ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“አሜሪካ አፍሪካን የመቀራመት ፍላጎት የላትም”አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ
አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት እንጂ አፍሪካን የመቀራመት ፍላጎት እንደሌላት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ተናገሩ።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ለቢቢሲ እንዳሉት አሜሪካ ወደ አፍሪካ የምታማትረው ብዙ ዕድሎች ስላሉ ነው።
እንጂ የአፍሪካ አገራት ከማን ጋር ወዳጅ መሆን እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው እኛ አለቃ ሆነን ልንነግራቸው አይደለም ብለዋል ዲፕሎማቷ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ አሜሪካ በአህጉሩ የተለየ ፍላጎት ያሳደረች በሚመስል መልኩ ከፍተኛ ባለሥልጣናቷን እግር አብዝተዋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት ዬለን የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን የጎበኙት ከሳምንት በፊት ነበር።
ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ጆ ባይደን እምብዛምም ባልተለመደ ሁኔታ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በዋሺንግተን በመጥራት ጉባኤ አካሄደው ነበር።
ቻይናም በአህጉሪቱ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ሲሆን፣ አዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት ጉብኝት በማድረግ አገራቸው ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምተፈልግ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ቻይና፣ ሩሲያ እና ደቡብ አፍሪካ ምዕራባውያኑን ያላስደሰተ የጋራ የጦር ልምምድ ለማድረግ እየተዘጋጁ ናቸው።
ከሩሲያ እና ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሌላ ቻይናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ወደ አፍሪካ አገራት ጉብኝት አዘውትራለች።
“እኛ ወደዚህ አህጉር መምጣት ከጀመርን ዘመናት ተቆጥረዋል። በዚህ አህጉር ብዙ ዕድሎች እንዳሉ ይሰማናል። ይሁንና የአሜሪካ ፍላጎት አብሮ የመሥራት እንጂ አፍሪካን የመቀራመት አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል፤ አምባሳደር ሊንዳ።
ሩሲያ እያካሄደችው ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ደቡብ አፍሪካ ለሞስኮ ባሳየችው መልካም ግንኙነት በምዕራቡ ዓለም ስትተች ቆይታለች።
አምባሳደር ሊንዳ የሩሲያው ወታደራዊ ቅጥረኛ ቡድን ዋግነር ወደ አፍሪካ ምድር እየሰረገ መሆኑ አደገኛ እንደሆነም አመላክተዋል።
“ዋግነር በማሊ ሴቶችን መድፈርን ጨምሮ በርካታ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያደርሳል፤ በሴንትራል አፍሪካም ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማል” ሲሉ ቡድኑን ኮንነዋል።
በፍጥነት እያደገ ካለ ምጣኔ ሃብት ጋር ተያይዞ አፍሪካ ከፍተኛ የጥሬ ዕቃ ክምችት ያላት አህጉር ናት።
ከዚህም ባሻገር አፍሪካ ከሌላው አህጉር በተለየ በርካታ ወጣት ያላት ሲሆን የሕዝብ ቁጥሯም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ያለ ከመሆኑ አንጻር ብልጹግ አገራት ለመጪ ዘመን ሰፊ የገበያ ፍላጎታቸው ሁነኛ ተስፋ ሆና ትታያቸዋለች።