ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትታሰራላችሁ እያሉ በሚሊዮን ዶላሮች የሚያጭበረብሩት ሐሰተኞቹ የቻይና ፖሊሶች
በዓለማችን ገንዘብ ለማግኘት የሚደረጉ ማጭበርበሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቁ መጥተዋል።
እንዴት ታሰቡ? የሚያስብሉ ማጭበርበሪያ መንገዶችንም የዲጂታል ዘመኑ ቀላል አድርጓቸዋል።
ከሰሞኑም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዲያስፖራ ቻይናውያንን ወደ ቻይና ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ ለእስር ትዳረጋላችሁ የሚሉ ሐሰተኛ የቻይና ፖሊሶች ብቅ ብለዋል።
አንዳንዶቹም ሙሉ አንጡራ ሃብታቸውን ለእነዚህ አጭበርባሪዎች ሰጥተዋል።
ሙሉ ጥሪታቸውን ለአጭበርባሪዎች ከሰጡ መካከል ብሪታኒያዊ-ቻይናዊቷ ሄለን ያንግ አንዷ ናት። ግለሰቦቹ የቻይና ፖሊስ የደንብ ልበስን ለብሰው ከቻይና በቪዲዮ የደወሉላት ሲሆን፣ ፖሊስ ጣቢያውንም በቪዲዮ አስጎብኝተዋታል።
በቻይና ውስጥ በጣም ተፈላጊዋ ሴት እንደሆነች በማሳመን ገንዘቧን የበሏት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው።
እነዚህ ግለሰቦች በለንደን አካውንታንት (የሂሳብ ባለሙያ) የሆነችውን ሄለንን በከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር በትውልድ አገሯ ቻይና ምርመራ ተከፍቶብሻል አሏት።
ሄለን ምንም የማታውቀው ወንጀል መፈጸሟን የሚያሳይ የተቀነባበሩ በርካታ ማስረጃ ቀረበላት።
እነዚህ ሐሰተኛ ፖሊሶች ለቻይና ተላልፋ እንደምትሰጥ እና እንደምትታሰርም ነገሯት።
ወደ ቻይና ተላልፎ መሰጠት ያስደነገጣት ሄለንም ሙሉ ሕይወቷን የቆጠበችውን 29 ሺህ ፓውንድ ጥሪቷን “የዋስ ገንዘብ” በሚል ላከች።
“በአሁኑ ወቅት ሞኝ የሆንኩ ያህል ነው የሚሰማኝ። በወቅቱ ግን ያ እውነት እንዳልሆነ ለማወቅ የምችልበት ዕድል አልነበረም። በጣም አሳማኝ ነበር” ትላለች።
ሄለን ብቻ አይደለችም የእነዚህ አጭበርባሪዎች ሰለባ የሆነችው በርካታ የቻይና ዲያስፖራዎች ናቸው።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የቻይና ኤምባሲዎች ከእነዚህ ሐሰተኛ ፖሊሶች ተጠንቀቁ በሚል ማስጠንቀቂያዎች አውጥተዋል።
ኤምባሲዎቹ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካው ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን አውጥቷል።
በሎስ አንጀለስ የሚኖሩ አንዲት የዕድሜ ባለጸጋ ለቻይና ተላልፈው እንዳይሰጡ በሚል 3 ሚሊዮን ዶላር ለእነዚህ አጭበርባሪዎች ከፍለዋል።
የቻይና ፖሊስ አባላት ነን የሚሉት ማጭበርባሪዎቹ የሚጀምሩት በስልክ ጥሪ ነው። መጀመሪያ ላይ ብዙ አደገኛ አይመስልም የስልክ ጥሪው።
ለሄለንም መጀመሪያ የደወለላት ግለሰብ የቻይና ጉምሩክ ሠራተኛ ነኝ ያለ ሲሆን፣ በስሟ የተላከ ሕገወጥ እሽግ ይዘናል ሲል ነገራት።
ሄለን ምንም እቃ እንዳልላከች የተናገረች ሲሆን፣ ማንነቷ ተሰርቋል ብላ ካመነች የፖሊስ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባት ነገራት።
