍጻሜ ይሆን?

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ለ50 ዓመታት በመቆየት አንጋፋ የሆነው ህወሓት ለሁለተኛ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲነት ዕውቅናው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰርዟል።

ሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአገሪቱ የሥልጣን መንበር ላይ ዋነኛው ኃይል ሆኖ የቆየው ህወሓት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ቡድን ብሎ በመሰየም ሕገወጥ አድርጎት ነበር።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ህወሓት ከሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ወጥቶ በኃይል በተገዘ የአመጻ ተግባር ላይ በመሣተፉ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቶ እንዲሰረዝ መወሰኑን አስታውቆ ነበር።

ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በተካሄደ ድርድር ተቋጭቶ ህወሓት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲመለስ የሽብር ቡድንነት ፍረጃው ተነስቶለታል።

ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ህወሓት የነበረን ዕውቅናው በማስመለስ እና እንደ አዲስ በመመዝገብ ጉዳይ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ሲወዛገብ ቆይቶ፤ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ የቀረበውን ሃሳብ ባለመቀበል እንዲሁም ማሟላት ያለበትን ሂደት ባለመፈጸም በድጋሚ ግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ከፓርቲነት ተሰርዟል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኃያል የነበረው እና በዕድሜም ጎምቱ ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው ህወሓት ከሽምቅ ተዋጊነት፣ ወደ አገር መሪነት፣ ከዚያም ወደ ክልል አስተዳዳሪነት፣ ተመልሶ ወደ ትጥቅ እንቅስቃሴ፣ ከዚያም ወደ ክልላዊ ፓርቲነት አሁን ደግሞ ሕጋዊ ዕውቅና ወደ ሌለው ቡድንነት ወርዷል።

ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ያልለየው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከየት ተነስቶ አሁን ካለበት ሁኔታ ላይ ደረሰ?. . .

የህወሓት ጥንስስ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የንጉሡ አስተዳደር ወድቆ ወታደራዊው መንግሥት ወደሥልጣን መውጣቱን ተከትሎ ነበር የካቲት 11/1967 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያስታወቀው።

ለህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማኅበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተባለው መደበኛ ያልሆነ ቡድን ነበር።

የትግራይ ተማሪዎች ስብስብ የነበረው ማገብት ከ45 ዓመታት በላይ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ለነበረው ለህወሓት መመሥረት ዋነኛው ጥንስስ ነበረ።

ማገብት በስምንት አባላት ተመሠረተ ሲሆን፣ እነዚሁ መሥራቾቹም ኋላ ላይ ለህወሓት እንቅስቃሴ መጀመር ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

ስምነቱ ግለሰቦች በሪሁ በርሀ (አረጋዊ በርሄ ዶ/ር)፣ ፋንታሁን ዘርአጽዮን (ግደይ ዘርአጽዮን)፣ ሙሉጌታ ሐጐስ፣ አምባዬ መስፍን (ስዩም መስፍን)፣ አመሃ ፀሃዬ (አባይ ፀሃዬ)፣ ዕቁባዝጊ በየነ፣ ዓለምሰገድ መንገሻ እና ዘርኡ ገሰሰ (አግአዚ) ናቸው።

ከጅማሬው ደርግን የተቃወመው ማገብት በትግራይ ሕዝብ ላይ ደረሰ ያለውን ጭቆና ለማስወገድ የትጥቅ ትግል ማድረግ እና መሪ ድርጅት እንደሚያስፈልግ በመወሰን መሥራት ጀመረ።

ለዚህም የተወሰኑት አባላቱ የኤርትራ አማጺ ቡድኖች ከነበሩት ከጀብሃ እና ከሕዝባዊ ግንባር ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ወደ ኤርትራ ሲሄዱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከተማ ውስጥ ሆነው ሕዝብ ማደራጀት ጀመሩ።

የህወሓት ዓላማ

ቡድኑ የትጥቅት ትግል በጀመረበት ወቅት ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እና 'ሪፐብሊክ' የመመሥረት ጉዳይ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ይህ ሐሳብ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳልቆየ መሥራቾቹ ይናገራሉ።

በ1968 ዓ.ም. በተካሄደው የመጀመሪያው የድርጅቱ ጉባኤ 'ነጻ ትግራይ' የሚለው አጀንዳ በአብዛኛው አባል ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ውድቅ ተደረገ።

ከዚያም የድርጅቱን ዓላማ የመደብ ትግል በማድረግ ለጭቁን ሕዝቦችን 'የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት' እንደሚታገል ቢገልጽም ህወሓትን የሚቃወሙ ድርጅቶት ግን ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ለመነጠል እንደተቋቋመ በመግለጽ ሲተቹት ቆይተዋል።

ክፍፍል በህወሓት ውስጥ

ህወሓት ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1968 ዓ.ም. በድርጅቱ ውስጥ ባሉ አመራሮች መካከል መከፋፈል አጋጥሞ የነበረ ሲሆን ይህም 'ሕንፍሽፍሽ' በመባል ይታወቃል።

