በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሠራተኞች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ተለቀቁ

ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው ተለቀቁ።

ከ30 በላይ የሚሆኑት የፋብሪካው ሠራተኞች ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ ውስጥ ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ.ም. ንጋት ላይ ነበር በታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱት።

ምንጮች እንዳሉት በሠራተኞቹ ላይ እገታውን የፈጸመው መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው እና ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው፣ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን አባላት ናቸው።

የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች እገታን ተከትሎ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቀው እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት ካገቷቸው በፋብሪካው አውቶብስ ተሳፍረው ሲጓዙ ከነበሩት ሠራተኞች መካከል የሥራ ድርሻቸው ጽዳት እና ጥበቃ የሆኑትን በመለየት ከለቀቁ በኋላ 17 ሰዎችን ይዞ አቆይቶ ነበር።

የሠራተኞች እገታ ባጋጠመ ወቅት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሁለት ኃላፊዎች 17 ያህል ሠራተኞች የት እንዳሉ እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ቢቢሲ ከምንጮቹ እንዳጣራው በታጣቂዎቹ ታግተው ለቀናት የቆዩት ሠራተኞች ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው ባለፈው ቅዳሜ እና ዕሁድ ተለቀዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ነዋሪ እና የፋብሪካው ኃላፊዎች ሠራተኞቹ የሲሚንቶ ግብዓት ተቆፍሮ ወደሚወጣበት ስፍራ በድርጅቱ የሠራተኞች ማመላለሽ አውቶብስ እየተጓዙ ሳለ ነበር በታጣቂ ቡድኑ አባላት የታገቱት።

ይህ ሠራተኞቹ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት የታገቱበት ፋብሪካ የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ነው።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በስፋት በሚንቀሳቀስበት በዚህ አካባቢ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም በዚህ አካባቢ ሰዎችን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለ ጉዳይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገረዋል።

ከእንዲህ አይነቶቹ የእገታዎች ጋር ስሙ የሚነሳው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላቱ በእንዲህ ያለ ድርጊት ውስጥ እንደማይሳተፉ አስተባብሎ ነበር።

በቢቢሲ ይህንና ተመሳሳይ የእገታ ድርጊቶችን በተመለከተ ከአካባቢው እና ከክልሉ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ታጣቂ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚፈጽመው ጥቃት ባሻገር ሰዎችን በመያዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ለማስለቀቂያነት እንደሚጠቅ ገልጸው ነበር።

ባለሥልጣኑ ጨምረውም ታጣቂው ቡድን በተለያየ አካባቢ የተበታተነ እና እርስ በእርሱ ግጭት ውስጥ ያለ መሆኑን በመግለጽ፣ ምንም አይነት “ፖለቲካዊ አጀንዳ የላቸውም” ብለዋል።

በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የሚነገር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚወስዳቸው እርምጃዎች የተነሳ አካባቢው ሰላም ከራቀው ዓመታት ተቆጥረዋል።

በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ የቡድኑ እንቅስቃሴ እና የጥቃት አድማስ እየሰፋ በመምጣቱ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች እና የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።