ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሰናል በሜዳው ከቪላ አቻ ቢወጣም አርቴታ "በልጆቼ ኮርቻለሁ" አሉ
አርሰናል በሜዳው አስተን ቪላን አስተናግዶ በሁለት ጎል ልዩነት መምራት ቢልችልም ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበት አቻ ወጥቷል።
መድፈኞቹ በጨዋታው መገባደጃ ያስቆጠሩት ጎል ተሽሮባቸዋል።
ካይ ሀቨርትዝ ጨዋታው ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የማሸነፊያውን ጎል ቢያስቆጥርም ሚኬል ሜሪኖ የመታውን ኳስ በእጁ ነክቷል በሚል ተሰርዞበታል።
አርሰናል በጋብርኤል ማርቲኔሊ እና ካይ ሀቨርትዝ ጎሎች ጨዋታውን እየመራ ሳለ ነው የቪላ ዩሪ ቲሌሜንስ በጭንቅላቱ ባስቆጠራት ጎል የቪላን መነቃቃት የመለሰው።
ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ኦሊ ዋትኪንስ ያገኛትን ኳስ ከመረብ በማገናኘት ቪላ አቻ እንዲሆን አስችሏል።
የአርሰናል የክንፍ መስመር ተጫዋች ሊሳንድሮ ትሮሳርድ ለሁለቱም ጎሎች ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል። በጭማሪ ሰዓት ወደ ጎል የሰደዳት ኳስ የመረቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጭ ወጥታለች።
ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል ከመሪው ሊቨርፑል በስድስት ነጥብ ርቆ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የአርን ስሎት ቡድን ሊቨርፑል አንድ ቀሪ ጨዋታ አለው።
ቪላ ደግሞ ወደ ሰባተኛ ደረጃ የመጣ ሲሆን አራተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኒውካስል በሁለት ነጥብ ልዩነት ላይ ይገኛል።
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት "ልጆቼ በስድስት ቀናት በሶስት ጨዋታዎች ባሳዩት ውጤት ኮርቻለሁ" ብለዋል።
"በጣም ድንቅ ነበሩ። ከጨዋታው ከዚህ የተሻለ ውጤት ማግኘት ነበረብን። በጠቅላላው ኩራት ነው የሚሰማኝ።"
አርሰናል በሜዳው በሁለት ጎሎች ልዩነት እየመራ ነጥብ ሲጥል ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ቪላ ደግሞ በሁለት ጎሎች ልዩነት እየተመራ ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ ከ15 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው።
በሌሎች ጨዋታዎች ቦርንመዝ ወደ ኒውካስል ሜዳ አቅንቶ 4-1 ረትቶ ተመልሷል። የቦርንመዙ ጀስቲን ክላይቨርት ሶስት ጎሎች በማስቆተር ሀት-ትሪክ ሰርቷል።
የሊጉ መሪ ሊቨርፑል በመጨረሻዎች ደቂቃዎች በዳርዊን ኑኔዝ አማካይነት ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ብሬንትፈርድን አሸንፎ ተመልሷል።
ሌስተር ሲቲ በፉልሀም ዌስት ሀም በክሪስታል ፓላስ በተመሳሳይ ሁለት ለምንም ተሸንፈዋል።
እሑድ ኤቨርተን ከቶተንሀም፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ከብራይተን፣ ኖቲንግሀም ከሳውዝአምፕተን እንዲሁም ኢፕስዊች ከማንቸስተር ሲቲ ይጫወታሉ።
ሊጉን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሊቨርፑል በ50 ነጥብ ሲመራ አርሰናል በ44 ነጥብ ሁለተኛ፤ ኖቲንግሀም ደግሞ በ41 ነጥብ ሶስተኛ በመሆን ይከተላሉ።