በዚህ ወቅትም በአመራሮቹ መካከል የነበረውን መከፋፈል ለመፍታት የወሰደው እርምጃም ፀረ-ዲሞክራሲያዊ እንደነበር አንዳንድ ቀደምት የቡድኑ አባላት ያስታውሳሉ።

ከዚህም በኋላ በ1977 ዓ.ም. በአመራር አባላቱ መካከል በድጋሚ ልዩነት ተፈጥሮ ከመሥራቾቹ መካከል ከነበሩት ውስጥ አረጋዊ በርሀ (ዶ/ር) እና ግደይ ዘርአጽዮን ድርጅቱን ጥለው እንዲወጡ ተደርገዋል።

በወቅቱ የተደረገውን ግምገማ እና የተግባራዊ እንዲደረግ የቀረበውን አዲስ ወታደራዊ ዕቅድ ብዙዎቹ የድርጅቱ አባላት ቢደግፉትም "በጊዜው የተመሠረተው ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) የተባለ የፖለቲካ ክንፍ ግን ድርጅቱን በአጠቃላይ እንቀየረው" የሚል ሐሳብ እንደነበረው የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።

የህወሓት ኮሚኒስታዊ ባህሪ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ያበቃለት ቢመስልም የድርጅቱ ውስጣዊ ባህሪና አደረጃጀት ሳይቀየር በሚመራው ኢህአዴግ ውስጥ 'አብዮታዊ ዲሞክራሲ' የሚባል ብዙ ያነጋገረ 'እንግዳ' ርዕዮተ ዓለምን በመያዝ እስከ መጨረሻው ዘልቋል።

የሩሲያ እና የቻይና አብዮቶች አድናቂ የነበረው ህወሓት እንደ መርኅ ግን ብዙም የማትታወቀው በምሥራቅ አውሮፓ ውስጥ ያለችውን የአልባንያን ኮሚኒዝም ይከተል ነበር።

ህወሓት በአገሪቱ የሥልጣን እርከን ላይ ጉልህ ሚና በነበረው ወቅት እና ከኤርትራ ጋር የተካሄደው የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ በ1993 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ በአመራሩ ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል ገጥሞታል።

በዚህ የክፍፍልም የህወሓት ሊቀመንበር እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩት ቡድን የበላይነቱን ይዞ ተቀናቃኞቹን አገለለ።

በዚህም በህወሓት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት እና ተጽእኖ የነበራቸው ከፍተኛ የቡድኑ አመራር አባላት ከድርጅቱ ሲባረሩ የተወሰኑት ደግሞ በሙስና ተከሰው ለእስር ተዳርገው ነበር።

ከዚህም በኋላ በህወሓት ውስጥ ኃያል ሆነው የወጡት መለስ ዜናዊ የህወሓትን ድርጅታዊ እና የአገሪቱን መንግሥታዊ ሥልጣን ጠቅልለው በመያዝ በህወሓት፣ በኢህአዴግ እና በአገሪቱ ጉዳይ ላይ ብቸኛው ወሳኝ ሰው ሆነው እስከ ህልፈታቸው ድረስ ቀጠሉ።

ከባዱ የህወሓት ፈተና

የህወሓት/ኢህአዴግ አንጎል የነበሩት የመለስ ዜናዊ ሞትን ተከትሎ ድርጀቱ ጠንካራ መሪ በማጣቱ እየተዳከመ ከቀደመ ዘመኑ በተለየ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ሊቀመንበሩን ለመቀያየር ተገድዶ ነበር።

በኢህአዴግ ላይ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ድርጅቱ ውስጣዊ ግምገማ አድርጎ ለውጥ ለማድረግ ከወሰነ በኋላ ህወሓት ተቆጣጥሮት ከነበረው የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ቀስበቀስ ተገፍቶ አመራሮቹ ወደ ትግራይ ተመልሰው ነበር።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ኢህአዴግን ለመለወጥ በወሰዱት አርምጃ ህወሓት ባለመስማማቱ ከመሠረተው እና ከመራው የብሔራዊ ድርጅቶች ግንባር ተነጥሎ ወጣ።

ህወሓት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር የገባበት ውዝግብ እና ፍጥጫ ተባብሶ ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም. ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ አመራሮቹ ዳግም ጠመንጃ አንስተው ወደ በረሃ ወርደው ለሁለት ዓመታት ቆይተዋል።

ጦርነት ቆሞ ሰላም ከወረደ በኋላ ግን የህወሓት አመራሮች በመካከላቸው አለመግባባት እና መካሰስ ጀምረው በጉልህ የሚታይ ከፍፍል ተፈጠረ። ይህም በሊቀመንበሩ ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል እና በአቶ ጌታቸው የሚመራ ሁለት ቡድን ተፈጥሮ ለወራት ሲወዛገብ ቆይቷል።

በመጨረሻም የደብረ ፂዮን ቡድን በ2016 ዓ.ም. ባካሄደው እና ዕውቅናን ባላገኘው የህወሓት ጉባኤ አቶ ጌታቸው እና በርካታ የድርጅቱ አመራሮች እንዲሁም አባላት እንዲባረሩ ተደረገ።

ይህም ህወሓት የገጠመው አራተኛው ክፍፍል ሊባል ይችላል።

አቶ ጌታቸው እና አጋሮቻቸው አሁን ከህወሓት ተለይተው በትግራይ ላይ ያተኮረ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ጥረት እያደረጉ ነው።

ህወሓት ግጭትን እንዴት ይፈታል?

