ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርስቲ በአስማት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ሊሰጥ ነው
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ኤክስተር ዩኒቨርስቲ በሚመጣው የአውሮፓውያን ዓመት 2024 ተማሪዎችን አስማት (ምትሃት) በማስተማር የማስተርስ ዲግሪ ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርስቲው አስማት በማስተርስ ዲግሪ ለመስጠት ሲወስን በአገሪቱ ካሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም መካከል ቀዳሚው እንደሚሆን ተነግሯል።
በሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ) ደረጃ ዩኒቨርስቲው የሚሰጠው ትምህርት “በምትሃት እና በአስማት ጥበብ” የማስተርስ ዲግሪ የሚባል ሲሆን፣ የትምህርት ዘርፉን ለመጀመር ምክንያት የሆነው “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስማትን ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት መፈጠሩ” መሆኑን የትምህርት ክፍሉ መሪ ተናግረዋል።
ትምህርቱ ስለጥንቆላ እና አስማት ታሪክ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ባሉ ማኅበረሰቦች እና በሳይንስ ላይ ስላላቸው ተጽእኖ እንደሚዳስስ ተነግሯል።
በዘርፉ በኤክስተር ዩኒቨርስቲ በማስተርስ ደረጃ የሚሰጠው ሥልጣና አንድ ዓመት የሚወስድ ሲሆን፣ በሚቀጥለው መስከረም ይጀምራል ተብሏል።
በታሪክ፣ በሥነ ጽሁፍ፣ በፍልስፍና፣ በሥነ ልቦና፣ በድራማ፣ በሃይማኖት፣ በአርኪዮሎጂ እና በሶሲዮሎጂ እውቀት ያላቸው ምሁራን፣ አስማት በምሥራቁ እና በምዕራቡ የዓለም ክፍል ውስጥ ስላለው ሚና ያስተምራሉ።
ዩኒቨርስቲው እንዳለው በምትሃት ላይ ሊሰጥ ያሰበው የሁለተኛ ዲግሪ ጥናት፣ ታሪክ እና ሌሎች ሰፊ የዕውቀት መስኮችን በማካተት በማስተማር በዩናትድ ኪንግደም የመጀመሪያው ነው።
የትምህርት ክፍሉ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሚሊ ሴሎቭ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርቱ ዘርፍ እንዲሁም ከትምህርቱ ዘርፍ ውጪ ባሉ የማኅበረሰቡ አባላት ዘንድ በአስማት እና በጥንቆላ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች ወሳኝ ጥያቄዎች እየሆኑ ነው” ብለዋል።
ፕሮፌሰር ሴሎቭ ጨምረውም “ይህ የሁለተኛ ዲግሪ ጥናት በሰዎች ዘንድ ያለውን ምዕራቡን ዓለም የምክንያታዊነት እና የሳይንስ ቦታ፣ እንዲሁም ቀሪውን ዓለም ደግሞ የአስማት እና የባዕድ አምልኮ ስፍራ አድርጎ የመመልከተን ሁኔታ እንዲመረምሩ ያደርጋል።”
ትምህርቱን የሚከታተሉ ሰዎች በማስተማር፣ በምክር አገልግሎት፣ በሥልጠና፣ በቅርስ እና ሙዚየሞች፣ በቤተ መዛግብት፣ በቱሪዝም፣ በጥበት ተቋማት እና በተለያዩ የሥራ መስኮች ውስጥ እንዲሰሩ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ተብሏል።