ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን ውጊያ ምክንያት ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን ተመድ ገለጸ
አንድ ወር በሞላው የሱዳን ውጊያ ምክንያት ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ።
አብዛኞቹ ሰዎች የተፈናቀሉት እዛው አገር ውስጥ ነው።
ንጹኃን ዜጎችን ለመጠበቅ ስምምነት ቢኖርም የሱዳን ጦርም ይሁን ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ውጊያ ቀጥሏል።
ውጊያው ካርቱምን ጨምሮ በሌሎችም ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው።
በካርቱም መውጫ አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተከፈተ ተኩስ ብዙዎች መጎዳታቸውን ተከትሎ ሁለቱም የሱዳን ተዋጊዎች አንዳቸው ሌላቸውን እየከሰሱ ነው።
ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ውጊያ ላለማካሄድ ሁለቱ ተዋጊዎች ስምምነት ለማድረግ በጅዳ ይገናኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በስፋት ሰፍሮ ስለሚገኝ ስምምነቱ እውን መሆኑ አጠራጣሪ ይሆናል።
በዳርፉር ያለው ውጊያም እየተባባሰ መጥቷል። ኤል ጄኔያ አረብ በሚባለው ቦታ ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ቤቶች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
በሱዳን ያለውን ጦርነት ለማቆም አስቸጋሪ ከመሆኑን ባሻገር ውጥረቱ ወደ መላው ቀጠናው ሊዛመትም ይችላል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል በካርቱም፣ በኦምዱርማን እና በዳርፉር ክልሏ ጄኔይና ውስጥ ግጭቶች ቀጥለዋል።
በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ አንድ ወር ሞልቶታል።
የሱዳን ተፋላሚዎች በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ለቀናት ድርድር ካደረጉ በኋላ ባለፈው ሐሙስ “ለድርድሩ ተገዢ ለመሆን” ስምምነት ፈርመዋል።
ትላንት እሑድ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሳዑዲ አረቢያ፣ ጂዳ ውስጥ ንግግራቸውን መልሰው ይጀምራሉ ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ድርድር ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ቢስማሙም ተኩስ አቁም ላይ ግን መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።
አራት ሳምንታትን ባስቆጠረው በዚህ ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 200 ሺህ የሚጠጉ ደግሞ አገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል። በተጨማሪም ቢያንስ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ሱዳናውያን ተፈናቅለው እዚያው አገራቸው ውስጥ ይገኛሉ።
የተስፋፋው ዘረፋ እና የዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች ሱዳንን ለቀው መውጣት ከፍተኛ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት እንዲከሰት አድርጓል።