ህወሓት ለ17 ዓመታት ባካሄደው የትጥቅ ትግል ወቅት ከፍልሚያ ውስጥ ገብቶ የነበረው ከወታደራዊው መንግሥት ጋር ብቻ አልነበረም።

ቡድኑ የትጥቅ ትግል በሚያደርግበት ጊዜ በተመሳሳይ ወታደራዊው መንግሥትን ተቃውመው ከወጡት ከኢዲዩ፣ ከጀበሃ፣ ከኢህአፓ እና ከሌሎችም ቡድኖች ጋር የነበረውን ፖለቲካዊ ልዩነት በኃይል ነበር የተፈታው።

ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ በትግራይ ሕዝብ ስም ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ስብስቦች መካከል አንዱ የነበረው የግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ (ግገሓት) መሪዎችን በመግደል ተጋዮቹን ደብዛቸውን እንዳጠፋ ይነገራል።

በውስጡ የተከሰቱ ልዩነቶች እና አለመግባባቶችም ፍጻሜያቸው አሸናፊው ወገን የተሸነፉ አባላቱን ከድርጅቱ ማባረር እና አንዳንድ ጊዜም እስር እንዳጋጠማቸው ቀደም ያሉ ክስተቶች ያመለክታሉ።

ነገር ግን ከደርግ ጋር የሚደረገው ጦርነት እየሰፋ ከትግራይ ባሻገር ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸጋገር በየአካባቢዎቹ ያሉትን ሕዝቦች ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶችን ማቀፍ እንዲሁም በማቋቋም ህወሓት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን)፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና በኋላም ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር በመጣመር ኢሕአዴግን ፈጥሯል።

በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ የደርግን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም በ1987 ዓ.ም በጸደቀው ሕገ መንግሥት ለአገሪቱ ብሔሮች እውቅናን ሰጥቷል የሚሉት እንዳሉ ሁሉ፤ ሥርዓቱ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት ችላ ያለ ነው እየተባለ ሲወቀስ ቆይቷል።

እነ ማን ህወሓትን መሩ?

ህወሓት እንደተመሠረት ለአንድ ዓመት ያህል ከመሥራቾቹ አንዱ የነበረው ገሰሰ አየለ (ስሁል) በጊዜያዊነት ከመራው በኋላ አቶ ስብሐት ነጋ ከ1971 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የድርጅቱ ሊቀ መንበር በመሆን መርተውታል።

ቀጥሎም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ በሞት እስከ ተለዩበት ጊዜ ድረስ ከ20 ዓመታት በላይ የህወሓት ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎም በ2004 ዓ.ም. አቶ አባይ ወልዱ የድርጀቱን ሊቀመንበርነት ቢረከቡም ብዙም ሳይቆዩ ድርጅቱን በተገቢው ሁኔታ መምራት አልቻሉም ተብለው እንዲነሱ ተደርገዋል።

በመጨረሻም በደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) መመራት የጀመረው ህወሓት በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን ተሰሚነት አጥቶ በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ተወስኖ ለመቆየት ከተገደደ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።

ህወሓት በጦርነቱ ወቅት በርካታ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮቹ እና አባላቱ ለእስር ከመዳረጋቸው በተጨማሪ ጥቂት የማይባሉት ቀድምት እና አንጋፋ አመራሮቹን ጨምሮ በጦርነቱ ወቅት አጥቷል።

ከትጥቅ ትግል ጊዜ አንስቶ በድርጅቱ ውስጥ ለአስርታት የቆዩት አመራሮቹ አብዛኛውን እና ዋነውን የድርጅቱን ከፍተኛ ሥልጣን ይዘው አሁን ድረስ ይገኛሉ። ህወሓትንም ከሚያስተቹት ጉዳዮች መካከልም ይህ አዲስ እና ወጣት አመራሮችን በብዛት አለማፍራቱ ነው።

ከባድ ውድመትን ካስከተለው ጦርነት ዳፋ ያላገገመው ህወሓት ከገጠመው ክፍፍል በተጨማሪ አሁን ደግሞ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ መንቀሳቀስ የሚያስችለው ዕውቅናው ተገፏል።

ይህ ውሳኔ ለ50 የቆየውን የህወሓትን ፖለቲካዊ ሕይወት ወደ ፍጻሜ ያመራው ይሆናል ወይስ በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ተመልሶ የሚያንሰራራበት ሌላ ዕድል ያገኝ ይሆን?