ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማቀራረብ በቱርክ የተደረገው ውይይት ጉልህ ውጤት ሳያመጣ ተጠናቀቀ
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ለማርገብ ለሁለት ቀናት በቱርክ መዲና አንካራ ሲደረግ የነበረው ድርድር ጉልህ ለውጥ ሳያሳይ ተጠናቀቀ።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የሚያስገኝላትን የመግባቢያ ሠነድ ከፈረመች በኋላ በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ የምትለውን የባሕር በር ያስገኝላታል የተባለ ሲሆን ሶማሊላንድ ደግሞ በምላሹ የአገርነት እውቅና ከኢትዮጵያ ታገኛለች ተብሏል።
ሶማሊያ በበኩሏ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው ስትል ቆይታለች።
ይህን ተከትሎ የሁለቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሁለተኛ ዙር ድርድር አንካራ ላይ ተሰባስበው ነበር።
በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አደራዳሪነት የተደረገው ንግግር ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ የሦስቱ አገራት ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ ለውጥ ተገኝቷል ብለዋል።
እንደቀደመው የአንካራ ድርድር በሁለተኛው ዙር እንዲሁ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፊት ለፊት አልተገናኙም።
ቀጥተኛ ካልሆነው ሁለተኛ ዙር ንግግር በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን “በዋነኛ መርሆች ላይ መግባባት ተደርሷል” ብለዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሦስተኛ ዙር ንግግር ለማድረግ ለመስከረም 7/2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙን ተናግረዋል።
“ለሦስተኛ ዙር ድርድር ስንዘጋጅ፤ እየገነባን ያለነው መነሳሳት ወደ መጨረሻው መፍትሄ ይወስደናል ብለን ተሰፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ታዬ አፅቀሥላሴ አገራቸው “አሁን ላይ ያለውን ልዩነት የሚፈታ እና ግንኙነትን የሚያድስ ንግግር ለማድረግ” ዝግጁ ናት ብለዋል።
የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞሊም ቱርክ ሁለቱን አገራት ለማደራደር የምታደርገውን ጥረት አድንቀው ሁሉንም ሊያግባባ ከሚችል ስምምነት ለመድረስ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ አንካራ ከማቅናታቸው በፊት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ማህሙድን ከስምምነት በሚደረስበት ሁኔታ ላይ ነሐሴ 4 እና 5/ 2016 ዓ.ም. አነጋግረዋቸዋል።
በቱርክ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ትብብር አስፈላጊነት አጽንኦት የሰጡት ኤርዶዋን፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ አገራቸው ጥረቷን እንደምትቀጥል መናገራቸውን የቱርክ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኤክስ ገጹ አስፍሮ ነበር።
ቱርክ ከሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት።
ቱርክ የሶማሊያ የቅርብ አጋር ስትሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት በተጨማሪ ለበርካታ ሶማሊያውያን የትምህርት ዕድል ትሰጣለች።
ከወራት በፊትም ቱርክ እና ሶማሊያ ጉልህ የሚባል ምጣኔ ሀብታዊ እና ወታደራዊ ስምምነት አድርገው ግዙፍ የቱርክ የጦር መርከብ ወደ ሶማሊያ መላኳ ይታወሳል።
በአውሮፓውያኑ 2017 ቱርክ በሞቃዲሾ ትልቁን የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር ያቋቋመች ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ደግሞ ቱርክ እና ሶማሊያ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ፈርመዋል።
በተመሳሳይ ቱርክ እና ኢትዮጵያ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስሮች አላት።
ኢትዮጵያ ቱርክ ሰራሽ የሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከሚገዙ ቀዳሚ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ነች።
ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ አገራት ከጥቂት ዓመታት በፊት ዝርዝሩ ይፋ ያልሆነ ደታደራዊ ስምምነቶችን ተፈራርመው ነበር።
ቱርክ እንዲሁ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ቀጥረው የሚገኙ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ግዙፍ የኢንደስትሪ ባለቤት ነች።