ሄለን ብትጠራጠርም ስልኩን አልዘጋችውም። “በቻይና ተወልደን ያደግን ልጆች በዋነኝነት የምንማረው ታዛዥነትን ነው። ፓርቲውም ሆነ ወላጆቼ አንድ ነገር እንዳደርግ ሲጠይቁኝ እምቢ አልልም” ትላለች።
ከዚያም አንድ ፖሊስ አናግሪ ተባለች። ፋንግ ነኝ ያለ ፖሊስ አናገራት። ፖሊስ መሆንህን በምን አውቃለሁ? በሚል ማስረጃ በጠየቀችበት ወቅት ግለሰቡ በቪዲዮ ደወለላት።
የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሶ የነበረ ሲሆን የፖሊስ መታወቂያውንም አሳያት። በመቀጠልም ፖሊስ ጣቢያውን በቪዲዮ ያስጎበኛት ሲሆን በርካታ የደንብ ልብስ የለበሱ መኮንኖች እንዲሁም ትልቅ የፖሊስ አርማ ያለበት ጠረጴዛም አየች።
“ጥርጣሬዎቼ በሙሉ ጠፉ እናም ይቅርታ ከዚህ በኋላ እጠነቀቃለሁ። ብዙ ወንጀለኞች እኮ አሉ ስትል” ለፖሊስ ነኝ ባዩ ነገረችው።
ከዚህ ግለሰብ ጋር እያወሩ እያለ ከጀርባ ድምጽ የተሰማት ሲሆን፣ ስለሷ ጉዳይ ስልክ ስለተደወለለት እንዲመልስ የሚጠይቅ ነበር። እንድትጠብቅ ካናገራት በኋላ ተመልሶ መጥቶ ሲያናግራት ሕገወጥ እሽግ የሚለው ሐሳብ ቀረ። በከፍኛ የገንዘብ ማጭበርበር ተጠርጣሪ መሆኗ እንደተነገረው ገለጸላት።
“ይህ የማይረባ ጉዳይ ነው አልኩት። እሱም በምላሹ ማንም ሰው ጥፋተኛ ነኝ አይልም። መሠረታዊው ነገር ማስረጃው ነው” ሲል እንደገለጸላት ታስረዳለች።
በስሟ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያለው የባንክ ደብተር የሚመስል ነገር አሳይዋት። ፖሊስ ነኝ ባዩ ፋንግ ንጹህ ከሆነች እውነተኛ አጭበርባሪዎች እንዲያዙ ልታግዝ እንደሚገባ ነገራት።
ስለ ምርመራው ለማንም እንደማትናገር ቃል በመግባት ምሥጢራዊ ስምምነት እንድትፈርም አደረጋት። ሄለን ስለ ጉዳዩ ትንፍሽ ካለች የስድስት ወር እስራት እንደሚጠብቃት ማስጠንቀቂያ ተሰጣት።
“በቻይና ፖሊስ ቃለ መጠይቅ እንደተደረገልሽ ለማንም ብትናገሪ ሕይወትሽ አደጋ ላይ ይወድቃል” ሲል እንዳስፈራራት ታስረዳለች።
ከዚያም እነዚህ አጭበርባሪዎች ሄለን ቀን ከሌት የምታደርጋቸውን ጉዳዮች መስማት ስላለባቸው አንድ መተግበሪያ እንድትጭን አደረጉ።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሄለን ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል በተለመደ ሁኔታ ሕይወቷ ቀጠለች። ማታ ማታ ግን እያንዳንዷን የሕይወቷን የየዕለት ተግባት በዝርዝር በመግለጽ እንድትጽፍ የታዘዘችውን ትሰራለች።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ፖሊስ ነኝ ባዩ ፋንግ ደውሎ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነገራት። ከዚያም በርካቶች እንደወነጀሏት የሚያሳይ የጽሑፍ መግለጫ አሳያት።
አንድ እስረኛ ነው የተባለ ግለሰብ ለፖሊስ ሲናዘዝ እና በማጭበርበር ውስጥም እሷን በስሟ ጠርቶ አለቃው እንደሆነች የሚናገርበት ቪዲዮ ተላከላት።
ቢቢሲ ቪዲዮውን የተመለከተ ሲሆን ግለሰቡ የኮቪድ ጭንብል ያጠለቀ ሲሆን የሚሰማው ድምጽ ከከንፈር እንቅስቃሴው ጋር ይዛመዳል የሚለውን ማወቅ አልተቻለም።
የሄለንን ስም ወይም ሌላ ሰለባን ስም የሚጠቅስ ድምጽ በአርትዖት መጨመርም ቀላል ነው። ለሄለን ግን እውነተኛ ፖሊሶች ጋር እየተነጋገረች ስለመሆኗ ምንም ጥርጣሬ አላደረባትም።
