ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስሪላንካ ሚኒስትር ለመብራት መቋረጥ አንድ 'ዱርዬ' ዝንጀሮን ተጠያቂ አደረጉ
በስሪላንካ ሙሉ በሙሉ መብራት ለመቋረጡ 'አደብ ያልገዛ' የተባለ አንድ ዝንጀሮ ተጠያቂ ተደረገ።
ዝንጀሮው ለመብራት መቋረጥ ተጠያቂ የተደረገው በኃይል አቅርቦት ሚኒስትሩ ኩማራ ጃያኮዲ ነው።
እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ ዝንጀሮው ከኮሎምቦ ደቡብ አቅጣጫ የሚገኘው ማከፋፈያ ላይ ጉዳት አድርሰውበታል።
"ዝንጀሮው በኃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመሮች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ የኃይል ሚዛኑን አስቶታል" ብለዋል ሚኒስትሩ።
የመብራት መጥፋቱ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እሑድ፣ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ነው የተከሰተው። በዚህ የተነሳ ብዙ ዜጎች በጄኔሬተር ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል።
አሁን ኃይል ቀስ በቀስ እየተመለሰ ነው ተብሏል።
በማኅበራዊ የትሥሥር መድረኮች በርካቶች ሚኒስትሩ ላይ እየተሳለቁ ነው።
"አንድ ዝንጀሮ 'ባልቦላውን' ማጥፋት ከቻለ ስለ መሠረተ ልማት እድሳት ለማሰብ ጊዜው አሁን ነው" ሲል ማሪዮ የተባለ ዜጋ በኤክስ ገጽ ፅፏል።
ሌላ የኤክስ ተጠቃሚ፣ በእንግሊዝኛ፣ "monkey business'' (መጭበርበር ይሉሃል ይህ ነው!) ዓይነት ስላቅ ተሳልቋል።
ጀሚላ ሁሴን የተባለች የዴይሊ ሚረር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ "በዓለም ላይ ዝንጀሮዎች በኃይል ማሰራጫ ላይ ስለተደባደቡ መብራት የሚጠፋባት አገር ስሪላንካ ብቻ ትመስለኛለች" ስትል ጽፋለች።
ዴይሊ ሚረር እንደዘገበው ከሆነ ባለፉት በርካታ ዓመታት የኤሌክትሪክ መሐንዲሶች የኃይል መስመሩ እድሳት ይፈልጋል ብለው ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ባለሥልጣናት ግን ጆሮ አልሰጧቸውም።
አንድ ባለሙያ እንዳሉት የኃይል ጣቢያው በጣም ደካማና ያረጀ ከመሆኑ የተነሳ አንድ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሲጎዳ ሙሉ አገሪቱ በጨለማ ትዋጣለች።
ስሪላንካ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2022 የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ በተዘፈቀች ጊዜ ተመሳሳይ የኃይል መቋረጥ በመላ አገሪቱ ገጥሟት ነበር።