ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፖለቲካ ፓርቲነት ተሰረዘ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት (ህወሓት) ከገንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን አስታወቀ።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ህወሓት ከየካቲት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ዕግድ በመጣል ህወሓት የሚጠበቅበትን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ የሰጠው ጊዜ በመጠናቀቁ በድርጅቱ ላይ የመሰረዝ ውሳኔ አሳልፏል።

ከአራት ዓመት በፊት በትግራይ ውስጥ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት ተፈርጆ የነበረው ህወሓት፣ በኃይል እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፉ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰርዞ እንደነበር ይታወሳል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በአመጻ ድርጊት በመሳተፉ የተነሳ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፍ 98 መሠት ከፖለቲካፓርቲነት መሠረዙን ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውሷል።

ነገር ግን በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ አማካይነት ህወሓት በልዩ ሁኔታ ለመመዝገብ ችሎ ነበር።

የምርጫ ቦርድ ዛሬ የፓርቲውን መሰረዝ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በአዋጅ ቁጥር 1332/2016ን ተከትሎ በወጣው መመርያ ቁጥር 25/2016 እና ቦርዱ ምዝገባውን ተከትሎ እንዲፈጽም የሰጠውን ትዕዛዝ ህወሓት ባለማክበሩ በተለያየ ጊዜ ማሳሰቢያ ቢሰጥም ፓርቲው "በሕግ የተጣለበትን ግዴታ አልፈጸመም" ብሏል።

ከዚህም ባሻገር ፓርቲው አምኖበት እና ተስማምቶ ከቦርዱ የተቀበለውን የፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ አላውቅም ማለቱን በመጥቀስ "ሕጋዊ ሰውነቴ በዚህ ሠነድ አይረጋገጥም" ማለቱን ገልጾ "ሕግን እና መመሪያን ለማክበርም ፈቃደኛ ባለመሆን" መቆየቱን ቦርዱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ሲመዘገብ በሕጉ ላይ የተዘረዘሩትን ሰነዶች፣ የፓርቲ ፕሮግራም፣ የፓርቲውን መተዳደርያ ደንብ እና የፓርቲውን አመራሮች ስም ዝርዝር ከፊርማ ጋር ለቦርዱ ማቅረቡን ጠቅሷል።

ነገር ግን ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲሰረዝ የተላለፈው ውሳኔ እንዲነሳ ሚያዝያ 13 እና ሚያዝያ 28 2015 ዓ.ም. ለቦርዱ ባቀረበው ጥያቄ "በልዩ ሁኔታ" ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ እንዲቀርቡ የተጠየቁትን ሠነዶች አንዳቸውንም አያይዞ አለማቅረቡን ቦርዱ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ህወሓት ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ፓርቲዎችን በልዩ ሁኔታ የሚመዘግብ አዋጅ በታወጀ በሁለተኛው ወር ጥያቄ ሲያቀርብ፣ በወቅቱ የአዋጁ ዓላማ፣ አፈጻጸም እና በአዋጁ መሠረት በልዩ ሁኔታ ፓርቲ ሆኖ የመመዝገብ ሂደት በግልጽ አስታውቋል።

"ይህንኑ ለሕዝብ ይፋ የሆነውን አዋጅ ዓላማ እና አፈጻጸም በግልጽ በማወቅ እና በመረዳት አዋጁ ላይ የተመለከቱትን ሰነዶች አያይዞ በማቅረብ በአዋጁ የተጠየቀውን የምዝገባ ሥርዓት በመፈጸም" ምዝገባው መከናወኑን ቦርዱ ገልጿል።

ህወሓት ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ጥያቄው የቀረበው የአዋጁን መውጣት ተከትሎ መሆኑን፣ ፍትህ ሚኒስቴር ህወሓት ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ "በልዩ ሁኔታ" ስለመመዝገብ የሚያስረዳ መሆኑን ገልጿል።

ቦርዱ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. በልዩ ሁኔታ በመመዝገብ የሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት በተሰጠበት ወቅት በግልጽ የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነት እንደማይመለስለት መግለጹንም አስፍሯል።

በወቅቱም የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው ሰርተፍኬቱን እና "ደብዳቤውን በሚገባ አይተው እነብበው እና ተስማምተው ፈርመው" መውሰዳቸውን በመግለጽ "በልዩ ሁኔታን ተመዝግቦ የተሰጠን ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ አንቀበለውም ማለት ተቀባይነት የለውም" ብሏል።

ከተመሠረተ ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ህወሓት በምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ የቀረበለትን አማራጭ ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ ለዚህም የቀደመው እውቅናው እንዲመለስለት እንጂ በአዲስ መልክ ለመመዝገብ ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

ባለፈው ሳምንት ህወሓት ባወጣው መግለጫ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት የድርጅቱን ህልውና የሚያረጋግጥ በመሆኑ እንደ አዲስ ምዝገባ እንዲፈጽም እንደማይገደድ አስታውቋል።

በዚህም የድርጅቱን ሕጋዊ ዕውቅና ለመመለስ የሚያስፈልገው ፖለቲካዊ ውሳኔ እንጂ የሕግ ጉዳይ አለመሆኑን በመጥቀስ የፌደራል መንግሥቱ እና ሌሎችም የፕሪቶሪያ ስምምነት አሸማጋዮች የህወሓትን ነባር ዕውቅና እንዲመለስለት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቦ ነበር።