“ስሜን ስሰማ አስታወከኝ። በከባድ ችግር ውስጥ እንደገባሁ አሳመነኝ” ትላለች። ምንም እንኳን ሄለን የብሪታንያ ዜጋ ብትሆንም ፖሊስ ነኝ ባዩ ፋንግ ለቻይና ተላልፋ እንደምትሰጥ ሲነግራት አመነች።
“ከዚያም ሻንጣሽን ለማዘጋጀት 24 ሰዓት አለሽ። ፖሊስ መጥቶ ወደ አየር ማረፊያ ይወስድሻል አለኝ” ትላለች።
በመቀጠልም የዋስ ገንዘብ ማምጣት ከቻለች ተላልፋ የመሰጠቷን ጉዳይ ማስቆም እንደምትችል ገለጸላት። የባንክ ሂሳቧን ዝርዝር ሁኔታ ለምርመራ ከላከች በኋላ 29 ሺህ ፓውንድ እንድትልክ ተነገራት።
“ለልጄ ለቤት መግዣ ገንዘቡን ልሰጣት ቃል ገብቼ ስለነበር አዘንኩ” ትላለች ሄለን።
በዚህ ያላበቁት ሐሰተኛ ፖሊሶቹ ሌላ 250 ሺህ ዶላር እንድታመጣ ካለበለዚያ ተላልፋ እንደምትሰጥ አስጠነቀቋት።
“ለሕይወቴ እየታገልኩ ነበር። ወደ ቻይና ከተወሰድኩ መመለስ አልችልም።”
ሄለን ከአንድ ጓደኛዋ ገንዘቡን ልትበደር ስትሞክር ግለሰቡ ለልጇ ስለ ሁኔታው ነገራት። ሄለን ለልጇም ስለ ሁኔታው አልቅሳ ሁሉም ነገር ነገረቻት። መጀመሪያ ግን ግለሰቦቹ እንዳይሰሙ ስልኳን የኩሽና መሳቢያ ውስጥ አስገብታ ልጇን ወደ መኝታ ክፍል ወስዳ በብርድ ልብስ ተሸፍነው ነበር የነገረቻት።
ልጇም ሁኔታውን በትዕግስት ካዳመጠች በኋላ እያጭበረበሯት እንደሆነ ገለጸችላት። የሄለን ባንክ ውሎ አድሮ የተጭበረበረችውን ገንዘብ መለሰላት።
“ለሁለት ሳምንታት ያህል እንቅልፍ አልተኛሁም። አንድ ሰው ሌት ተቀን ስልክህን እየተከታተለ መሆኑን እያወቅህ እንዴት ይተኛል?” ትጠይቃለች።
እንቅልፍ አጥታ ባለችበት በዚህ ወቅት ሁለት ጊዜ መኪናዋን አጋጭታ ነበር። በሰው ላይ ጉዳት ባታደርስም በሁለተኛው አደጋ መኪናዋ ከጥቅም ውጪ ሆናለች።
እነዚህ አጭበርባሪዎች ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ የቻይና የውጭ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲሰጡ ለማድረግ የራሳቸውን እገታ እንዲያቀነባብሩ ተደርገዋል።
በአውስትራሊያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በተከታታይ በማጋጠማቸው የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ መርማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
“ግለሰቦቹ ታግተናል በሚል በሰውነታቸው ላይ ደም እንዲመስል ቲማቲም ወይም ወጥ አፍስሰው በደካከመ ሁኔታ እርዳታ እንዲደረግላቸው እንዲጠይቁ ተገደዋል” ይላሉ።
ተማሪዎቹ ራሳቸውን ከሕዝብ ዕይታ በማራቅ እንዳይታዩ የሚያደርጓቸው ሲሆን፣ እነዚህም ቪዲዮዎች ቻይና ላሉ ቤተሰቦቻቸው ከገንዘብ ጥያቄ ጋር ይላካል።
እነዚህ አጭበርባሪዎች በቻይና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች የሚፈጸሙ ሲሆን፣ በርካቶቹም የሚንቀሳቀሱት እንደ ካምቦዲያ፣ ላኦስ እና ማይናማር ባሉ አገራት ነው።
ባለፈው ዓመት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች ወደ ቻይና መመለሳቸውን የቻይና የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።