ከፖለቲካ ፓርቲነት በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት ስለውሳኔው ምን ይላል?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን የፖለቲካ ፓርቲነት ዕውቅናን መሰረዙን ተከትሎ ውሳኔው "የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጎዳ ነው" ሲሉ ሲሉ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑዔል አሰፋ ተናገሩ።

አቶ አማኑዔል ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ቦርዱ ለፓርቲው የሰጠውን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከመሰረዙ በፊት እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ መግለፁን አስታውሰዋል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከማክሰኞ ግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወቃል።

ህወሓት ከፓርቲነት የተሰረዘው፤ ቦርዱ ያዘዘውን "የእርምት እርምጃ" ተግባራዊ ባለማድረጉ መሆኑን በመግለጫው ላይ ገልጿል።

ነገር ግን የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ፓርቲው የተሰጠውን የምዝገባ ምስክር ወረቀት እንደማይቀበል ሲገልጽ መቆየቱን ተናግረው "ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን የሚመዘገቡበት እና የሚተዳደሩበት ሥርዓት በማበጀት እንደ አንድ የዲሞክራሲ ቤት ሆኖ ከማገልገል ይልቅ የራሱን አቋም ይዞ የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚጎዳ መልኩ ተንቀሳቅሷል" ሲሉ ወንጅለዋል።

አቶ አማኑዔል አክለውም ቦርዱ የኢትዮጵያ መንግሥትን "ወደ ሌለ መንገድ ለመምራት የሚያስችል መንገድ የከፈተ ነው የሚመስለኝ" ሲሉ ከውሳኔው አንጻር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የምርጫ ቦርድ "የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚጎዳ መልኩ ነው የተንቀሳቀሰው" ሲሉ የተናገሩት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት "የፕሪቶሪያ ስምምነትን ካለመቀበል የተነሳ ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የቦርዱ አመራሮች ስምምነቱን ስላልተቀበሉ "እጃቸው ላይ ያለውን የሕግ ከለላ በመጠቀም የፕሪቶሪያ ስምምነትን በሚጎዳ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል" ሲሉም ወንጅለዋል።

ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. እንደ አዲስ ፓርቲ መመዝገባቸውን የሚገልጸውን ሰርተፍኬት አልቀበልም ማለታቸውን እና በተደጋጋሚ ሕጋዊ ሰውነታቸው እንዲመለስ ሲጠይቁ መቆየታቸውን አቶ አማኑዔል አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ላይ ግን ህወሓት በልዩ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ በሕጉ የሚጠየቁ ዝርዝር ሰነዶች ማቅረቡን እና የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሰርቲፊኬቱን እና ደብዳቤውን በሚገባ ተስማምተው በፈቃዳቸው ፈርመው መውሰዳቸውን አስታውቋል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሕጋዊ ሰውነቱ መነሳቱን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እንዲያደራድረው ግንቦት 7 2017 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።

ህወሓት ምርጫ ቦርድ ለፓርቲው የሰጠውን ምስክር ወረቀት መሰረዙ "አደገኛ" እና በ2015 ዓ.ም. የተፈረመው የፕሪቶርያ ስምምነት ላይ "ከፍተኛ ስጋት" የደቀነ ነው ብሏል።

ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አማኑኤል ይህንኑ ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በነበራቸው የተለያዩ ውይይቶችም ላይ አንስተው በስፋት መነጋገራቸውን አብራርተዋል።

ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ያወጣው ህወሓትን የመሰረዝ መግለጫ "ነሐሴ 3 ወይንም 4 ሊያደርጉት የሚችሉት ጉዳይ ነበር" ብለዋል።

ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. ሰጥቶት የነበረውን እንደ አዲስ ምዝገባ ነው የሰረዘው የሚሉት አቶ አማኑዔል፣ ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከጦርነቱ በኋላ ግንኙነት የመሠረተው በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ምርጫ ቦርድ ህወሓትን እንደ አዲስ መዝግቦ የምስክር ወረቀት ከመስጠቱ በፊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ ሕጋዊ ግንኙነት መጀመሩን አስታውሰዋል።

"የፕሪቶሪያ ስምምነት ይመልሳቸዋል የተባሉት ነገሮች ደግሞ ምንም መልስ አላገኙም። ስለዚህ እነርሱ መልስ እንዲያገኙ እንሠራለን። የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት በሚመለከት ትግራይ ውስጥ ካሉ [መልስ ካላገኙ] ጉዳዮች አንዱ ይሆናል" ብለዋል።

የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ የትግራይ ሕገ መንግሥታዊ ግዛት፣ የመልሶ ግንባታ፣ የትጥቅ መፍታት፣ የተጠያቂነት እና ሌሎች ጉዳዮች አለመፈታታቸውን የዘረዘሩት ምክትል ሊቀመንበሩ የአሁኑ ውሳኔ ተጨማሪ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

". . . ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት በሚመለከት በጦርነቱ ጊዜ የተሰረዘ ስለሆነ . . . በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የሚታይ ይሆናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመከተል የፕሪቶርያን ውሳኔ "የሚነካ ነገር የሚያደርግ ከሆነ አደገኛ ይሆናል" ሲሉም አስረድተዋል።

ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ሰርተፊኬት ሰርዠዋለሁ የሚለው ውሳኔው ከቦርዱ ጋር ያለንን ግንኙነት በሚመለከት የተሰጠ ውሳኔ ነው የሚሉት አቶ አማኑዔል፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት የተለየ ነው ይላሉ።

"ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት የተመሠረተው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረቀት ላይ ሳይሆን በሁለታችን መካከል ዓለም እያየ በፕሪቶሪያ ላይ የተፈራረምነው ስምምነት ላይ ነው።"

ይህ የፕሪቶሪያ ስምምነት ግንኙነት የምርጫ ቦርድ "ሰጠው ነሳሁ በሚለው ወረቀት ላይ" አይመሠረትም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን ማንኛውም ግንኙነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ሠሰረት መቀጠል አለበት ብለዋል።

ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ግንኙነት በማድረግ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እርስ በእርስ እውቅና በዚህ ስምምነት በኩል መሰጣጠታቸውንም አቶ አማኑኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ህወሓት ከአሸባሪነት መሰረዙን፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመሥርቶም ክልሉን እያስተዳደረ መሆኑን ምክትል ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል።

ከስምምነቱ በኋላም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚያደርጋቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቶች እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነት ህወሓት 2013 ዓ.ም. ጥር ወር ላይ መሰረዙ ይታወሳል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ሲጠይቅ የቆየው ህወሓት፣ የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን ለመመለስ የሚያስችል ሕግ የለኝም በማለቱ አዲስ ሕግ ወጥቷል።

"የወጣው ሕግ ግን የተሰረዘ ሕጋዊ ሰውነታችንን የሚመልስ ሳይሆን አዲስ አድርጎ የሚመዘግብ ነው፤ አዲስ አድርጎ የሚመዘግብ ብቻ ሳይሆን ጥፋተኝነትንም በህወሓት ላይ የሚጭን ነው" ሲሉ አቶ አማኑዔል ይናገራሉ።

አክለውም ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ የታወጀውን ጦርነቱን ለመከላከል መምራቴ እና መሳተፌ "የመብት ጉዳይ ነው" ይህ በአመጻ ተግባር ላይ መሰማራት ሊባል አይችልም ሲል መከራከሩን ያነሳሉ።

ይህንን መቀበል የኢትዮጵያ "የሕግ ማስከር ዘመቻ" መቀበል እና የትግራይ ሕዝብ "የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያጠፋ፣ ተጠያቂነትን ወደ ትግራይ የሚገለብጥ ስለሆነ የወጣውን አዲስ ሕግ አልተቀበለውም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት የሰረዘው ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ለፓርቲው የሰጠው ቀነ ገደብ ማክሰኞ ግንቦት 5/2017 ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።

ቦርዱ ይህንን ቀነ ገደብ ባሳወቀበት መግለጫው፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል "የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን" በሦስት ወራት ውስጥ እንዲያካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ቦርዱ ህወሓትን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄድ ያዘዘው፤ "በአመጽ እና በሕገ- ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ" የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን "በልዩ ሁኔታ" እንደሚዘገቡ የሚያስችለው አዋጅ በሚያስቀምጠው ድንጋጌ መሠረት ነው።

ይህ አዋጅ "በልዩ ሁኔታ" የሚመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያካሄዱ በምርጫ ቦርድ ሊታዘዙ እንደሚችሉ ይደነግጋል።